የዓመፅ ውጤት ምን ሆነ?
ክፍል 7
የዓመፅ ውጤት ምን ሆነ?
1-3. የይሖዋን ትክክለኛነት ጊዜ ያረጋገጠው እንዴት ነው?
አምላክ ባለው የመግዛት መብት ላይ የተነሳውን ጥያቄ በተመለከተ ሰዎች ያለ አምላክ እርዳታ በራሳቸው ሐሳብ እየተመሩ ለብዙ መቶ ዘመናት ራሳቸውን የገዙበት የሰው አገዛዝ ምን ውጤት አስገኘ? ሰዎች ከአምላክ የተሻሉ ገዢዎች ለመሆን በቅተዋልን? ሰው በሰው ላይ በፈጸመው ኢሰብአዊነት መሠረት እንፍረድ ከተባለ ሰዎች ከአምላክ በተሻለ ሁኔታ ራሳቸውን በራሳቸው ለመግዛት እንዳልበቁ ጥርጥር የለውም።
2 የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የአምላክን አገዛዝ አንፈልግም ባሉ ጊዜ ችግር ተከተለ። በራሳቸውና ከእነርሱ በመጡት ሰብአዊ ቤተሰብ ሁሉ ላይ መከራን አመጡ። ለዚህም ተወቃሹ ራሳቸው እንጂ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። የአምላክ ቃል “እነርሱ ረከሱ፤ ልጆቹም አይደሉም፤ ጉድለቱ የራሳቸው ነው” ይላል። — ዘዳግም 32:5 አዓት
3 አዳምና ሔዋን ከአምላክ ዝግጅት ቢወጡ ሰውነታቸው እየደከመ ከሄደ በኋላ በመጨረሻ እንደሚሞቱ አምላክ የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ትክክለኛነት ታሪክ አረጋግጧል። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:19) ከአምላክ አገዛዝ ስለወጡ አካላቸው እየደከመ ሄደና ከጊዜ በኋላ ሞቱ።
4. ሁላችንም ፍጽምና የሌለንና ለበሽታና ለሞት የተጋለጥን ሆነን የተወለድነው ለምንድን ነው?
4 በኋላም በዘሮቻቸው ሁሉ ላይ የደረሰው ነገር ሮሜ 5:12 እንደገለጸው ነው:- “ኃጢአት በአንድ ሰው [የሰብአዊው ቤተሰብ ራስ በነበረው በአዳም] ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” ስለዚህ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በአምላክ የበላይ ተቆጣጣሪነት ላይ ባመፁ ጊዜ እንከን ያለባቸው ኃጢአተኞች ሆኑ። ወላጆች ባሕሪያቸውን ለልጆቻቸው እንዲያወርሱ ከሚያደርገው የተፈጥሮ ሕግ ጋር በሚስማማ መንገድ አዳምና ሔዋንም ለዘሮቻቸው ማውረስ የሚችሉት የአመፃቸው ውጤት የሆነውን አለፍጽምና ነበር። ሁላችንም እንከን ያለብን፣ ለበሽታና ለሞት የተጋለጥን ሆነን የተወለድነው ለዚህ ነው።
5, 6. ሰው እውነተኛ ሰላምንና ብልጽግናን ለማምጣት ስላደረገው ጥረት ታሪክ ምን ያሳያል?
5 በዚህ ሁኔታ ብዙ መቶ ዘመናት አልፈዋል። ብዙ አገዛዞች ተፈራርቀዋል። በአእምሮ ሊታሰብ የሚችል መስተዳድር በሙሉ ተሞክሯል። ሆኖም በሰብአዊው ቤተሰብ ላይ በተደጋጋሚ አሰቃቂ ነገሮች ደርሰዋል። አሁን ስድስት ሺህ ዓመታት ካለፉ በኋላ ሰዎች በምድር ዙሪያ ሰላምን፣ ፍትሕንና ብልጽግናን ለሰው ሁሉ ለማምጣትና ባሁኑ ወቅት የደግነትን፣ የርህራኄንና የትብብርን መልካም ጥቅሞች ጠንቅቀው አውቀው መሆን አለባቸው ተብሎ ሊታሰብ ይችል ይሆናል።
6 እውነቱ ግን የዚህ ቀጥተኛ ተቃራኒ ነው። ሰው የፈጠረው የትኛውም ዓይነት መስተዳድር ለሁሉም ሰው እውነተኛ ሰላምንና ብልጽግናን አላመጣም። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ብቻ በጀርመን ሆን ተብሎ በተጠነሰሰ ሤራ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ በጦርነቶች ደግሞ ከ100 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ሰዎች ታርደዋል። በዘመናችን ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሰዎች ባለመቻቻልና በፖለቲካዊ ልዩነቶች ሳቢያ በድብደባ ተሰቃይተዋል፣ ተገድለዋል፣ እንዲሁም ታስረዋል።
ዛሬ ያለው ሁኔታ
7. በዛሬው ጊዜ ያለው የሰብአዊው ቤተሰብ ሁኔታ እንዴት ሊገለጽ ይችላል?
