ምዕራፍ 49
በገሊላ መስበክና ሐዋርያቱን ማሠልጠን
ማቴዎስ 9:35–10:15 ማርቆስ 6:6-11 ሉቃስ 9:1-5
-
ኢየሱስ እንደገና በገሊላ ተዘዋወረ
-
ሐዋርያቱን እንዲሰብኩ ላካቸው
ኢየሱስ ወደ ሁለት ዓመት ያህል በስፋት ሲሰብክ ቆይቷል። ታዲያ አሁን አገልግሎቱን ጋብ አድርጎ ዘና የሚልበት ጊዜ ይሆን? ኢየሱስ እንዲህ ከማድረግ ይልቅ የስብከት ሥራውን በማስፋት ገሊላ ውስጥ “በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፣ የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እየፈወሰ በየከተማውና በየመንደሩ ይዞር ጀመር።” (ማቴዎስ 9:35) በዚያ የተመለከተው ነገርም የስብከት ሥራውን ይበልጥ ማስፋት እንዳለበት እንዲያምን አድርጎታል። ይሁንና ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?
ኢየሱስ በሄደበት ሁሉ የሚያገኛቸው ሰዎች መንፈሳዊ ፈውስና መጽናኛ እንደሚያስፈልጋቸው አስተዋለ። እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈዋል፤ እንዲሁም ተጥለዋል። ለእነዚህ ሰዎች እጅግ ስላዘነላቸው ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “አዎ፣ አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።”—ማቴዎስ 9:37, 38
ኢየሱስ ሰዎቹን ለመርዳት ምን እንደሚያስፈልግ ያውቃል። በመሆኑም 12 ሐዋርያቱን ጠርቶ ጥንድ ጥንድ እያደረገ በማጣመር ስድስት የሰባኪዎች ቡድን አደራጀ። ከዚያም የሚከተለውን ግልጽ መመሪያ ሰጣቸው፦ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ማንኛውም የሳምራውያን ከተማም አትግቡ፤ ከዚህ ይልቅ ከእስራኤል ቤት ወደጠፉት በጎች ብቻ ሂዱ። በምትሄዱበት ጊዜም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል’ ብላችሁ ስበኩ።”—ማቴዎስ 10:5-7
ሐዋርያቱ የሚሰብኩት ኢየሱስ ባስተማራቸው የጸሎት ናሙና ላይ ስለተጠቀሰው መንግሥት ነው። “መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል” መባሉ አምላክ የሾመው ንጉሥ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው መሆኑን ይጠቁማል። ይሁንና ደቀ መዛሙርቱ የዚህ መንግሥት እውነተኛ ወኪሎች መሆናቸውን የሚያረጋግጠው ምንድን ነው? ኢየሱስ የታመሙ ሰዎችን እንዲፈውሱ ሌላው ቀርቶ የሞቱ ሰዎችንም እንኳ እንዲያስነሱ ሥልጣን ሰጣቸው፤ ይህንንም በነፃ ማከናወን እንዳለባቸው ነገራቸው። ታዲያ ሐዋርያቱ በየዕለቱ የሚያስፈልጓቸውን እንደ ምግብ ያሉ ነገሮች ከየት ሊያገኙ ነው?
ኢየሱስ ለስብከት ጉዟቸው ቁሳዊ ነገሮችን ማዘጋጀት እንደማያስፈልጋቸው ነገራቸው። ወርቅ ወይም ብር አሊያም መዳብ በቦርሳቸው መያዝ አያስፈልጋቸውም። ሌላው ቀርቶ ለጉዞ የምግብ ከረጢት ወይም ሁለት ልብስ አሊያም ትርፍ ጫማ መያዝ የለባቸውም። ለምን? ኢየሱስ “ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 10:10) ደቀ መዛሙርቱ የሚሰብኩትን መልእክት የሚቀበሉ ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ያሟሉላቸዋል። ኢየሱስ “ወደ አንድ ቤት ስትገቡ አካባቢውን ለቃችሁ እስክትሄዱ ድረስ እዚያው ቆዩ” ብሏል።—ማርቆስ 6:10
ኢየሱስ፣ በየቤቱ እየሄዱ ለሚያናግሯቸው ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዴት መስበክ እንደሚችሉም መመሪያ ሰጣቸው፤ እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ቤትም ስትገቡ ቤተሰቡን ሰላም በሉ። ቤቱ የሚገባው ሆኖ ከተገኘ ሰላማችሁ ይድረሰው፤ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስ። የሚቀበላችሁ ወይም ቃላችሁን የሚሰማ ሰው ካጣችሁ ከዚያ ቤት ወይም ከተማ ስትወጡ፣ የእግራችሁን አቧራ አራግፉ።”—ማቴዎስ 10:12-14
የአንድ ከተማ ወይም መንደር ነዋሪዎች በሙሉ የደቀ መዛሙርቱን መልእክት ላይቀበሉ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ምላሽ የሰጠች ከተማ ነዋሪዎች ምን ይጠብቃቸዋል? ኢየሱስ ከባድ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ሲገልጽ “እውነት እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ ይቀልላቸዋል” አለ።—ማቴዎስ 10:15