በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ የሚጠላቸው ድርጊቶች

አምላክ የሚጠላቸው ድርጊቶች

ትምህርት 10

አምላክ የሚጠላቸው ድርጊቶች

አምላክ መጥፎ ናቸው ስለሚላቸው ድርጊቶች እንዴት ሊሰማህ ይገባል? (1)

ስህተት የሆኑ ወሲባዊ ምግባሮች የትኞቹ ናቸው? (2)

አንድ ክርስቲያን የሚከተሉትን ድርጊቶች እንዴት መመልከት ይኖርበታል:- መዋሸትን? (3) ቁማርን? (3) ስርቆትን? (3) ጠበኝነትን? (4) መናፍስታዊ እምነትን? (5) ስካርን? (6)

አንድ ሰው ከመጥፎ ድርጊቶች መላቀቅ የሚችለው እንዴት ነው? (7)

1. የአምላክ አገልጋዮች ጥሩ የሆነውን ነገር ሁሉ ይወድዳሉ። ይሁን እንጂ ክፉ የሆነውን ነገር ደግሞ መጥላት አለባቸው። (መዝሙር 97:10) አምላክ የሚጠላቸውን አንዳንድ ድርጊቶች ማስወገድ አለባቸው ማለት ነው። ከእነዚህ ድርጊቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

2. ዝሙት:- ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸም፣ ምንዝር፣ ከእንስሳት ወይም ከቅርብ ዘመድ ጋር ወሲብ መፈጸም፣ እንዲሁም ግብረ ሰዶም በአምላክ ላይ የሚሠሩ ከባድ ኃጢአቶች ናቸው። (ዘሌዋውያን 18:6፤ ሮሜ 1:26, 27፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) አንድ ወንድና ሴት ሕጋዊ ጋብቻ ሳይኖራቸው አብረው የሚኖሩ ከሆነ መለያየት አለበለዚያም ሕጋዊ ጋብቻ መፈጸም ይኖርባቸዋል።​—ዕብራውያን 13:4

3. መዋሸት፣ ቁማር፣ ስርቆት:- ይሖዋ አምላክ ሊዋሽ አይችልም። (ቲቶ 1:2 አዓት) የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ደግሞ መዋሸት የለባቸውም። (ምሳሌ 6:16-19፤ ቆላስይስ 3:9, 10) ማንኛውንም ዓይነት ቁማር የሚጫወቱ ሰዎች የስግብግብነት መንፈስ የተጠናወታቸው ናቸው። በዚህም ምክንያት ክርስቲያኖች እንደ ሎተሪ፣ በፈረስ ግልቢያ እንደ መወራረድና እንደ ቢንጎ በመሰሉትና በማንኛውም ዓይነት ሌላ ቁማር አይካፈሉም። (ኤፌሶን 5:3-5) በተጨማሪም ክርስቲያኖች አይሠርቁም። የሌላ ሰው ዕቃ ሳያስፈቅዱ አይወስዱም ወይም እያወቁ የተሠረቀ ዕቃ አይገዙም።​—ዘጸአት 20:15፤ ኤፌሶን 4:28

4. ቁጣ፣ ጠበኝነት:- ቁጣ ልጓም ካልተደረገለት ወደ ጠብ ያደርሳል። (ዘፍጥረት 4:5-8) ጠበኛ የሆነ ሰው የአምላክ ወዳጅ ሊሆን አይችልም። (መዝሙር 11:5፤ ምሳሌ 22:24, 25) ሌሎችን መበቀል ወይም ሰዎች መጥፎ ነገር ሲያደርጉብን አጸፋዊ እርምጃ መውሰድ ስህተት ነው።​—ምሳሌ 24:29፤ ሮሜ 12:17-21

5. አስማታዊ ድግምትና መናፍስታዊ እምነት:- አንዳንድ ሰዎች የታመሙ ሰዎችን ለማዳን በመናፍስታዊ ኃይሎች ይጠቀማሉ። ሌሎች ደግሞ ጠላቶቻቸውን እንዲታመሙ ለማድረግ ወይም ለመግደል ሲሉ ያስደግሙባቸዋል ወይም አስማት ያደርጉባቸዋል። እንዲህ ያለው ኃይል የሚመጣው ከሰይጣን ነው። ስለዚህ ክርስቲያኖች በማናቸውም እንዲህ ያሉ ድርጊቶች መካፈል የለባቸውም። (ዘዳግም 18:9-13) ራሳችንን ሌሎች ከሚፈጽሙብን አስማት ወይም ድግምት ልንጠብቅ የምንችልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ከይሖዋ ጋር መቀራረብ ነው።​—ምሳሌ 18:10

6. ስካር:- ጥቂት ወይን ጠጅ፣ ቢራ ወይም ሌላ ዓይነት የአልኮል መጠጥ መጠጣት ስህተት አይደለም። (መዝሙር 104:15፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:23) ከመጠን በላይ መጠጣትና መስከር ግን በአምላክ ዘንድ ኃጢአት ነው። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:8) ከመጠን በላይ መጠጣት ጤንነትህን ከመጉዳቱም በላይ ቤተሰብህን ያናጋል። በተጨማሪም ለሌሎች ፈተናዎች በቀላሉ እንድትሸነፍ ሊያደርግህ ይችላል።​—ምሳሌ 23:20, 21, 29-35

7. አምላክ መጥፎ ናቸው የሚላቸውን ድርጊቶች የሚፈጽሙ ሰዎች “የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (ገላትያ 5:19-21) በእርግጥ አምላክን የምትወድና እርሱንም ለማስደሰት የምትፈልግ ከሆንክ እንደነዚህ የመሰሉትን ድርጊቶች ከመፈጸም ልትርቅ ትችላለህ። (1 ዮሐንስ 5:3) አምላክ መጥፎ ናቸው የሚላቸውን ነገሮች መጥላትን ተማር። (ሮሜ 12:9) አምላካዊ ልማዶች ካሏቸው ሰዎች ጋር አብረህ ዋል። (ምሳሌ 13:20) በዚህ ረገድ ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር ባልንጀራ መሆን ሊረዳህ ይችላል። (ያዕቆብ 5:14) ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላክ በጸሎት አማካኝነት በሚሰጠው እርዳታ ተማመን።​—ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13

[በገጽ 20 እና 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አምላክ ስካርን፣ ስርቆትን፣ ቁማርንና የጠበኝነት ድርጊቶችን ይጠላል