በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 98

ሐዋርያት ትልቅ ቦታ እንደሚፈልጉ እንደገና አሳዩ

ሐዋርያት ትልቅ ቦታ እንደሚፈልጉ እንደገና አሳዩ

ማቴዎስ 20:17-28 ማርቆስ 10:32-45 ሉቃስ 18:31-34

  • ኢየሱስ ስለ ሞቱ እንደገና ተናገረ

  • ትልቅ ቦታ ለሚፈልጉት ሐዋርያት ትምህርት መስጠት

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በስተ ደቡብ ፔሪያን አቋርጠው ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ ሲሆን ኢያሪኮ አጠገብ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ። ሌሎችም በ33 ዓ.ም. በሚከበረው የፋሲካ በዓል ላይ ለመገኘት አብረዋቸው እየተጓዙ ነው።

ኢየሱስ ለፋሲካ በዓል ኢየሩሳሌም ለመድረስ ስላሰበ ከደቀ መዛሙርቱ ፊት ፊት እየሄደ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ግን ፈርተዋል። አልዓዛር በሞተበት ጊዜ ኢየሱስ ከፔሪያ ወደ ይሁዳ ሊሄድ ሲል ቶማስ ሌሎቹን “ከእሱ ጋር እንድንሞት አብረነው እንሂድ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 11:16, 47-53) በእርግጥም ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ አደገኛ በመሆኑ ደቀ መዛሙርቱ መፍራታቸው ምንም አያስገርምም።

ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ በቅርቡ ለሚፈጸመው ነገር እንዲዘጋጁ ለመርዳት ሲል ለብቻቸው ወስዶ እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት አልፎ ይሰጣል። እነሱም ሞት ይፈርዱበታል፤ እንዲሁም እንዲያፌዙበት፣ እንዲገርፉትና በእንጨት ላይ እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ እሱም በሦስተኛው ቀን ይነሳል።”—ማቴዎስ 20:18, 19

ኢየሱስ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር ይህ ሦስተኛ ጊዜው ነው። (ማቴዎስ 16:21፤ 17:22, 23) በዚህ ጊዜ ግን በእንጨት ላይ እንደሚሰቀል ገለጸ። ሐዋርያቱ የነገራቸውን ቢሰሙም ምን ማለቱ እንደሆነ አልገባቸውም። ምናልባትም የእስራኤል መንግሥት በምድር ላይ ተመልሶ እንደሚቋቋም እየጠበቁ ይሆናል፤ በዚህ ምድራዊ መንግሥት ከክርስቶስ ጋር ክብርና ትልቅ ቦታ ለማግኘት ፈልገው ሊሆን ይችላል።

ከኢየሱስ ጋር ከሚጓዙት ሰዎች መካከል ያዕቆብና ዮሐንስ የተባሉት ሐዋርያት እናት ትገኝበታለች፤ ይህች ሴት ሰሎሜ ሳትሆን አትቀርም። ኢየሱስ ለእነዚህ ሁለት ሐዋርያት “የነጎድጓድ ልጆች” የሚል ትርጉም ያለው ስም ሰጥቷቸዋል፤ እንዲህ ያላቸው ቁጡ በመሆናቸው እንደሆነ ጥርጥር የለውም። (ማርቆስ 3:17፤ ሉቃስ 9:54) እነዚህ ሁለት ሐዋርያት በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ የማግኘት ምኞት ካደረባቸው ትንሽ ቆይተዋል። እናታቸውም ይህን ታውቃለች። አሁን እናታቸው እነሱን ወክላ ወደ ኢየሱስ በመቅረብ በፊቱ ሰገደችና አንድ ውለታ እንዲውልላት ለመነችው። ኢየሱስም “ምንድን ነው የፈለግሽው?” አላት። እሷም “በመንግሥትህ እነዚህን ሁለቱን ልጆቼን፣ አንዱን በቀኝህ አንዱን ደግሞ በግራህ አስቀምጥልኝ” አለችው።—ማቴዎስ 20:20, 21

ጥያቄው የመነጨው ከያዕቆብና ከዮሐንስ ነው። ኢየሱስ በቅርቡ ስለሚደርስበት ኀፍረትና ውርደት ተናግሮ መጨረሱ ነው፤ በመሆኑም እነዚህን ሐዋርያት “የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ በቅርቡ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁ?” አላቸው። እነሱም “እንችላለን” ብለው መለሱ። (ማቴዎስ 20:22) ይህ ምን እንደሚያስከትልባቸው ግን የገባቸው አይመስልም።

የሆነ ሆኖ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “በእርግጥ የእኔን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ግን አባቴ ላዘጋጀላቸው የሚሰጥ እንጂ በእኔ ፈቃድ የሚሆን አይደለም።”—ማቴዎስ 20:23

አሥሩ ሐዋርያት ያዕቆብና ዮሐንስ ያቀረቡትን ልመና ሲሰሙ ተቆጡ። ምናልባትም ቀደም ሲል ሐዋርያቱ በመካከላቸው ታላቅ ስለሚሆነው ሰው በተከራከሩ ጊዜ ያዕቆብና ዮሐንስ በክርክሩ ላይ የጎላ ድርሻ ኖሯቸው ይሆናል። (ሉቃስ 9:46-48) ያም ሆነ ይህ አሁን የቀረበው ጥያቄ፣ ራስን ከሁሉ እንደሚያንስ አድርጎ ስለመቁጠር ኢየሱስ የሰጠውን ምክር 12ቱም ሐዋርያት እንዳልሠሩበት ያሳያል። አሁንም ቢሆን ትልቅ ቦታ የማግኘት ፍላጎታቸው አልጠፋም።

ኢየሱስ አሁን የተነሳውን ውዝግብና ይህ በሐዋርያቱ መካከል ያስከተለውን መጥፎ ስሜት ለማስወገድ ወሰነ። አሥራ ሁለቱን አንድ ላይ ከጠራቸው በኋላ እንዲህ በማለት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መከራቸው፦ “ብሔራትን የሚገዙ ነገሥታት በሕዝባቸው ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ፣ ታላላቆቻቸውም በኃይል እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ። በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መሆን የለበትም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባል፤ እንዲሁም ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ሊሆን ይገባል።”—ማርቆስ 10:42-44

ኢየሱስ ሊከተሉት የሚገባው የእሱን ምሳሌ እንደሆነ ሲገልጽ “የሰው ልጅም የመጣው ለማገልገልና በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል አይደለም” አላቸው። (ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ ለሦስት ዓመት ገደማ ሌሎችን ሲያገለግል ቆይቷል። ለሰው ዘር ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት እንኳ ፈቃደኛ ነው! ደቀ መዛሙርቱም ክርስቶስ ያሳየውን ይህንኑ ዝንባሌ በማሳየት ከመገልገል ይልቅ ማገልገል እንዲሁም ራሳቸውን ከፍ ከማድረግ ይልቅ ከሁሉ እንደሚያንሱ አድርገው ራሳቸውን መቁጠር ይኖርባቸዋል።