በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 60

በተአምራዊ ሁኔታ ተለወጠ—ክርስቶስ በክብሩ ታየ

በተአምራዊ ሁኔታ ተለወጠ—ክርስቶስ በክብሩ ታየ

ማቴዎስ 16:28–17:13 ማርቆስ 9:1-13 ሉቃስ 9:27-36

  • ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ሲለወጥ ማየት

  • ሐዋርያት የአምላክን ድምፅ ሰሙ

ኢየሱስ ከሄርሞን ተራራ 25 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኘው በቂሳርያ ፊልጵስዩስ ክልል ሕዝቡን እያስተማረ ሳለ የሚከተለውን አስገራሚ ሐሳብ ለሐዋርያቱ ተናገረ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ እዚህ ከቆሙት መካከል አንዳንዶች የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ፈጽሞ ሞትን አይቀምሱም።”—ማቴዎስ 16:28

ደቀ መዛሙርቱ፣ ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደሆነ ግራ ሳይገባቸው አልቀረም። ኢየሱስ ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ አንድ ረጅም ተራራ ወጣ። ሦስቱ ሐዋርያት እንቅልፍ እንደተጫጫናቸው ስለተገለጸ ይህ የሆነው ምሽት ላይ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ እየጸለየ ሳለ በፊታቸው ተለወጠ። ሐዋርያቱ ፊቱ እንደ ፀሐይ ሲያበራና ልብሱም እንደ ብርሃን ሲያንጸባርቅ ወይም ነጭ ሲሆን ተመለከቱ።

ከዚያም ሁለት ሰዎች ተገለጡ፤ እነዚህ ሰዎች “ሙሴና ኤልያስ” እንደሆኑ ተገልጿል። እነሱም “በኢየሩሳሌም ስለሚፈጸመውና ከዚህ ዓለም ተለይቶ ስለሚሄድበት ሁኔታ” ከኢየሱስ ጋር ይነጋገሩ ጀመር። (ሉቃስ 9:30, 31) ‘ከዚህ ዓለም ተለይቶ መሄድ’ የሚለው አገላለጽ የኢየሱስን ሞትና ከዚያ በኋላ የሚከናወነውን ትንሣኤውን እንደሚያመለክት መረዳት ይቻላል፤ ኢየሱስ ከዚህ ትንሽ ቀደም ብሎ ስለዚህ ጉዳይ ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 16:21) አሁን የሚያደርጉት ውይይት፣ ጴጥሮስ ከተመኘው በተቃራኒ ኢየሱስ ተዋርዶ መገደሉ የማይቀር ነገር እንደሆነ ያረጋግጣል።

በዚህ ጊዜ ሦስቱ ሐዋርያት ሙሉ በሙሉ ነቅተው የሚሆነውን ነገር በአግራሞት መመልከትና ማዳመጥ ጀመሩ። የሚያዩት ነገር ራእይ ቢሆንም በእውን እየተፈጸመ ያለ ስለሚመስል ጴጥሮስ እንዲህ አለ፦ “ረቢ፣ እዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው። ስለዚህ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ድንኳኖች እንትከል።” (ማርቆስ 9:5) ጴጥሮስ ድንኳን ለመትከል ያሰበው ራእዩን ለማራዘም ፈልጎ ይሆን?

ጴጥሮስ እየተናገረ ሳለ “ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ‘በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት’ የሚል ድምፅ ተሰማ።” ሐዋርያቱ የአምላክን ድምፅ ሲሰሙ በፍርሃት ተውጠው በግንባራቸው ተደፉ፤ ሆኖም ኢየሱስ “ተነሱ። አትፍሩ” አላቸው። (ማቴዎስ 17:5-7) ሦስቱ ሐዋርያት ቀና ብለው ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ሌላ ማንንም አላዩም። ራእዩ አብቅቷል። ጎህ ሲቀድና ከተራራው ሲወርዱ ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሳ ድረስ ራእዩን ለማንም እንዳትናገሩ” ሲል አዘዛቸው።—ማቴዎስ 17:9

ኤልያስ በራእዩ ላይ መታየቱ ጥያቄ ያስነሳል። በመሆኑም ሐዋርያቱ “ጸሐፍት ኤልያስ በመጀመሪያ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም “ኤልያስ መምጣቱን መጥቷል፤ እነሱ ግን . . . አላወቁትም” ብሎ መለሰላቸው። (ማቴዎስ 17:10-12) ኢየሱስ፣ የኤልያስን ዓይነት ሚና ስለተጫወተው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መናገሩ ነው። ኤልያስ ለኤልሳዕ መንገዱን እንዳዘጋጀ ሁሉ ዮሐንስም ለክርስቶስ መንገዱን አዘጋጅቷል።

ይህ ራእይ ኢየሱስንም ሆነ ሐዋርያቱን ምንኛ የሚያበረታታ ነው! ራእዩ ክርስቶስ በመንግሥቱ በክብር ሲመጣ የሚኖረውን ሁኔታ የሚያሳይ ናሙና ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት ደቀ መዛሙርቱ “የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ” ተመልክተዋል ማለት ይቻላል። (ማቴዎስ 16:28) በተራራው ላይ እያሉ ‘ግርማውን በገዛ ዓይናቸው አይተዋል።’ ኢየሱስ፣ አምላክ የመረጠው ንጉሥ እንደሚሆን የሚያረጋግጥ ምልክት እንዲያሳያቸው ፈሪሳውያን ቢጠይቁትም እንዲህ ዓይነት ምልክት አልሰጣቸውም። በሌላ በኩል ግን የቅርብ ደቀ መዛሙርቱ፣ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ሲለወጥ አይተዋል፤ ይህ ራእይ ስለ መንግሥቱ የተነገሩ ትንቢቶች እንደሚፈጸሙ ያረጋግጣል። በመሆኑም ጴጥሮስ “ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል” በማለት ከጊዜ በኋላ ጽፏል።—2 ጴጥሮስ 1:16-19