በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 15

ኢየሱስ የፈጸመው የመጀመሪያ ተአምር

ኢየሱስ የፈጸመው የመጀመሪያ ተአምር

ዮሐንስ 2:1-12

  • በቃና የተደረገ ሠርግ

  • ኢየሱስ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ለወጠ

ናትናኤል ከኢየሱስ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት አንዱ ከሆነ ሦስተኛ ቀኑ ነው። ኢየሱስ፣ ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርቱ መካከል ከአንዳንዶቹ ጋር በመሆን ወዳደጉበት አካባቢ ማለትም በስተ ሰሜን ወደምትገኘው የገሊላ አውራጃ እየተጓዘ ነው። የሚሄዱት ወደ ቃና ሲሆን ናትናኤል የመጣው ከዚህች ከተማ ነው። ቃና፣ ኢየሱስ ካደገባት ከናዝሬት በስተ ሰሜን ኮረብታ ላይ ትገኛለች። በዚህች ከተማ በአንድ የሠርግ ድግስ ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል።

የኢየሱስ እናትም ወደ ሠርጉ መጥታለች። ማርያም የሙሽሮቹ ቤተሰብ ወዳጅ በመሆኗ ወደ ሠርጉ የተጠሩትን ብዙ እንግዶች በማስተናገድ ረገድ ድርሻ የነበራት ይመስላል። በመሆኑም የጎደለ ነገር መኖሩን ልክ ስታስተውል “የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል” ብላ ለኢየሱስ ነገረችው።—ዮሐንስ 2:3

ማርያም የወይን ጠጅ በማለቁ ኢየሱስ አንድ ነገር እንዲያደርግ መጠቆሟ ነበር። ኢየሱስ፣ በሐሳቧ አለመስማማቱን ለመግለጽ ፈሊጣዊ አነጋገር በመጠቀም “አንቺ ሴት፣ ይህ ጉዳይ እኔንና አንቺን ምን ይመለከተናል?” ሲል ጠየቃት። (ዮሐንስ 2:4) በአምላክ የተሾመ ንጉሥ እንደ መሆኑ መጠን እንቅስቃሴውን የሚመራው በሰማይ ያለው አባቱ እንጂ ቤተሰቡ ወይም ጓደኞቹ አይደሉም። ማርያምም በዚያ የሚያገለግሉትን ሰዎች “የሚላችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ” በማለት ጉዳዩን ለልጅዋ ተወችው፤ በዚህ መንገድ ጥበብ አሳይታለች።—ዮሐንስ 2:5

በሠርጉ ቦታ፣ እያንዳንዳቸው ከ40 ሊትር በላይ ሊይዙ የሚችሉ ከድንጋይ የተሠሩ ስድስት ጋኖች ነበሩ። ኢየሱስ፣ የሚያስተናግዱትን ሰዎች “ጋኖቹን ውኃ ሙሏቸው” አላቸው። ከዚያም “አሁን ቀድታችሁ ለድግሱ አሳዳሪ ስጡት” ብሎ ነገራቸው።—ዮሐንስ 2:7, 8

አሳዳሪው በወይን ጠጁ ጣዕምና ጥራት በጣም ተደነቀ፤ ሆኖም የወይን ጠጁ ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንደተገኘ አላወቀም። በመሆኑም ሙሽራውን ጠርቶ “ሰው ሁሉ በቅድሚያ ጥሩውን የወይን ጠጅ ያቀርብና ሰዎቹ ከሰከሩ በኋላ መናኛውን ያቀርባል። አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስካሁን ድረስ አስቀምጠሃል” አለው።—ዮሐንስ 2:10

ኢየሱስ የፈጸመው የመጀመሪያው ተአምር ይህ ነው። አዳዲሶቹ ደቀ መዛሙርት ይህን ሲያዩ በእሱ ላይ ያላቸው እምነት ተጠናከረ። ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ከእናቱና ከወንድሞቹ ጋር ሆኖ ከገሊላ ባሕር በስተ ሰሜን ምዕራብ ወደምትገኘው ቅፍርናሆም የተባለች ከተማ ተጓዘ።