በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 16

ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት አሳየ

ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት አሳየ

ዮሐንስ 2:12-22

  • ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን አጸዳ

በቃና ከተካሄደው ሠርግ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም አቀና። እናቱና ወንድሞቹ ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳም አብረውት ናቸው።

ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም የሄደው ለምንድን ነው? ይህች ከተማ ከናዝሬት ወይም ከቃና ይበልጥ አማካይ ቦታ ላይ የምትገኝ ከመሆኗም ሌላ ሰፊ ሳትሆን አትቀርም። በተጨማሪም ከኢየሱስ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት አብዛኞቹ የሚኖሩት በቅፍርናሆም ወይም በአቅራቢያዋ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ በመኖሪያ አካባቢያቸው እያሉ ሊያሠለጥናቸው ይችላል።

ኢየሱስ በቅፍርናሆም በቆየባቸው ጊዜያትም አስደናቂ ነገሮችን ፈጽሟል። በመሆኑም በዚህች ከተማና በአካባቢዋ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ስላደረጋቸው ነገሮች ሰሙ። ብዙም ሳይቆይ ግን ኢየሱስና የአይሁድን እምነት አጥብቀው የሚከተሉት ወዳጆቹ፣ በ30 ዓ.ም. በሚከበረው የፋሲካ በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ አለባቸው።

ደቀ መዛሙርቱ በኢየሩሳሌም ባለው ቤተ መቅደስ ሳሉ ከዚህ ቀደም አይተው የማያውቁትን አስገራሚ የሆነ የኢየሱስ ባሕርይ ተመለከቱ።

የአምላክ ሕግ በሚያዘው መሠረት እስራኤላውያን በቤተ መቅደሱ የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፤ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚመጡ ሰዎችም በዚያ በሚቆዩበት ጊዜ ምግብ ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም ራቅ ካሉ ቦታዎች ወደ ኢየሩሳሌም የሚመጡ ሰዎች ገንዘብ ይዘው በመሄድ “ከብት፣ በግ፣ ፍየል” እንዲሁም በከተማዋ ሲቆዩ የሚያስፈልጓቸውን ሌሎች ነገሮች እዚያ እንዲገዙ ሕጉ ይፈቅዳል። (ዘዳግም 14:24-26) በኢየሩሳሌም የነበሩ ነጋዴዎች በቤተ መቅደሱ ሰፊ ግቢ ውስጥ እንስሳትንና ወፎችን ይሸጣሉ። አንዳንዶቹ ግን ሕዝቡን ከፍተኛ ዋጋ በማስከፈል ያጭበረብራሉ።

ኢየሱስ በዚህ በጣም በመናደዱ የገንዘብ ለዋጮቹን ሳንቲሞች በተነ፣ ጠረጴዛዎቻቸውን ገለባበጠ እንዲሁም ሰዎቹን አባረራቸው። ከዚያም “እነዚህን ከዚህ አስወጡ! የአባቴን ቤት የንግድ ቤት ማድረጋችሁ ይብቃ!” አላቸው።—ዮሐንስ 2:16

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን ሲመለከቱ “ለቤትህ ያለኝ ቅንዓት ይበላኛል” የሚለውን ስለ አምላክ ልጅ የተነገረ ትንቢት አስታወሱ። አይሁዳውያን ግን “እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ የሚያረጋግጥ ምን ምልክት ታሳየናለህ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን ውስጥ አነሳዋለሁ” ሲል መለሰላቸው።—ዮሐንስ 2:17-19፤ መዝሙር 69:9

አይሁዳውያኑ፣ ኢየሱስ ቃል በቃል ስለ ቤተ መቅደሱ የተናገረ ስለመሰላቸው “ቤተ መቅደሱን ለመገንባት 46 ዓመት ፈጅቷል፤ ታዲያ አንተ በሦስት ቀን ታነሳዋለህ?” አሉት። (ዮሐንስ 2:20) ኢየሱስ ግን ቤተ መቅደስ ሲል ስለ ራሱ ሰውነት መናገሩ ነበር። ከሦስት ዓመት በኋላ ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ቃል አስታወሱ።