በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 86

ጠፍቶ የነበረው ልጅ ተመለሰ

ጠፍቶ የነበረው ልጅ ተመለሰ

ሉቃስ 15:11-32

  • ጠፍቶ የነበረው ልጅ ምሳሌ

ኢየሱስ ስለጠፋችው በግ እና ስለጠፋው ድራክማ ሳንቲም የሚገልጹትን ምሳሌዎች የተናገረው ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በምትገኘው በፔሪያ እያለ ሳይሆን አይቀርም። ሁለቱም ምሳሌዎች፣ አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ ገብቶ ወደ አምላክ ሲመለስ ልንደሰት እንደሚገባ ያስተምሩናል። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ስለሚቀርብ ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ተችተውታል። ይሁንና እንዲህ ያሉት ተቺዎች ኢየሱስ ከተናገራቸው ሁለት ምሳሌዎች ትምህርት አግኝተው ይሆን? በሰማይ ያለው አባታችን ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን እንዴት እንደሚመለከታቸው ተረድተውስ ይሆን? ኢየሱስ አሁን የሚናገረው ልብ የሚነካ ምሳሌ ይህንኑ ጠቃሚ ትምህርት የሚያጎላ ነው።

በምሳሌው ላይ የተገለጸው አባት፣ ሁለት ልጆች ያሉት ሲሆን ዋነኛው ገጸ ባሕርይ ታናሹ ልጅ ነው። ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም ሆኑ ኢየሱስን የሚያዳምጡት ሌሎች ሰዎች ስለ ታናሹ ልጅ ከተገለጸው ሐሳብ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። ኢየሱስ ስለ አባትየውና ስለ ታላቁ ልጅ የተናገረው ነገርም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤ ምክንያቱም ከእነሱ አመለካከት የምናገኘው ትምህርት አለ። እንግዲያው ኢየሱስ ምሳሌውን ሲተርክ ከሦስቱም ሰዎች ስለምናገኘው ትምህርት ለማሰብ ሞክር፦

ኢየሱስ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት” በማለት ምሳሌውን ጀመረ። “ታናሽየውም ልጅ አባቱን ‘አባቴ ሆይ፣ ከንብረትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው። በመሆኑም አባትየው ንብረቱን ለልጆቹ አካፈላቸው።” (ሉቃስ 15:11, 12) ታናሽየው ልጅ ድርሻውን የጠየቀው አባቱ በመሞቱ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። አባትየው በሕይወት አለ። ልጁ ድርሻው አሁን እንዲሰጠው የጠየቀው ከአባቱ ተለይቶ እንደፈለገው ለመኖር ስላሰበ ነው። ታዲያ ንብረቱን ምን ያደርግበት ይሆን?

ኢየሱስ ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሽየው ልጅ ያለውን ነገር ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ተጓዘ፤ በዚያም ልቅ የሆነ ሕይወት በመኖር ንብረቱን አባከነ።” (ሉቃስ 15:13) ይህ ልጅ፣ ጥበቃ የሚያገኝበትን ቤት እንዲሁም ለልጆቹ አሳቢ የሆነውንና አስፈላጊውን ነገር የሚያቀርብላቸውን አባቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። እዚያም ከዝሙት አዳሪዎች ጋር ሲቀብጥ ንብረቱን ሁሉ ረጭቶ ጨረሰው። ከዚያም ኢየሱስ ቀጥሎ እንደገለጸው አስቸጋሪ ጊዜ መጣ፦

“ያለውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ በዚያ አገር በሙሉ ከባድ ረሃብ ተከሰተ፤ በዚህ ጊዜ ችግር ላይ ወደቀ። ከችግሩም የተነሳ ከዚያ አገር ሰዎች ወደ አንዱ ሄዶ የሙጥኝ አለ፤ ሰውየውም አሳማ እንዲጠብቅለት ወደ ሜዳ ላከው። እሱም አሳማዎቹ የሚመገቡትን ምግብ በልቶ ለመጥገብ ይመኝ ነበር፤ ነገር ግን የሚሰጠው አልነበረም።”—ሉቃስ 15:14-16

