በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 61

ኢየሱስ ጋኔን የያዘውን ልጅ ፈወሰ

ኢየሱስ ጋኔን የያዘውን ልጅ ፈወሰ

ማቴዎስ 17:14-20 ማርቆስ 9:14-29 ሉቃስ 9:37-43

  • ጋኔን የያዘውን ልጅ ለመፈወስ ጠንካራ እምነት አስፈለገ

ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ከተራራው ሲወርዱ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ አገኙ። የሆነ ችግር ያለ ይመስላል። ጸሐፍት ደቀ መዛሙርቱን ከበው እየተከራከሯቸው ነው። ሕዝቡ ኢየሱስን ሲያዩት በጣም ተደሰቱ፤ ከዚያም ሰላም ሊሉት ወደ እሱ ሮጡ። ኢየሱስም “ከእነሱ ጋር የምትከራከሩት ስለ ምን ጉዳይ ነው?” ሲል ጠየቀ።—ማርቆስ 9:16

ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው በኢየሱስ ፊት ተንበርክኮ እንዲህ አለው፦ “መምህር፣ ልጄ ዱዳ የሚያደርግ መንፈስ ስላደረበት ወደ አንተ አመጣሁት። በያዘው ስፍራ ሁሉ መሬት ላይ ይጥለዋል፤ ከዚያም አፉ አረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱን ያፋጫል እንዲሁም ይዝለፈለፋል። ደቀ መዛሙርትህ እንዲያስወጡት ጠየቅኳቸው፤ እነሱ ግን ሊያስወጡት አልቻሉም።”—ማርቆስ 9:17, 18

ደቀ መዛሙርቱ ልጁን መፈወስ ባለመቻላቸው ጸሐፍት ያቃልሏቸው እንዲያውም በጥረታቸው ያሾፉ የነበረ ይመስላል። በመሆኑም ኢየሱስ ለተጨነቀው አባት መልስ ከመስጠት ይልቅ ሕዝቡን “እምነት የለሽና ጠማማ ትውልድ ሆይ፣ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር መቆየትና እናንተን መታገሥ ሊኖርብኝ ነው?” አላቸው። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ጠንከር ያለ ሐሳብ የሰነዘረው እሱ ባልነበረበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱን ሲያስቸግሯቸው ለቆዩት ጸሐፍት እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ቀጥሎም ኢየሱስ በጭንቀት ወደተዋጠው አባት ዘወር ብሎ “እስቲ ልጅህን ወደዚህ አምጣው” አለ።—ሉቃስ 9:41

ልጁ ወደ ኢየሱስ ሲቀርብ በእሱ ላይ ያደረው ጋኔን መሬት ላይ ጥሎ አንዘፈዘፈው። ልጁም አፉ አረፋ እየደፈቀ ይንከባለል ጀመር። ኢየሱስ አባትየውን “እንዲህ ማድረግ ከጀመረው ምን ያህል ጊዜ ሆነው?” ሲል ጠየቀው። አባትየውም “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳት ውስጥና ውኃ ውስጥ ይጥለዋል” በማለት መለሰ። ከዚያም “ማድረግ የምትችለው ነገር ካለ እዘንልንና እርዳን” ሲል ኢየሱስን ተማጸነው።—ማርቆስ 9:21, 22

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም እንኳ ልጁን ሊረዱት ስላልቻሉ አባትየው ምን እንደሚያደርግ ግራ ገብቶታል። ኢየሱስ የሰውየውን አሳዛኝ ልመና ሲሰማ “‘የምትችለው ነገር ካለ’ አልክ? እምነት ላለው ሰው፣ ሁሉ ነገር ይቻላል” በማለት አበረታታው። ወዲያውም የልጁ አባት “እምነት አለኝ! እምነቴ እንዲጠነክር ደግሞ አንተ እርዳኝ!” በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ።—ማርቆስ 9:23, 24

ኢየሱስ፣ ሕዝቡ ወደ እሱ ግር ብሎ እየሮጠ በመምጣት ላይ መሆኑን አስተዋለ። ሁሉም እያዩ ጋኔኑን “አንተ ዱዳና ደንቆሮ የምታደርግ መንፈስ ከእሱ ውጣ፤ ዳግመኛም ወደ እሱ እንዳትገባ አዝሃለሁ!” ሲል ገሠጸው። ጋኔኑ ሲወጣ ልጁን አስጮኸው፤ እንዲሁም ብዙ ጊዜ አንዘፈዘፈው። ከዚያም ልጁ የሞተ ያህል ሆነ። ብዙ ሰዎች ይህን ሲያዩ “ሞቷል!” አሉ። (ማርቆስ 9:25, 26) ሆኖም ኢየሱስ እጁን ሲይዘው ልጁ ተነሳ፤ “ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰ።” (ማቴዎስ 17:18) ሕዝቡ ኢየሱስ በሚያደርገው ነገር በጣም መደነቃቸው የሚያስገርም አይደለም።

ቀደም ሲል ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን እንዲሰብኩ ሲልካቸው አጋንንት አስወጥተው ነበር። ስለዚህ አሁን ቤት ውስጥ ብቻቸውን ሲሆኑ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ሲሉ ኢየሱስን ጠየቁት። እሱም እምነት ስላነሳቸው እንደሆነ ሲገልጽ “እንዲህ ዓይነቱ በጸሎት ካልሆነ በቀር ሊወጣ አይችልም” አላቸው። (ማርቆስ 9:28, 29) ኃይለኛ የሆነውን ጋኔን ለማስወጣት ጠንካራ እምነት ብቻ ሳይሆን ኃይል የሚሰጠውን የአምላክን እርዳታ ለማግኘት መጸለይም ያስፈልጋል።

ኢየሱስ እንዲህ በማለት ውይይቱን ደመደመ፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት ካላችሁ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም” አላቸው። (ማቴዎስ 17:20) በእርግጥም እምነት ታላቅ ኃይል አለው!

በይሖዋ አገልግሎት የምናደርገውን እድገት የሚገቱ እንቅፋቶችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ልክ እንደ ተራራ ልንገፋቸውና ልናስወግዳቸው የማንችላቸው ሆነው ይታዩን ይሆናል። ሆኖም እምነት ካዳበርን እንደ ተራራ ያሉ እንቅፋቶችንና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መወጣት እንችላለን።