የአምላክ ዓላማ ወደ ፍጻሜው ይገሰግሳል
ክፍል 8
የአምላክ ዓላማ ወደ ፍጻሜው ይገሰግሳል
1, 2. አምላክ መከራን ለማስወገድ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው እንዴት ነው?
የአመፀኞች ሰዎችና አጋንንት አገዛዝ ሰብአዊውን ቤተሰብ ለብዙ መቶ ዘመናት ወደ አዘቅት አስገብቶ ሲጎትታቸው ቆይቷል። ሆኖም አምላክ ሥቃያችንን በቸልታ ተመልክቶ አያውቅም። ከዚህ ይልቅ ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ሰዎችን ከክፋትና ከሥቃይ መዳፍ ለማስለቀቅ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።
2 በኤደኑ አመፅ ጊዜ አምላክ ይህችን ምድር ለሰዎች ገነታዊ ቤት የሚያደርግ መንግሥት ለማቋቋም ያለውን ዓላማ መግለጽ ጀመረ። (ዘፍጥረት 3:15) በኋላም የአምላክ ዋና ቃል አቀባይ የሆነው ኢየሱስ ይህችን መጪ የአምላክ መንግሥት የትምህርቱ ዋና ርዕስ አደረጋት። የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ እርሷ እንደሆነች ተናገረ።—ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ 12:21
3. ኢየሱስ ለምድር የሚመጣላትን መስተዳድር ምን ብሎ ጠርቶታል? ለምንስ?
3 ያች ወደፊት የምትመጣው የአምላክ መንግሥት የምትገዛው ከሰማይ ስለሚሆን ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት” በማለት ጠርቷታል። (ማቴዎስ 4:17) በተጨማሪም የመንግሥቲቱ አመንጪ አምላክ ስለሆነ “የእግዚአብሔር መንግሥት” በማለት ጠርቷታል። (ሉቃስ 17:20) የመንግሥቲቱ አባላት ስለሚሆኑት ሰዎችና መንግሥቲቱም ምን እንደምታከናውን አምላክ በየዘመኑ የነበሩትን ጸሐፊዎቹን ትንቢት እንዲጽፉ በመንፈሱ መርቷቸዋል።
አዲሱ የምድር ንጉሥ
4, 5. ኢየሱስ የአምላክን ተቀባይነት ያገኘ ንጉሥ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነበር?
4 የመንግሥቲቱ ንጉሥ ማን ስለመሆኑ የሚናገሩትን ትንቢቶች ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የፈጸማቸው ኢየሱስ ነው። በሰው ልጆች ላይ በምትገዛው በዚያች ሰማያዊት መንግሥት መሪ እንዲሆን የተመረጠው ኢየሱስ መሆኑ ተረጋገጠ። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ በሰማይ ኃያልና የማይሞት መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ እንዲኖር አምላክ አስነሣው። ትንሣኤ ለማግኘቱ ብዙ ምሥክሮች ነበሩ።—ሥራ 4:10፤ 9:1–9፤ ሮሜ 1:1–4፤ 1 ቆሮንቶስ 15:3–8
5 ከዚያ በኋላ ኢየሱስ “በእግዚአብሐር ቀኝ ተቀመጠ።” (ዕብራውያን 10:12) እዚያም የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ እርምጃ እንዲወስድ አምላክ ሥልጣን እስኪሰጠው ድረስ ተጠባብቋል። ይህም አምላክ “ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” ብሎ ለኢየሱስ የተናገረበትን በመዝሙር 110:1 ላይ የሚገኘውን ትንቢት የሚፈጽም ነበር።
6. ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ለመሆን ብቁ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ በምድር ሳለ ለዚህ ቦታ ብቁ መሆኑን አሳይቷል። ከባድ ስደት ቢደርስበትም ለአምላክ ፍጹም አቋሙን ጠብቋል። እንዲህ በማድረጉም ፈተና ሲደርስበት ለአምላክ ታማኝ የሚሆን ሰው አይገኝም ብሎ ሰይጣን የተናገረው ክስ ውሸት መሆኑን አሳይቷል። ፍጹሙ ሰው የነበረው ‘ሁለተኛው አዳም’፣ ኢየሱስ አምላክ ፍጹማን ሰዎችን መፍጠሩ ምንም ስሕተት እንዳልነበረ አሳይቷል።—1 ቆሮንቶስ 15:22, 45፤ ማቴዎስ 4:1–11
7, 8.ኢየሱስ በምድር ሳለ ምን መልካም ሥራዎችን ሠርቷል? በዚህስ ምን አሳይቷል?
7 ኢየሱስ በጥቂት የአገልግሎቱ ዓመታት ያከናወናቸውን መልካም ነገሮች ያህል ያከናወነ የትኛው መሪ ነው? ኢየሱስ ከአምላክ መንፈስ ባገኘው ኃይል አማካኝነት ሕሙማንን፣ ሽባዎችን፣ ዕውሮችን፣ ደንቆሮችንና ዲዳዎችን ይፈውስ ነበር። ሙታንን ሳይቀር አስነስቷል! መንግሥታዊ ኃይል ሲጨብጥ በምድር ዙሪያ ለሰው ልጆች ምን ሊያደርግላቸው እንደሚችል በትንሹ አሳይቷል።—ማቴዎስ 15:30, 31፤ ሉቃስ 7:11–16
8 ኢየሱስ በምድር ሳለ ብዙ ጥሩ ነገሮችን በመሥራቱ የተነሳ ደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ዮሐንስ 21:25 *
ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” ብሏል።—9. ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ ኢየሱስ ይጎርፉ የነበሩት ለምንድን ነው?
