አምላክ ምን እንደሚፈልግብህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?
ትምህርት 1
አምላክ ምን እንደሚፈልግብህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን አስፈላጊ እውቀት ይገኛል? (1)
የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ማን ነው? (2)
መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚኖርብህ ለምንድን ነው? (3)
1. መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ውድ የሆነ የአምላክ ስጦታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ አፍቃሪ አባት ለልጆቹ የጻፈውን ደብዳቤ ይመስላል። ስለ አምላክ እውነቱን፣ ማለትም እርሱ ማን እንደሆነና ሕጎቹ ምን እንደሆኑ ይነግረናል። የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንዴት እንደምንወጣና እውነተኛ ደስታ እንዴት እንደምናገኝ ይገልጽልናል። አምላክን ለማስደሰት ምን ማድረግ እንደሚኖርብን የሚነግረን ብቸኛ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።—መዝሙር 1:1-3፤ ኢሳይያስ 48:17, 18
2. መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ከ1513 ከዘአበ ጀምሮ በ1,600 ዓመታት ጊዜና 40 በሚያክሉ የተለያዩ ሰዎች ነው። 66 የሚያክሉ ትንንሽ መጻሕፍት ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት በአምላክ መንፈስ የተነሳሱ ሰዎች ናቸው። የጻፉትም የራሳቸውን ሳይሆን የአምላክን ሐሳብ ነው። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ በሰማይ የሚኖረው አምላክ እንጂ ማንኛውም ምድራዊ ሰው አይደለም።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17፤ 2 ጴጥሮስ 1:20, 21
3. በተጨማሪም አምላክ መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል እንዲገለበጥና እስከ ዘመናችን ተጠብቆ እንዲኖር አድርጓል። የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዛት የታተመ መጽሐፍ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በመጀመርህ የማይደሰቱ ሰዎች ይኖራሉ፤ ይሁን እንጂ የእነዚህ ሰዎች ተቃውሞ ጥናትህን እንድታቆም ሊያደርግህ አይገባም። ዘላለማዊ የሆነው የወደፊት ተስፋህ የተመካው የሚደርስብህን ተቃውሞ በሙሉ ተቋቁመህ አምላክን በማወቅህና ፈቃዱን በማድረግህ ላይ ነው።—ማቴዎስ 5:10-12፤ ዮሐንስ 17:3