በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 63

ኢየሱስ ማሰናከልንና ኃጢአትን በተመለከተ ምክር ሰጠ

ኢየሱስ ማሰናከልንና ኃጢአትን በተመለከተ ምክር ሰጠ

ማቴዎስ 18:6-20 ማርቆስ 9:38-50 ሉቃስ 9:49, 50

  • ማሰናከልን በተመለከተ የተሰጠ ምክር

  • አንድ ወንድም ኃጢአት ቢፈጽም

ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ሊኖራቸው ስለሚገባው አመለካከት በምሳሌ አስተምሮ መጨረሱ ነው። ልክ እንደ ልጆች ተከታዮቹም ትሑቶችና ሥልጣን የማይፈልጉ መሆን አለባቸው። ደቀ መዛሙርቱ ‘እንደዚህ ያሉትን ትናንሽ ልጆች በኢየሱስ ስም በመቀበል እሱን እንደሚቀበሉ’ ማሳየት ይኖርባቸዋል።—ማቴዎስ 18:5

ከዚህ ትንሽ ቀደም ብሎ ሐዋርያቱ፣ ታላቅ የሆነው ማን እንደሆነ ሲከራከሩ ስለነበር ይህን ትምህርት እንደ እርማት ሊመለከቱት ይችላሉ። አሁን ደግሞ ሐዋርያው ዮሐንስ በዚያ ወቅት ስላየው ሌላ ነገር እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “መምህር፣ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያስወጣ አየን፤ ይሁንና ከእኛ ጋር ሆኖ አንተን ስለማይከተል ልንከለክለው ሞከርን።”—ሉቃስ 9:49

ዮሐንስ፣ የመፈወስ ወይም አጋንንትን የማስወጣት ሥልጣን ያላቸው ሐዋርያት ብቻ እንደሆኑ ተሰምቶት ይሆን? ከሆነ ይህ አይሁዳዊ ሰው፣ ክፉ መናፍስትን ሊያስወጣ የቻለው እንዴት ነው? ዮሐንስ፣ ሰውየው ከኢየሱስና ከሐዋርያቱ ጋር ስላልሆነ ተአምራት ሊፈጽም እንደማይገባው የተሰማው ይመስላል።

በመሆኑም ኢየሱስ የሰጠው የሚከተለው መልስ ዮሐንስን አስገርሞት መሆን አለበት፦ “በስሜ ተአምር ሠርቶ ወዲያውኑ ስለ እኔ ክፉ ነገር ሊናገር የሚችል ስለሌለ አትከልክሉት። እኛን የማይቃወም ሁሉ ከእኛ ጋር ነውና። ደግሞም የክርስቶስ በመሆናችሁ ምክንያት አንድ ጽዋ የሚጠጣ ውኃ የሚሰጣችሁ ሁሉ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ በምንም መንገድ ብድራቱን አያጣም።”—ማርቆስ 9:39-41

ይህ ሰው ከኢየሱስ ጎን ለመቆም በዚህ ወቅት የግድ ከክርስቶስ ጋር መሆን አያስፈልገውም። የክርስቲያን ጉባኤ ገና አልተቋቋመም፤ ስለዚህ ግለሰቡ ከኢየሱስ ጋር አለመጓዙ የእሱ ተቃዋሚ አያስብለውም፤ ወይም የሐሰት ሃይማኖት እያስፋፋ ነው ማለት አይደለም። ሰውየው በኢየሱስ ስም ላይ እምነት እንዳለው ግልጽ ነው፤ ደግሞም ኢየሱስ ከተናገረው መረዳት እንደሚቻለው ብድራቱን አያጣም።