9 ኢየሱስ ለሰዎች ታላቅ ፍቅር የነበረው ደግና ርኅሩኅ ነበር። ኢየሱስ ችግረኞችንና ቅስማቸው የተሰበረ ሰዎችን ይረዳ ነበር፤ ሆኖም ሀብት ወይም ሥልጣን ያላቸውን ሰዎች አድልዎ አያደርግባቸውም ነበር። ቅን ልብ የነበራቸው ሰዎች ኢየሱስ “እናንተ ደካሞች፣ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” በማለት ላቀረበላቸው ፍቅራዊ ጥሪ እሺ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። (ማቴዎስ 11:28–30) ፈሪሀ አምላክ የነበራቸው ሰዎች ወደ እርሱ በመጉረፍ አገዛዙን በተስፋ ተጠባብቀዋል።—ዮሐንስ 12:19
ተባባሪ ገዥዎች
10, 11. በምድር ላይ በመግዛት ከኢየሱስ ጋር የሚተባበሩት እነማን ናቸው?
10 ሰብአዊ መስተዳድሮች የአስተዳዳሪዎች ቡድን እንዳላቸው ሁሉ የአምላክ መንግሥትም በኅብረት የሚሠራ የመሪዎች ቡድን አላት። ኢየሱስ ለቅርብ ተባባሪዎቹ ከእርሱ ጋር በሰው ልጆች ላይ አብረው እንደሚገዙ ቃል ገብቶላቸው ስለነበር ከእርሱ በቀር ሌሎችም በምድር ላይ በመግዛት ተካፋይ ይሆናሉ ማለት ነው።—ዮሐንስ 14:2, 3፤ ራዕይ 5:10፤ 20:6
11 ስለዚህ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከኢየሱስ ጋር እንዲሆኑ ለሰማያዊ ሕይወት ትንሣኤ ያገኛሉ። እነርሱም ለሰው ልጆች ዘላለማዊ በረከቶችን የምታመጣውን የአምላክን መንግሥት ይመሠርታሉ። (2 ቆሮንቶስ 4:14፤ ራዕይ 14:1–3) ስለዚህ ባለፉት ዘመናት ይሖዋ ለሰብአዊው ቤተሰብ ዘላለማዊ በረከቶችን ለሚያመጣው አመራር መሠረት ሲጥል ቆይቷል።
ከአምላክ ውጭ የሆነ አገዛዝ ሊያበቃ ነው
12, 13. የአምላክ መንግሥት አሁን ምን ለማድረግ ተዘጋጅታለች?
12 አምላክ በዚህ መቶ ዘመን በምድር ጉዳዮች ላይ እጁን ጣልቃ አስገብቷል። የዚህ ብሮሹር ክፍል 9 እንደሚገልጸው በክርስቶስ የምትመራው የአምላክ መንግሥት በ1914 መቋቋሟንና አሁን ደግሞ የሰይጣንን ጠቅላላ ሥርዓት ለማጥፋት ዝግጁ እንደሆነች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ያመለክታል። ይህች መንግሥት በክርስቶስ ‘ጠላቶች መካከል ለመግዛት’ ተዘጋጅታለች።—መዝሙር 110:2
13 ይህን በሚመለከት በዳንኤል 2:44 ላይ የሚገኘው ትንቢት “በእነዚያም [አሁን ባሉት] ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት [በሰማይ] ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ [የሰው አገዛዝ ዳግመኛ እንዲኖር አይፈቀድለትም።] [ይህችም የአምላክ መንግሥት] እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች” ይላል።
14. የሰው አገዛዝ በማክተሙ ምክንያት የሚገኙ አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
14 ከአምላክ ውጭ የሆነ አገዛዝ በሙሉ ተወግዶ የአምላክ መንግሥት አገዛዝ በምድር ላይ ፍጹም ሥልጣን ትይዛለች። መንግሥቲቱ የምትገዛው ከሰማይ ስለሆነ በሰዎች ልትበላሽ አትችልም። የመግዛት ሥልጣንም መጀመሪያውኑ ወደነበረበት ወደ አምላክ ይመለሳል። የአምላክ አገዛዝ ምድርን በሙሉ ስለምትቆጣጠር በሐሰት ሃይማኖቶች ወይም አጥጋቢ ባልሆኑ የሰው ፍልስፍናዎችና ፖለቲካዊ ንድፈ ሐሳቦች የሚሳሳት ሰው አይኖርም። ከእነዚህ ነገሮች ውስጥ አንዱም እንዲኖር አይፈቀድለትም።—ማቴዎስ 7:15–23፤ ራዕይ ምዕራፍ 17 እስከ 19
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.8 ስለ ኢየሱስ ሕይወት ሙሉ ማብራሪያ ለማግኘት በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የበለጠው ታላቅ ሰው የተሰኘውን በ1991 በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተዘጋጀ መጽሐፍ ይመልከቱ።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በመጪው አዲስ ዓለም ምን እንደሚሠራ ለማሳየት በምድር ሳለ ሕሙማንን ይፈውስና የሞቱትንም ያስነሣ ነበር
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ ሰማያዊት መንግሥት ከአምላክ ውጭ የሆነ ማንኛውንም ዓይነት አገዛዝ ደምስሳ እንዳልነበረ ታደርጋለች