በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 13

ኢየሱስ ፈተናዎችን ከተቋቋመበት መንገድ መማር

ኢየሱስ ፈተናዎችን ከተቋቋመበት መንገድ መማር

ማቴዎስ 4:1-11 ማርቆስ 1:12, 13 ሉቃስ 4:1-13

  • ሰይጣን ኢየሱስን ፈተነው

ኢየሱስ በዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ የአምላክ መንፈስ ወደ ይሁዳ ምድረ በዳ ወሰደው። ኢየሱስ የሚያስብበት ብዙ ነገር አለ። ሲጠመቅ ‘ሰማያት ተከፍተው’ ነበር። (ማቴዎስ 3:16) ይህም በሰማይ የተማራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች ማስታወስ እንዲችል አድርጎታል። በእርግጥም ብዙ የሚያሰላስልበት ነገር አለው!

ኢየሱስ በምድረ በዳ 40 ቀንና 40 ሌሊት ቆየ። በዚህ ወቅት ምንም ነገር አልቀመሰም። ኢየሱስ በጣም በተራበበት ወቅት ሰይጣን ዲያብሎስ ሊፈትነው ወደ እሱ በመቅረብ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው። (ማቴዎስ 4:3) ኢየሱስ ግን ተአምር የመሥራት ኃይሉን ለግል ጥቅም ማዋሉ ስህተት መሆኑን ስለሚያውቅ ለፈተናው አልተሸነፈም።

ሆኖም ዲያብሎስ ተስፋ አልቆረጠም። ሌላ ፈተና አቀረበ። ራሱን ከቤተ መቅደሱ አናት ላይ እንዲወረውር ኢየሱስን በመጠየቅ ተፈታተነው። ያም ሆኖ ኢየሱስ እንዲህ ያለ አስደናቂ ትዕይንት ለማሳየት አልሞከረም። አምላክን በዚህ መንገድ መፈታተን ትክክል እንዳልሆነ ከቅዱሳን መጻሕፍት በመጥቀስ ገለጸ።

ዲያብሎስ ሦስተኛ ፈተና አቀረበለት፤ “የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን” በሆነ መንገድ ለኢየሱስ ካሳየው በኋላ “አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። በዚህ ጊዜም ኢየሱስ “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ!” በማለት በግልጽ ተቃወመው። (ማቴዎስ 4:8-10) ኢየሱስ፣ ቅዱስ አገልግሎት መቅረብ ያለበት ለይሖዋ ብቻ እንደሆነ ስለሚያውቅ የተሳሳተ ነገር እንዲያደርግ ለቀረበለት ፈተና አልተሸነፈም። ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ለመቆም መርጧል።

ለኢየሱስ ከቀረቡት ከእነዚህ ፈተናዎችና እሱ ከሰጠው ምላሽ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። እነዚህ ፈተናዎች በምናብ የተፈጠሩ አይደሉም፤ ይህም አንዳንዶች እንደሚሉት ዲያብሎስ በሰዎች ውስጥ ያለ የክፋት ባሕርይ ሳይሆን በእውን ያለ የማይታይ አካል መሆኑን ያሳያል። በተጨማሪም ይህ ዘገባ የዓለም መንግሥታት በሙሉ የዲያብሎስ ንብረት መሆናቸውን፣ በሌላ አባባል የሚቆጣጠራቸው እሱ መሆኑን ያመለክታል። ባይሆኑማ ኖሮ ዲያብሎስ እነሱን ለክርስቶስ እንደሚሰጠው መናገሩ እንዴት ፈተና ሊሆን ይችላል?

በተጨማሪም ዲያብሎስ፣ ኢየሱስ አንድ ጊዜ እንኳ ቢያመልከው በምላሹ ትልቅ ነገር ለማድረግ ይኸውም የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል። ዲያብሎስ እኛንም በተመሳሳይ መንገድ ሊፈትነን ይሞክር ይሆናል፤ ምናልባትም ዓለማዊ ብልጽግና፣ ሥልጣን ወይም ክብር ለማግኘት የሚያስችሉ የሚያጓጉ አጋጣሚዎችን ያቀርብልን ይሆናል። ፈተናው ምንም ይሁን ምን መቼም ቢሆን ለአምላክ ታማኝ በመሆን የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን ብልህነት ነው! ይሁንና ዲያብሎስ፣ ኢየሱስን የተወው “ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ” ብቻ እንደሆነ አስታውስ። (ሉቃስ 4:13) ከእኛም ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ነገር ሊያደርግ ስለሚችል ሁልጊዜ ንቁ መሆን አለብን።