በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች አደረጃጀት

የይሖዋ ምሥክሮች አደረጃጀት

ትምህርት 14

የይሖዋ ምሥክሮች አደረጃጀት

የይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ እንቅስቃሴያቸውን የጀመሩት መቼ ነው? (1)

የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች የሚመሩት እንዴት ነው? (2)

ለሥራቸው የሚያስፈልጉ ወጪዎች የሚሸፈኑት እንዴት ነው? (3)

በእያንዳንዱ ጉባኤ ሥራውን በግንባር ቀደምትነት የሚመሩት እነማን ናቸው? (4)

በየዓመቱ የትኞቹ ትላልቅ ስብሰባዎች ይደረጋሉ? (5)

በዋናው መሥሪያ ቤትና በቅርንጫፍ ቢሮዎች ምን ዓይነት ሥራዎች ይከናወናሉ? (6)

1. የይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ እንቅስቃሴያቸውን የጀመሩት በ1870ዎቹ ዓመታት ነው። በመጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ ነበር። በ1931 ግን የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ስም ተቀበሉ። (ኢሳይያስ 43:10) ድርጅቱ በጣም አነስተኛ ከሆነ ጅምር ተነስቶ ምስራቹን ከ230 በሚበልጡ አገሮች በትጋት የሚያውጁ በሚልዮን የሚቆጠሩ ምሥክሮችን ያቀፈ ሆኗል።

2. አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በየሳምንቱ ሦስት ጊዜ ይሰበሰባሉ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ እንድትገኝ ተጋብዘሃል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ትምህርቶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ስብሰባዎቹ የሚከፈቱትና የሚዘጉት በጸሎት ነው። በተጨማሪም በአብዛኞቹ ስብሰባዎች ላይ ‘መንፈሳዊ መዝሙሮች’ ከልብ በመነጨ ስሜት ይዘመራሉ። (ኤፌሶን 5:18, 19) የመግቢያ ዋጋ የማይከፈል ሲሆን ሙዳየ ምጽዋትም አይዞርም።​—ማቴዎስ 10:8

3. አብዛኞቹ ጉባኤዎች ስብሰባዎቻቸውን የሚያደርጉት በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ነው። የመንግሥት አዳራሾች የይሖዋ ምሥክሮች በሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚሠሩ ቀለል ያሉ ሕንጻዎች ናቸው። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ምንም ዓይነት ምስል፣ ሥነ ስቅለት ወይም ሌላ ተመሳሳይ ነገር አይታይም። ለአዳራሹ የሚያስፈልጉ ወጪዎች የሚሸፈኑት በፈቃደኝነት በሚሰጡ መዋጮዎች ነው። መዋጮ ማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ የመዋጮ ሣጥን ይቀመጣል።​—2 ቆሮንቶስ 9:7

4. በእያንዳንዱ ጉባኤ ሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች ይኖራሉ። ሽማግሌዎች ጉባኤውን በማስተማር ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይሳተፋሉ። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-7፤ 5:17) በዚህ ሥራቸውም የጉባኤ አገልጋዮችን እርዳታ ያገኛሉ። (1 ጢሞቴዎስ 3:8-10, 12, 13) እነዚህ ሰዎች ከቀሩት የጉባኤ አባላት በማዕረግ ወይም በክብር የሚበልጡ አይደሉም። (2 ቆሮንቶስ 1:24) የተለየ የማዕረግ ስም የላቸውም። (ማቴዎስ 23:8-10) አለባበሳቸውም ቢሆን ከሌሎች የተለየ አይደለም። ለሚያከናውኑት ሥራ የሚከፈላቸው ደመወዝ የለም። ሽማግሌዎች በፈቃደኝነት የጉባኤውን መንፈሳዊ ደህንነት ይከታተላሉ። ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ ማጽናኛና አመራር ለመስጠት ይችላሉ።​—ያዕቆብ 5:14-16፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3

5. በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ ትላልቅ ስብሰባዎች ያደርጋሉ። በእነዚህ ጊዜያት በርካታ ጉባኤዎች አንድ ላይ ተሰብስበው ልዩ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም ይከታተላሉ። የአዳዲስ ደቀ መዛሙርት ጥምቀት በእያንዳንዱ የትልቅ ስብሰባ ፕሮግራም ላይ ከሚከናወኑ ድርጊቶች አንዱ ነው።​—ማቴዎስ 3:13-17፤ 28:19, 20

6. የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኘው በኒው ዮርክ ነው። በዚህ ዋና መሥሪያ ቤት የምድር አቀፉን ጉባኤ በበላይነት የሚመለከቱ ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች ቡድን ይገኛል። ይህ ቡድን የአስተዳደር አካል ይባላል። በተጨማሪም በመላው ዓለም ከ100 የሚበልጡ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ይገኛሉ። በእነዚህ ቢሮዎች ፈቃደኛ የሆኑ ነጻ ሠራተኞች የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን በማተምና ወደ ተለያዩ ጉባኤዎች በመላክ ሥራ ይካፈላሉ። በተጨማሪም የስብከቱን ሥራ ለማደራጀት የሚያስፈልግ አመራር ይሰጣል። ለምን በአቅራቢያህ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ ለመጎብኘት እቅድ አታወጣም?