በአምላክ ሕግ መሠረት አሳማዎች ርኩስ ናቸው፤ ያም ቢሆን ይህ ልጅ የአሳማ እረኛ ለመሆን ተገዷል። ጠኔ ስለበረታበት የሚጠብቃቸው አሳማዎች የሚበሉትን ምግብ እንኳ እስከ መመኘት ደረሰ። ይህ ልጅ መከራው ሲከፋበት ‘ወደ ልቦናው ተመለሰ።’ ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን? እንዲህ አለ፦ “ስንቶቹ የአባቴ ቅጥር ሠራተኞች ምግብ ተርፏቸው እኔ እዚህ በረሃብ ልሞት ነው! ተነስቼ ወደ አባቴ በመሄድ እንዲህ እለዋለሁ፦ ‘አባቴ ሆይ፣ በአምላክና በአንተ ላይ በደል ፈጽሜአለሁ። ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም። ከቅጥር ሠራተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ።’” ከዚያም ተነስቶ ወደ አባቱ ሄደ።—ሉቃስ 15:17-20

አባቱ እንዴት ይቀበለው ይሆን? ልጁን ይቆጣው እንዲሁም መጀመሪያውኑም ከቤት ወጥቶ መሄዱ ሞኝነት መሆኑን በመግለጽ ይወቅሰው ይሆን? ወይስ የልጁ መመለስ ምንም ግድ እንዳልሰጠው ያሳያል? የአንተ ልጅ ቢሆን ኖሮ እንዴት ትቀበለው ነበር?

የጠፋው ልጅ ተገኘ

ልጁ ሲመለስ አባትየው የተሰማውን ስሜትና ያደረገውን ነገር ኢየሱስ እንዲህ በማለት ገለጸ፦ “ገና ሩቅ ሳለም አባቱ አየው፤ በዚህ ጊዜ አንጀቱ ተላወሰ፤ እየሮጠ ሄዶም አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው።” (ሉቃስ 15:20) ልጁ ልቅ ሕይወት ይመራ እንደነበር አባትየው ሰምቶ ሊሆን ቢችልም እጁን ዘርግቶ ተቀብሎታል። ይሖዋን እንደሚያውቁትና እንደሚያመልኩት የሚናገሩት የሃይማኖት መሪዎች፣ በሰማይ ያለው አባታችን ንስሐ ለሚገቡ ኃጢአተኞች ያለውን አመለካከት ከዚህ ምሳሌ ይገነዘቡ ይሆን? ኢየሱስም እንዲህ ያሉትን ሰዎች በደስታ እንደሚቀበል ያስተውሉ ይሆን?

አስተዋይ የሆነው ይህ አባት፣ በልጁ ፊት ላይ የሚነበበውን ሐዘን በመመልከት ልጁ እንደተጸጸተ መገንዘብ ይችል ይሆናል። አባትየው ልጁን በፍቅር መቀበሉ ልጁ ኃጢአቱን መናዘዝ ቀላል እንዲሆንለት ያደርጋል። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከዚያም ልጁ ‘አባቴ ሆይ፣ በአምላክና በአንተ ላይ በደል ፈጽሜአለሁ። ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም’ አለው።”—ሉቃስ 15:21

አባትየው ባሪያዎቹን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ቶሎ በሉ! ምርጥ የሆነውን ልብስ አምጥታችሁ አልብሱት፤ ለእጁ ቀለበት፣ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት። የሰባውንም ጥጃ አምጥታችሁ እረዱ፤ እንብላ፤ እንደሰት። ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና፤ አሁን ግን ሕያው ሆኗል። ጠፍቶ ነበር፤ ተገኝቷል።” ከዚያም “ይደሰቱ ጀመር።”—ሉቃስ 15:22-24

