በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

ትምህርት 3

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

ኢየሱስ የአምላክ ‘የበኩር’ ልጅ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? (1)

“ቃል” የተባለውስ ለምንድን ነው? (1)

ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር የመጣው ለምን ነበር? (2-4)

ተአምራት የፈጸመው ለምን ነበር? (5)

ኢየሱስ በቅርቡ ምን ያደርጋል? (6)

1. ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ መንፈሳዊ አካል ሆኖ ይኖር ነበር። የአምላክ የመጀመሪያ ፍጡር በመሆኑም የአምላክ ‘የበኩር’ ልጅ ተብሎ ተጠርቷል። (ቆላስይስ 1:15፤ ራእይ 3:14) አምላክ በቀጥታ የፈጠረው ልጅ ኢየሱስ ብቻ ነው። ይሖዋ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ሌሎች ፍጥረታት የፈጠረው ኢየሱስን “ዋና ሠራተኛ” አድርጎ በመጠቀም ነው። (ምሳሌ 8:22-31፤ ቆላስይስ 1:16, 17) በተጨማሪም አምላክ እንደ ዋና ቃል አቀባይ አድርጎ ተጠቅሞበታል። ኢየሱስ “ቃል” ተብሎ የሚጠራውም በዚህ ምክንያት ነው።—ዮሐንስ 1:1-3፤ ራእይ 19:13

2. አምላክ የኢየሱስን ሕይወት ወደ ማርያም ማኅፀን በማዛወር ልጁን ወደ ምድር ላከው። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ሰብዓዊ አባት አልነበረውም። ምንም ዓይነት ኃጢአት ወይም የፍጽምና ጉድለት ያልወረሰው በዚህ ምክንያት ነው። አምላክ ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ለሦስት ምክንያቶች ነው:- (1) ስለ አምላክ እውነቱን እንዲያስተምረን (ዮሐንስ 18:37)፣ (2) ፍጹም አቋም ጠብቆ እኛ ልንከተለው የሚገባንን አርዓያ እንዲያሳየን (1 ጴጥሮስ 2:21) እንዲሁም (3) ሕይወቱን ሠውቶ ከኃጢአትና ከሞት ነጻ እንዲያወጣን። መሥዋዕት ማቅረብ ያስፈለገው ለምንድን ነው?—ማቴዎስ 20:28

3. የመጀመሪያው ሰው አዳም የአምላክን ትእዛዝ በመተላለፍ መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአት” ብሎ የሚጠራውን ነገር ፈጸመ። ስለዚህም አምላክ የሞት ፍርድ ፈረደበት። (ዘፍጥረት 3:17-19) አዳም የአምላክን የአቋም ደረጃዎች ሳያሟላ በመቅረቱ ፍጽምናውን አጣ። ቀስ በቀስም አርጅቶ ሞተ። አዳም ኃጢአቱን ወደ ልጆቹ በሙሉ አስተላልፏል። እኛም የምናረጀው፣ የምንታመመውና የምንሞተው በዚህ ምክንያት ነው። ታዲያ የሰው ልጅ ከዚህ ሊድን የሚችለው እንዴት ነው?—ሮሜ 3:23፤ 5:12

4. ኢየሱስ ልክ እንደ አዳም ፍጹም ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በጣም ከባድ የሆነ ፈተና ሲያጋጥመው እንኳን ከአዳም በተለየ ሁኔታ አምላክን ፍጹም በሆነ መንገድ ታዟል። ስለዚህም ፍጹም የሆነውን ሰብዓዊ ሕይወቱን በመሠዋት ለአዳም ኃጢአት ካሣ ሊከፍል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ቤዛ” የሚለው ይህንን ነው። በዚህ መንገድ የአዳም ልጆች ከሞት ኩነኔ ነጻ ሊወጡ ይችላሉ። በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ የኃጢአት ሥርየት አግኝተው የዘላለም ሕይወት ሊወርሱ ይችላሉ።—1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6፤ ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 5:18, 19

5. ኢየሱስ በምድር ላይ ይኖር በነበረበት ጊዜ በሽተኞችን ፈውሷል፣ የተራቡትን መግቧል፣ ማዕበል ጸጥ እንዲል አድርጓል። ሙታንን እንኳን አስነስቷል። እነዚህን ተአምራት የፈጸመው ለምን ነበር? (1) ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች ያዝንና ሊረዳቸው ይፈልግ ስለ ነበረ፣ (2) ተአምራቱ የአምላክ ልጅ መሆኑን ስለሚያረጋግጡለት፣ (3) ንጉሥ ሆኖ ምድርን ሲያስተዳድር ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ምን እንደሚያደርግ ለማሳየት።—ማቴዎስ 14:14፤ ማርቆስ 2:10-12፤ ዮሐንስ 5:28, 29

6. ኢየሱስ ከሞተ በኋላ አምላክ መንፈሳዊ ፍጡር አድርጎ አስነሳው፤ ወደ ሰማይም ተመለሰ። (1 ጴጥሮስ 3:18) ከዚያ ወዲህ አምላክ ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። በቅርቡ ኢየሱስ ከዚህች ምድር ላይ ክፋትንና መከራን ፈጽሞ ያስወግዳል።—መዝሙር 37:9-11፤ ምሳሌ 2:21, 22

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የኢየሱስ አገልግሎት ማስተማርን፣ ተአምራት መፈጸምንና ሕይወቱን ለእኛ አሳልፎ መስጠትን ያካትት ነበር