በሌላ በኩል ግን ሰውየው ሐዋርያቱ በተናገሩትና ባደረጉት ነገር ቢሰናከል ይህ ከባድ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። ኢየሱስ “ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል” አለ። (ማርቆስ 9:42) ከዚያም ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ የእጅን፣ የእግርን ወይም የዓይንን ያህል ውድ የሆነ ነገር እንኳ የሚያሰናክላቸው ከሆነ ሊያስወግዱት እንደሚገባ ተናገረ። እንዲህ ያለውን ውድ ነገር የሙጥኝ ብሎ ወደ ገሃነም (የሂኖም ሸለቆ) ከመግባት ይልቅ ይህን ነገር አጥቶ ወደ አምላክ መንግሥት መግባት ይሻላል። ሐዋርያት በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ያለውንና ቆሻሻ የሚቃጠልበትን ይህን ሸለቆ አይተው እንደሚያውቁ ግልጽ ነው፤ በመሆኑም ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ስለ ዘላለማዊ ጥፋት መሆኑ ይገባቸዋል።

ኢየሱስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያም ሰጥቷል፦ “በሰማይ ያሉት መልአኮቻቸው በሰማይ ባለው አባቴ ፊት ዘወትር ስለሚቀርቡ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ።” “ትናንሾቹ” የተባሉት በአባቱ ዘንድ ምን ያህል ውድ ናቸው? ኢየሱስ 100 በጎች ስላሉትና አንዷ ስለጠፋችበት ሰው ተናገረ። ሰውየው 99ኙን ትቶ የጠፋችውን ይፈልጋል፤ ሲያገኛትም ከ99ኙ ይልቅ በእሷ ይበልጥ ይደሰታል። ኢየሱስ በመቀጠል “በሰማይ ያለው አባቴ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱም እንኳ እንዲጠፋ አይፈልግም” አለ።—ማቴዎስ 18:10, 14

ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ ያደረጉትን ክርክር አስታውሶ ሳይሆን አይቀርም “በሕይወታችሁ ውስጥ ጨው ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም ሰላም ይኑራችሁ” በማለት አሳሰባቸው። (ማርቆስ 9:50) ጨው ምግብን ይበልጥ ያጣፍጣል። ምሳሌያዊ ጨውም አንድ ሰው የሚናገረው ነገር በቀላሉ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደርጋል፤ ይህም ክርክር የማያስገኘው ነገር ይኸውም ሰላም እንዲሰፍን ይረዳል።—ቆላስይስ 4:6

ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ከባድ አለመግባባት ይፈጠራል፤ ኢየሱስ ይህ ሁኔታ ሲፈጠር ምን ማድረግ እንደሚገባ ተናግሯል። “ወንድምህ ቢበድልህ አንተና እሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ጥፋቱን በግልጽ ንገረው። ከሰማህ ወንድምህን ታተርፋለህ” ብሏል። የማይሰማ ከሆነስ? ኢየሱስ “ማንኛውም ጉዳይ ሁለት ወይም ሦስት ምሥክሮች በሚሰጡት የምሥክርነት ቃል ስለሚጸና አንድ ወይም ሁለት ሰው ይዘህ ሂድ” የሚል ምክር ሰጥቷል። ሁኔታው በዚህም ካልተፈታ ግን ጉዳዩን ኃላፊነት ያላቸው ሽማግሌዎች ውሳኔ እንዲሰጡበት ግለሰቦቹ “ለጉባኤ” ሊያቀርቡት ይገባል። ይሁንና ኃጢአት የፈጸመው ሰው እነሱንም ባይሰማስ? ኢየሱስ “እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ [አይሁዳውያን የማይቀርቧቸው ሰዎች] አድርገህ ቁጠረው” ብሏል።—ማቴዎስ 18:15-17

የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን መመሪያዎች በጥብቅ መከተል ይኖርባቸዋል። ኃጢአት የፈጸመ አንድ ሰው ጥፋተኛ እንደሆነና ተግሣጽ እንደሚያስፈልገው ከወሰኑ ሽማግሌዎቹ የሚሰጡት ፍርድ “ቀድሞውኑ በሰማያት የታሰረ” ነው። ግለሰቡን ንጹሕ ሆኖ ካገኙት ደግሞ ጉዳዩ “ቀድሞውኑ በሰማያት የተፈታ” ነው። እነዚህ መመሪያዎች የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ ጠቃሚ ይሆናሉ። እንዲህ ዓይነት የፍርድ ጉዳዮች በሚታዩበት ጊዜ ኢየሱስ “ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እገኛለሁ” ብሏል።—ማቴዎስ 18:18-20