7 በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ ሰብአዊው ቤተሰብ ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ ተመልከቱ። ወንጀልና አመፅ ተዛምቷል። በአደንዛዥ ዕፆች አለአግባብ መጠቀም እንደወረርሽኝ ተስፋፍቷል። በሩካቤ ሥጋ የሚተላለፉ በሽታዎች ወረርሽኝ ሆነዋል። አስፈሪው የኤድስ በሽታ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን እየቀሰፈ ነው። በያመቱ በአሥር ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሀብ ወይም በበሽታ ምክንያት ሲሞቱ በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ግን በጣም ብዙ ሀብት አላቸው። ሰዎች ምድርን እየበከሏትና እየበዘበዙአት ነው። በየትኛውም ቦታ የቤተሰብ ሕይወትና የሥነ ምግባር ደንቦች ፈራርሰዋል። በእርግጥም በዛሬው ጊዜ ያለው ኑሮ የሚያንፀባርቀው ‘የዚህ ዓለም አምላክ’ የሆነውን የሰይጣንን አስከፊ አገዛዝ ነው። ሰይጣን የሚገዛው ዓለም ለሰው የፍቅር፣ የርህራኄና የወዳጅነት ስሜት የሌለው ስሜተ ቀዝቃዛ፣ ጨካኝና በጠቅላላው ምግባረ ብልሹ ነው። — 2 ቆሮንቶስ 4:4
8. የሰው ልጆች የደረሱባቸውን ከፍተኛ የሥራ ውጤቶች እውነተኛ መሻሻል ብለን ልንጠራቸው የማንችለው ለምንድን ነው?
8 ሰዎች በሳይንሳዊና በቁሳዊ ዕድገታቸው ጽንፍ ላይ እንዲደርሱ አምላክ በቂ ጊዜ ፈቅዶላቸዋል። ይሁንና ደጋንና ቀስት በጠመንጃ፣ በታንክ፣ በቦምብ ጣይ ጄቶችና በኑክሌር ሚሳይሎች ሲተኩ ይህ እውነተኛ መሻሻል ነውን? ሰዎች ወደ ጠፈር መጓዝ ችለው በምድር
ላይ ግን በሰላም አብረው መኖር ሲያቅታቸው ይህ መሻሻል ነውን? በወንጀልና በአመፅ መብዛት ምክንያት ሰዎች በምሽት ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ቦታዎች በቀንም ሳይቀር በመንገድ ላይ በእግር መዘዋወር ሲፈሩ ይህ መሻሻል ነውን?ጊዜ ምን አሳይቷል?
9, 10. (ሀ) ያለፉት መቶ ዘመናት በግልጽ ያሳዩት ምንድን ነው? (ለ) አምላክ ነፃ ምርጫን ቀምቶ የማይወስደው ለምንድን ነው?
9 በመቶ የሚቆጠሩ ዓመታት የሙከራ ጊዜ ያሳየው ሰዎች ከአምላክ አመራር ወጥተው አካሄዳቸውን በተሳካ ሁኔታ ሊያቀኑ የማይችሉ መሆናቸውን ነው። ሰዎች ሳይበሉ፣ ሳይጠጡና ሳይተነፍሱ ለመኖር እንደማይችሉ ሁሉ ከአምላክ አመራር ወጥተው አካሄዳቸውን ሊያቀኑ አይችሉም። ማስረጃው ግልጽ ነው:- ለመኖር ምግብ፣ ውሃና አየር እንደሚያስፈልገን ሆነን እንደተፈጠርን ሁሉ በፈጣሪያችን አመራር መሠረት መኖር እንደሚያስፈልገን ሆነን ተፈጥረናል።
10 አምላክ ክፋትን በመፍቀዱ በነፃ ምርጫ አለአገባብ የመጠቀምን አሳዛኝ ውጤቶች ለአንዴና ለሁልጊዜው አሳይቷል። ነፃ ምርጫ በጣም ክቡር ስጦታ በመሆኑ አምላክ እሱን ከሰዎች በመንጠቅ ፈንታ አለአገባብ ሲጠቀሙበት ምን ውጤት እንደሚያስከትል እንዲያዩ አስችሎአቸዋል። የአምላክ ቃል “የሰው መንገድ አካሄዱን ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” ሲል እውነቱን ተናግሯል። “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” ያለውም እውነቱን ነው። — ኤርምያስ 10:23፤ መክብብ 8:9
11. መከራን ሊያስወግድ የቻለ የሰው አገዛዝ አለን?
