በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 32

በሰንበት የተፈቀደው ምንድን ነው?

በሰንበት የተፈቀደው ምንድን ነው?

ማቴዎስ 12:9-14 ማርቆስ 3:1-6 ሉቃስ 6:6-11

  • በሰንበት የአንድን ሰው እጅ ፈወሰ

በሌላ ሰንበት ኢየሱስ ወደ አንድ ምኩራብ ሄደ፤ ቦታው በገሊላ ሳይሆን አይቀርም። በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ተመለከተ። (ሉቃስ 6:6) ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ኢየሱስን በትኩረት እየተከታተሉት ነው። ለምን? “በሰንበት መፈወስ በሕግ ተፈቅዷል?” በማለት ያቀረቡት ጥያቄ ዓላማቸው ምን እንደሆነ በግልጽ ያሳያል።—ማቴዎስ 12:10

የሃይማኖት መሪዎቹ በሰንበት ሕክምና መስጠት የሚቻለው ለሕይወት የሚያሰጋ ሁኔታ ከተፈጠረ ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ወለም ቢለው አጥንቱን ቦታው ማስገባት ወይም በጨርቅ መጠቅለል የተከለከለ ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ሁኔታዎች ለሕይወት የሚያሰጉ አይደሉም። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ለኢየሱስ ይህን ጥያቄ ያቀረቡለት የዚህ ሰው ሥቃይ ስላስጨነቃቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስን የሚከስሱበት ሰበብ ለማግኘት ስለፈለጉ ነው።

ኢየሱስ ግን አስተሳሰባቸው ጠማማ እንደሆነ አውቋል። ‘በሰንበት መሥራትን የሚከለክለው ሕግ ተጣሰ’ የሚባለው መቼ እንደሆነ ያላቸው አመለካከት ከቅዱስ ጽሑፉ የራቀና ሚዛናዊነት የጎደለው እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (ዘፀአት 20:8-10) መልካም ሥራ በመሥራቱ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ የተሳሳተ ትችት ተሰንዝሮበታል። ስለዚህ ኢየሱስ እጁ የሰለለበትን ሰው “ተነሳና ወደ መሃል ና” ብሎ በመጋበዝ በጉዳዩ ላይ ፊት ለፊት ለመነጋገር የሚያስችል መድረክ አመቻቸ።—ማርቆስ 3:3

ኢየሱስ ወደ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ዞር ብሎ “ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው ሰው ቢኖርና በሰንበት ቀን ጉድጓድ ውስጥ ቢገባበት በጉን ጎትቶ የማያወጣው ይኖራል?” ብሎ ጠየቃቸው። (ማቴዎስ 12:11) በግ በገንዘብ የሚገኝ ንብረት በመሆኑ እስከሚቀጥለው ቀን ድረስ እዚያው ጉድጓድ ውስጥ አይተዉትም፤ ምክንያቱም እዚያ እያለ ቢሞት ኪሳራ ይሆንባቸዋል። ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ የቤት እንስሳቱን ይንከባከባል” ይላል።—ምሳሌ 12:10

ቀጥሎም ኢየሱስ የሚከተለውን ምክንያታዊነት የተንጸባረቀበት ንጽጽር ተጠቀመ፦ “ታዲያ ሰው ከበግ እጅግ አይበልጥም? ስለዚህ በሰንበት መልካም ነገር ማድረግ ተፈቅዷል።” (ማቴዎስ 12:12) ከዚህ አንጻር ኢየሱስ ሰውየውን መፈወሱ የሰንበትን ሕግ መጣስ አይሆንበትም። የሃይማኖት መሪዎቹ ይህን ምክንያታዊነትና ርኅራኄ የተሞላበት አነጋገር ማስተባበል ስላልቻሉ ዝም አሉ።

ኢየሱስ በተዛባ አስተሳሰባቸው በማዘን በዙሪያው ያሉትን በብስጭት ተመለከተ። ከዚያም ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። (ማቴዎስ 12:13) ሰውየው የሰለለ እጁን ሲዘረጋ ተፈወሰ። ግለሰቡ በዚህ እንደሚደሰት ጥርጥር የለውም፤ ይሁንና ኢየሱስን ለማጥመድ የሞከሩት ሰዎች ምን ተሰማቸው?

ፈሪሳውያን የሰውየው እጅ በመዳኑ መደሰት ሲገባቸው “ወዲያው ከሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች ጋር በመሰብሰብ [ኢየሱስን] እንዴት እንደሚገድሉት መመካከር ጀመሩ።” (ማርቆስ 3:6) ይህ የፖለቲካ ቡድን፣ ሰዱቃውያን የሚባሉትን የሃይማኖት ሰዎች ያቀፈ ሳይሆን አይቀርም። እንደ ወትሮው ቢሆን ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን እርስ በርስ አይስማሙም፤ አሁን ግን ኢየሱስን በመቃወም ግንባር ፈጠሩ።