በዚህ ጊዜ ታላቁ ልጅ ያለው በእርሻ ቦታ ነው። ኢየሱስ ስለ እሱ ሲናገር እንዲህ አለ፦ “ተመልሶ መጥቶ ወደ ቤት በተቃረበ ጊዜ የሙዚቃና የጭፈራ ድምፅ ሰማ። ስለዚህ ከአገልጋዮቹ አንዱን ጠርቶ ነገሩ ምን እንደሆነ ጠየቀው። አገልጋዩም ‘ወንድምህ መጥቷል፤ በደህና ስለመጣም አባትህ የሰባውን ጥጃ አርዶለታል’ አለው። እሱ ግን ተቆጣ፤ ወደ ቤት ለመግባትም አሻፈረኝ አለ። ከዚያም አባቱ ወጥቶ ይለምነው ጀመር። እሱም መልሶ አባቱን እንዲህ አለው፦ ‘እነሆ፣ እኔ ስንት ዓመት ሙሉ እንደ ባሪያ ሳገለግልህ ኖርኩ፤ መቼም ቢሆን ከትእዛዝህ ዝንፍ ብዬ አላውቅም፤ አንተ ግን ከጓደኞቼ ጋር እንድደሰት አንዲት የፍየል ጠቦት እንኳ ሰጥተኸኝ አታውቅም። ሆኖም ሀብትህን ከዝሙት አዳሪዎች ጋር ያወደመው ይህ ልጅህ ገና ከመምጣቱ የሰባውን ጥጃ አረድክለት።’”—ሉቃስ 15:25-30

ኢየሱስ ለተራው ሕዝብና ለኃጢአተኞች ምሕረት በማሳየቱና ትኩረት በመስጠቱ ልክ እንደ ታላቁ ልጅ የነቀፉት እነማን ናቸው? ጸሐፍትና ፈሪሳውያን አይደሉም? ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ለመናገር የተነሳሳው ኃጢአተኞችን በመቀበሉ ትችት ስለሰነዘሩበት ነው። በእርግጥም አምላክ ምሕረት በማሳየቱ ቅር የሚሰኙ ሁሉ ከዚህ ምሳሌ ትምህርት ሊያገኙ ይገባል።

ኢየሱስ ምሳሌውን የደመደመው አባትየው ለታላቁ ልጁ ያቀረበውን ልመና በመግለጽ ነው፦ “ልጄ፣ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ ደግሞም የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው። ሆኖም ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኗል፤ ጠፍቶ ነበር፤ ተገኝቷል። ስለዚህ ልንደሰትና ሐሴት ልናደርግ ይገባል።”—ሉቃስ 15:31, 32

ኢየሱስ፣ ታላቁ ልጅ በመጨረሻ ምን እንዳደረገ አልገለጸም። ሆኖም ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ‘ብዙ ካህናት ይህን እምነት ተቀብለዋል።’ (የሐዋርያት ሥራ 6:7) ከእነዚህም መካከል ኢየሱስ፣ ጠፍቶ ስለነበረው ልጅ የተናገረውን ይህን ልብ የሚነካ ምሳሌ ከሰሙት አንዳንዶቹ ይገኙበት ይሆናል። እነሱም እንኳ ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ንስሐ በመግባት ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና አድሰው ሊሆን ይችላል።

ከዚያ ጊዜ ወዲህ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከዚህ ግሩም ምሳሌ የሚገኙትን ጠቃሚ ነጥቦች ልብ ብለው ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከምሳሌው የሚገኘው የመጀመሪያ ትምህርት፣ “ሩቅ አገር” ያሉ ማራኪ ነገሮችን ለማግኘት ስንል ከመባዘን ይልቅ ጥበቃ በምናገኝበት በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሆነን ከሚወደንና የሚያስፈልገንን ከሚያቀርብልን አባታችን ሳንርቅ መኖር የጥበብ አካሄድ መሆኑን መገንዘብ ነው።

ሌላው የምናገኘው ትምህርት ደግሞ ማናችንም ብንሆን ከአምላክ መንገድ ከወጣን፣ የአባታችንን ሞገስ እንደገና ማግኘት እንድንችል በትሕትና ወደ እሱ መመለስ እንዳለብን ነው።

እጁን ዘርግቶ ልጁን በምሕረት በተቀበለው አባትና ምሬት ባደረበት ብሎም ወንድሙን ለመቀበል ፈቃደኛ ባልሆነው በታላቅ ወንድሙ መካከል ያለው ልዩነትም ሌላ ትምህርት ይሰጠናል። ባዝኖ የነበረ ሰው ከልቡ ንስሐ ገብቶ ‘ወደ አባቱ ቤት’ ሲመለስ የአምላክ አገልጋዮች ይቅር ሊሉትና በደስታ ሊቀበሉት እንደሚገባ ግልጽ ነው። እንግዲያው ‘ሞቶ የነበረው’ ወንድማችን ‘ሕያው ስለሆነ’ እንዲሁም ‘ጠፍቶ የነበረው’ ወንድማችን ‘ስለተገኘ’ እንደሰት።