11 አምላክ የሰውን አገዛዝ ለስድስት ሺህ ዓመታት መፍቀዱ ሰው መከራን ለማቆም እንደማይችል በማይረሳ መንገድ አሳይቷል። ሰው ከዚህ በፊትም መከራን አቁሞ አያውቅም። ለምሳሌ ያህል ንጉሥ ሰሎሞንም እንኳን በዘመኑ ከዚያ ሁሉ ጥበቡ፣ ሀብቱና ሥልጣኑ ጋር የሰው አገዛዝ የሚያስከትለውን ሥቃይ ሊያስወግድ አልቻለም ነበር። (መክብብ 4:1–3) በተመሳሳይም በዘመናችን የዓለም መሪዎች በጣም ዘመናዊ ከሆኑ የቴክኒክ ሥልጣኔያቸው ሁሉ ጋርም እንኳን ሥቃይን ሊያስወግዱ አልቻሉም። እንዲያውም በዚህ ምትክ ከአምላክ አገዛዝ ውጭ የሆኑ ሰዎች የባሰ ሥቃይን እንደጨመሩ ታሪክ አረጋግጧል።
የአምላክ አርቆ ተመልካችነት
12-14. አምላክ መከራን በመፍቀዱ ምን ዘላቂ ጥቅም ይገኛል?
12 አምላክ መከራን መፍቀዱ ለእኛ ስቃይ ሆኖብናል። ይሁን እንጂ እርሱ የመጨረሻውን ጥሩ ውጤት ስለሚያውቅ አርቆ አስተዋይነቱን አሳይቷል። የአምላክ አርቆ ተመልካችነት ለፍጥረታቱ የሚጠቅም ነው፤ ያውም ለጥቂት ዓመታት፣ ለጥቂት ሺህ ወይም ለሚልዮን ዓመታት ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ዓለም የሚጠቅም ነው።
13 ምናልባት ይህ ሁሉ ካለፈ በኋላ ወደፊት አንድ ሰው በአምላክ የአሠራር መንገድ ላይ ጥያቄ በማንሣት በነፃ ምርጫው አለአገባብ የሚጠቀምበት ሁኔታ ቢፈጠር አባባሉን እንዲያረጋግጥ ጊዜ መፍቀድ የማያስፈልግ ይሆናል። አምላክ ለአመፀኞች በሺህ የሚቆጠር ዘመን የፈቀደላቸው ስለሆነ በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ በየትኛውም
ሥፍራ ለዘላለም ዓለም ሊጠቀምበት የሚችል ሕጋዊ መሠረት ጥሏል።14 ይሖዋ በዚህ ዘመን ክፋትንና መከራን በመፍቀዱ ከእርሱ ጋር የማይስማማ ማንኛውም ነገር ያማረ ውጤት እንደማይኖረው በበቂ ሁኔታ የተረጋገጠ ሆኗል። በራሱ ሐሳብ የሚመራ የሰዎች ወይም የመንፈሳዊ ፍጥረታት ዕቅድ ዘላቂ ጥቅም ሊያመጣ እንደማይችል ያላንዳች ጥርጥር ይስተዋላል። ስለዚህ አምላክ ከዚያ ወዲያ ማንኛውንም ዓይነት አመፀኛ በቅጽበት ቢደመስስ ሙሉ በሙሉ ፍትሐዊ ይሆናል። “ኃጢአተኞችን ሁሉ ያጠፋል።” — መዝሙር 145:20፤ ሮሜ 3:4
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጀመሪያ ወላጆቻችን ከአምላክ አመራር ወጥተው በራሳቸው ሐሳብ ለመመራት ከመረጡ በኋላ በመጨረሻው አረጁና ሞቱ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአምላክ ውጭ የሆነ የሰው አገዛዝ አሰቃቂ መሆኑ ተረጋግጧል
[ምንጭ]
የአሜሪካ የጠረፍ ጠባቂ ጓድ ፎቶ