በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

ትምህርት 5

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

ይሖዋ ምድርን የፈጠረው ለምንድን ነው? (1, 2)

ምድር በአሁኑ ጊዜ ገነት ያልሆነችው ለምንድን ነው? (3)

ክፉ ሰዎች ምን ይሆናሉ? (4)

ኢየሱስ ወደፊት ለታመሙ፣ ለአረጋውያንና ለሙታን ምን ያደርግላቸዋል? (5, 6)

ወደፊት ከሚመጡት በረከቶች ተካፋይ ለመሆን ከፈለግህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? (7)

1. ይሖዋ ይህችን ምድር የፈጠረው ሰዎች ለዘላለም ተደስተው እንዲኖሩባት ነው። ፍላጎቱ ምድር ምንጊዜም ጻድቅና ደስተኛ በሆኑ ሰዎች እንድትሞላ ነበር። (መዝሙር 115:16፤ ኢሳይያስ 45:18) ምድር ለዘላለም ትኖራለች እንጂ ፈጽሞ አትጠፋም።​—መዝሙር 104:5፤ መክብብ 1:4

2. አምላክ ሰውን ከመፍጠሩ በፊት አንድ አነስተኛ የምድር ክፍል መርጦ በጣም ውብ የሆነ ገነት አደረገው። ያንንም ቦታ የኤደን የአትክልት ሥፍራ ብሎ ጠራው። የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ማለትም አዳምንና ሔዋንን ያስቀመጠው በዚህ ቦታ ነበር። አምላክ ልጆች እንዲወልዱና መላዋን ምድር እንዲሞሉ ዓላማው ነበር። ቀስ በቀስ ምድርን በሙሉ ወደ ገነትነት ይለውጣሉ።​—ዘፍጥረት 1:28፤ 2:8, 15

3. አዳምና ሔዋን ሆን ብለው የአምላክን ሕግ በመተላለፍ ኃጢአት ሠሩ። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ከኤደን አትክልት ቦታ አስወጣቸው። ገነትም ጠፋች። (ዘፍጥረት 3:1-6, 23) ቢሆንም ይሖዋ ለዚህች ምድር ያወጣውን የመጀመሪያ ዓላማ አልዘነጋም። የሰው ልጆች ለዘላለም የሚኖሩባት ገነት እንደሚያደርጋት ቃል ገብቷል። ግን ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?​—መዝሙር 37:29

4. ይህች ምድር ገነት ከመሆኗ በፊት ክፉ ሰዎች ከምድር ላይ መወገድ ይኖርባቸዋል። (መዝሙር 37:38) ይህም የሚሆነው ክፋትን ሙሉ በሙሉ በሚያጠፋው የአምላክ ጦርነት በአርማጌዶን ነው። ከዚያ ቀጥሎ ሰይጣን ለ1,000 ዓመት ይታሠራል። ምድርን የሚያበላሹ ክፉ ፍጥረታት አይኖሩም ማለት ነው። ከዚህ ጥፋት የሚተርፉት የአምላክ ሕዝቦች ብቻ ይሆናሉ።​—ራእይ 16:14, 16፤ 20:1-3

5. ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ምድር ላይ ለ1,000 ዓመት ይነግሣል። (ራእይ 20:6) ቀስ በቀስም ኃጢአትን ከአእምሮአችንና ከሰውነታችን ያስወግዳል። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት ወደነበሩበት ሁኔታ ተመልሰን ፍጹም ሰዎች እንሆናለን። በሽታ፣ እርጅናና ሞት አይኖሩም። ሕመምተኛ የነበሩ ሰዎች ይፈወሳሉ፣ ያረጁም ወደ ወጣትነት ይመለሳሉ።​—ኢዮብ 33:25፤ ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:3, 4

6. በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ዘመን ታማኝ የሆኑ ሰዎች መላዋን ምድር ገነት ያደርጓታል። (ሉቃስ 23:43) በተጨማሪም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሞተው የነበሩ ሰዎች ተነስተው በምድር ላይ መኖር ይጀምራሉ። (ሥራ 24:15) አምላክ የሚፈልግባቸውን ነገሮች ከፈጸሙ ለዘላለም በምድር ላይ ይኖራሉ። ካልፈጸሙ ደግሞ ለዘላለም ይጠፋሉ።​—ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 20:11-15

7. በዚህ መንገድ አምላክ ለምድር ያወጣው የመጀመሪያ ዓላማ በተሳካ ሁኔታ ይፈጸማል። ወደፊት ከሚመጡት ከእነዚህ በረከቶች ተካፋይ ለመሆን ትፈልጋለህ? የምትፈልግ ከሆነ ስለ ይሖዋ መማርህን መቀጠልና እርሱ የሚፈልግብህን ነገሮች መፈጸምህን መቀጠል ይገባሃል። በዚህ ረገድ በአቅራቢያህ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች መገኘት በጣም ይረዳሃል።​—ኢሳይያስ 11:9፤ ዕብራውያን 10:24, 25

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጠፋችው ገነት

[በገጽ 11 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከአርማጌዶን በኋላ ምድር ገነት ትሆናለች