በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዲያብሎስ ማን ነው?

ዲያብሎስ ማን ነው?

ትምህርት 4

ዲያብሎስ ማን ነው?

ሰይጣን ዲያብሎስ ከየት መጣ? (1, 2)

ሰይጣን ሰዎችን የሚያስተው እንዴት ነው? (3-7)

ዲያብሎስን መቃወም የሚኖርብህ ለምንድን ነው? (7)

1. “ዲያብሎስ” የሚለው ቃል ትርጉሙ ስለ ሌላ ሰው ሆን ብሎ በተንኮል ውሸት የሚናገር ማለት ነው። “ሰይጣን” ማለት ደግሞ ጠላት ወይም ተቃዋሚ ማለት ነው። እነዚህ ለአምላክ ዋነኛ ጠላት የተሰጡ ስሞች ናቸው። ሰይጣን በመጀመሪያ ከአምላክ ጋር በሰማይ የሚኖር ፍጹም መልአክ ነበር። ቆየት ብሎ ግን ራሱን ከመጠን በላይ ከፍ አድርጎ በመመልከቱ ለአምላክ ብቻ መሰጠት የሚገባውን አምልኮ ለራሱ ለማድረግ ፈለገ።—ማቴዎስ 4:8-10

2. ሰይጣን የተባለው ይህ መልአክ በእባብ አማካኝነት ሔዋንን አነጋገራት። ለእርስዋም ሐሰት የሆነ ነገር በመናገር በአምላክ ላይ እንድታምፅ አደረገ። ሰይጣን በዚህ ድርጊቱ የአምላክን “ልዕልና” ወይም የበላይነት ሥልጣን ተጋፋ። አምላክ ተገዢዎቹን የሚያስተዳድረው በትክክልና እነርሱን በሚጠቅማቸው መንገድ መሆኑ አጠያያቂ እንዲሆን አደረገ። በተጨማሪም ሰይጣን ለአምላክ እስከ መጨረሻ ታማኝ የሚሆን ሰው መኖሩ አጠራጣሪ እንዲሆን አደረገ። ይህን በማድረጉም ራሱን የአምላክ ጠላት አደረገ። ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ የተጠራውም በዚህ ምክንያት ነው።—ዘፍጥረት 3:1-5፤ ኢዮብ 1:8-11፤ ራእይ 12:9

3. ሰይጣን ሰዎችን ለማሳትና እርሱን እንዲያመልኩ ለማድረግ ይሞክራል። (2 ቆሮንቶስ 11:3, 14) ሰዎችን ከሚያስትባቸው መንገዶች አንዱ የሐሰት ሃይማኖት ነው። አንድ ሃይማኖት ስለ አምላክ ሐሰት የሆነ ነገር የሚያስተምር ከሆነ ለሰይጣን ዓላማ የቆመ ነው ማለት ነው። (ዮሐንስ 8:44) የሐሰት ሃይማኖት አባላት የሆኑ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ እያመለኩ እንዳሉ አድርገው በቅንነት ሊያስቡ ይችላሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የሚያገለግሉት ሰይጣንን ነው። “የዚህ ዓለም አምላክ” ሰይጣን ነው።—2 ቆሮንቶስ 4:4

4. ሰይጣን ሰዎችን በቁጥጥሩ ሥር የሚያደርግበት ሌላው መንገድ መናፍስታዊ እምነት ነው። እምነት ያላቸው ሰዎች መናፍስትን እንዲጠብቋቸው ወይም ሌሎችን እንዲጎዱ ወይም ወደፊት የሚሆነውን ነገር እንዲነግሯቸው አለበለዚያም ተአምር እንዲፈጽሙላቸው ሊጠይቁ ይችላሉ። ከእነዚህ ድርጊቶች በስተጀርባ ያለው ክፉ ኃይል ሰይጣን ነው። አምላክን ለማስደሰት ከፈለግን ከመናፍስታዊ እምነት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሊኖረን አይገባም።—ዘዳግም 18:10-12፤ ሥራ 19:18, 19

5. በተጨማሪም ሰይጣን ሰዎች በዘራቸው እንዲኮሩ እንዲሁም ፖለቲካዊ ድርጅቶችን እንዲያመልኩ በማድረግ ያስታል። የራሳቸው ዘር ወይም ብሔር ከሌሎች እንደሚበልጥ የሚሰማቸው ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ይህ ትክክል አይደለም። (ሥራ 10:34, 35) ሌሎች ሰዎች ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶች የሰው ልጆችን ችግሮች ይፈታሉ ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። እንዲህ ማድረጋቸውም የአምላክን መንግሥት አለመቀበላቸውን ያሳያል። ለችግሮቻችን መፍትሔው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው።—ዳንኤል 2:44

6. ሰይጣን ሰዎችን የሚያስትበት ሌላው ዘዴ ለኃጢአት ፍላጎት እንዲሸነፉ ማድረግ ነው። ይሖዋ የኃጢአት ድርጊቶች እንደሚጎዱን ስለሚያውቅ ከኃጢአት እንድንርቅ ይነግረናል። (ገላትያ 6:7, 8) በእነዚህ ድርጊቶች እንድትተባበራቸው የሚፈልጉ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህን ነገሮች እንድታደርግ የሚፈልገው ሰይጣን መሆኑን መዘንጋት የለብህም።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ 15:33

7. ሰይጣን ይሖዋን እንድትተው ለማድረግ በስደት ወይም በተቃውሞ ይጠቀም ይሆናል። በጣም ከምትወዳቸው ሰዎች አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በመጀመርህ በጣም ይቆጡ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ይሳለቁብህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሕይወትህን ያገኘኸው ከማን ነው? ሰይጣን በፍርሃት ተሸንፈህ ስለ ይሖዋ መማርህን እንድታቆም ይፈልጋል። ሰይጣን እንዲያሸንፍህ ልትፈቅድለት አይገባም! (ማቴዎስ 10:34-39፤ 1 ጴጥሮስ 5:8, 9) ዲያብሎስን በመቃወም ይሖዋን ደስ ልታሰኝና የይሖዋን ልዕልና እንደምትደግፍ ልታሳይ ትችላለህ።—ምሳሌ 27:11

[በገጽ 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሐሰት ሃይማኖት፣ መናፍስታዊ እምነትና ብሔራዊ ስሜት ሰዎችን ያስታሉ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ ይሖዋ መማርህን በመቀጠል ሰይጣንን ተቃወም