አምላክን የሚያስደስት የቤተሰብ ሕይወት
ትምህርት 8
አምላክን የሚያስደስት የቤተሰብ ሕይወት
ባል በቤተሰብ ውስጥ ያለው ቦታ ምንድን ነው? (1)
ባል ሚስቱን እንዴት ሊይዝ ይገባል? (2)
አባት ምን ዓይነት ኃላፊነቶች አሉት? (3)
ሚስት በቤተሰብ ውስጥ ያላት የሥራ ድርሻ ምንድን ነው? (4)
አምላክ ወላጆችና ልጆች ምን እንዲያደርጉ ይፈልጋል? (5)
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለያየትና ስለ መፋታት ያለው አመለካከት ምንድን ነው? (6, 7)
1. መጽሐፍ ቅዱስ ባል የቤተሰቡ ራስ እንደሆነ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ባል አንዲት ሚስት ብቻ ልትኖረው ይገባል። ባልና ሚስት ሕጉ በሚያዘው መሠረት በአግባቡ መጋባት ይኖርባቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 3:2፤ ቲቶ 3:1
2. ባል ሚስቱን ልክ እንደራሱ መውደድ ይኖርበታል። ኢየሱስ ተከታዮቹን በያዘበት ሁኔታ ሊይዛት ይገባል። (ኤፌሶን 5:25, 28, 29) በማንኛውም መንገድ ግፍ ሊፈጽምባት ወይም ሊደበድባት አይገባም። ከዚህ ይልቅ አክብሮት ሊያሳያት ይገባል።—ቆላስይስ 3:19፤ 1 ጴጥሮስ 3:7
3. አንድ አባት ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለማቅረብ በትጋት መሥራት ይኖርበታል። ለሚስቱና ለልጆቹ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማቅረብ አለበት። በተጨማሪም አንድ አባት ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን መንፈሳዊ ነገር ማቅረብ ይኖርበታል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ቤተሰቡ ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ እንዲማር በመርዳት ረገድ ቅድሚያ ወስዶ ጥረት ያደርጋል።—ዘዳግም 6:4-9፤ ኤፌሶን 6:4
4. አንዲት ሚስት ለባልዋ ጥሩ ረዳት መሆን ይገባታል። (ዘፍጥረት 2:18) ልጆቻቸውን በማስተማርና በማሠልጠን ረገድ ባልዋን ልትረዳው ይገባል። (ምሳሌ 1:8) ሚስት ለቤተሰብዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ እንድታደርግ ይሖዋ ይፈልግባታል። (ምሳሌ 31:10, 15, 26, 27፤ ቲቶ 2:4, 5) ለባልዋ የጠለቀ አክብሮት ሊኖራት ይገባል።—ኤፌሶን 5:22, 23, 33
5. ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙ አምላክ ይፈልጋል። (ኤፌሶን 6:1-3) ይሖዋ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩና እንዲገሥጹ ይጠብቅባቸዋል። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት በቂ ጊዜ መድበው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኗቸው፣ መንፈሳዊና ስሜታዊ እንክብካቤ እንዲያደርጉላቸው ይፈልጋል። (ዘዳግም 11:18, 19፤ ምሳሌ 22:6, 15) ወላጆች ልጆቻቸውን በጭካኔ መቅጣት የለባቸውም።—ቆላስይስ 3:21
6. ባልና ሚስት ተግባብተው መኖር በሚያስቸግራቸው ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች ሥራ ላይ ለማዋል መጣር ይኖርባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር እንድናሳይና ይቅር ባዮች እንድንሆን አጥብቆ ያሳስባል። (ቆላስይስ 3:12-14) የአምላክ ቃል ለጥቃቅን ችግሮች መፍትሔው መለያየት ነው የሚል ሐሳብ አያቀርብም። ይሁን እንጂ አንዲት ሚስት ባልዋ (1) ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለማቅረብ እምቢተኛ ሲሆን፣ (2) ተደባዳቢና ጠበኛ በመሆኑ ምክንያት ለጤንነቷና ለሕይወቷ የሚያሰጋት ሲሆን ወይም (3) በሚያደርስባት ከባድ ተቃውሞ የተነሳ ይሖዋን ለማምለክ በማትችልበት ደረጃ ላይ ስትደርስ ከባልዋ ለመለየት ልትመርጥ ትችላለች።—1 ቆሮንቶስ 7:12, 13
7. ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ታማኝ መሆን አለባቸው። ምንዝር በአምላክና በትዳር ጓደኛ ላይ የሚሠራ ኃጢአት ነው። (ዕብራውያን 13:4) የትዳር ጓደኛን ፈትቶ ሌላ ለማግባት መሠረት የሚሆነው ብቸኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸም የጾታ ግንኙነት ነው። (ማቴዎስ 19:6-9፤ ሮሜ 7:2, 3) ሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ሳይኖራቸው መፋታታቸውንና ሌላ ማግባታቸውን ይሖዋ አጥብቆ ይጠላል።—ሚልክያስ 2:14-16
[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አምላክ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩና እንዲገሥጹ ይጠብቅባቸዋል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አፍቃሪ የሆነ አባት ለቤተሰቡ በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ የሚያስፈልገውን ያቀርባል