በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 135

ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለብዙዎች ተገለጠ

ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለብዙዎች ተገለጠ

ሉቃስ 24:13-49 ዮሐንስ 20:19-29

  • ኢየሱስ ወደ ኤማሁስ በሚወስደው መንገድ ላይ ተገለጠ

  • ቅዱሳን መጻሕፍትን ለደቀ መዛሙርቱ በተደጋጋሚ ጊዜ ገለጠላቸው

  • የቶማስ ጥርጣሬ ተወገደ

ዕለቱ እሁድ፣ ኒሳን 16 ሲሆን ደቀ መዛሙርቱ በሐዘን ተውጠዋል። መቃብሩ ባዶ መሆኑ ምን ትርጉም እንዳለው አልገባቸውም። (ማቴዎስ 28:9, 10፤ ሉቃስ 24:11) በዚያው ቀን ወደ በኋላ ላይ ቀለዮጳና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር ከኢየሩሳሌም 11 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ወደ ኤማሁስ መጓዝ ጀመሩ።

ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ስለተፈጸመው ነገር እየተነጋገሩ ነው። በዚህ መሃል አንድ የማያውቁት ሰው አብሯቸው መሄድ ጀመረ። እሱም “እየተጓዛችሁ እንዲህ እርስ በርስ የምትወያዩበት ጉዳይ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። ቀለዮጳም መልሶ “በኢየሩሳሌም ውስጥ ለብቻህ የምትኖር እንግዳ ሰው ነህ እንዴ? ሰሞኑን በዚያ የተፈጸመውን ነገር አታውቅም ማለት ነው?” አለው። ሰውየውም “ምን ተፈጸመ?” ብሎ ጠየቃቸው።—ሉቃስ 24:17-19

እነሱም “ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ የተፈጸመው ነገር ነዋ!” አሉት። አክለውም “እኛ ግን ይህ ሰው እስራኤልን ነፃ ያወጣል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር” በማለት ተናገሩ።—ሉቃስ 24:19-21

ቀለዮጳና ጓደኛው በዚያ ዕለት የተፈጸሙትን ነገሮች ተረኩለት። ወደ ኢየሱስ መቃብር የሄዱ አንዳንድ ሴቶች መቃብሩን ባዶ እንዳገኙት እንዲሁም ተአምራዊ ነገር እንደተመለከቱ ይኸውም መላእክት ተገልጠው ኢየሱስ ሕያው መሆኑን እንደነገሯቸው ገለጹለት። ሁለቱ ደቀ መዛሙርት፣ ሌሎችም ወደ መቃብሩ እንደሄዱና ‘ሴቶቹ እንደተናገሩት ሆኖ እንዳገኙት’ ገለጹ።—ሉቃስ 24:24

ሁለቱ ደቀ መዛሙርት የተፈጸሙት ነገሮች ግራ እንዳጋቧቸው ግልጽ ነው። አብሯቸው እየተጓዘ ያለው ሰው፣ እንዲያዝኑ ያደረጋቸውን የተሳሳተ አመለካከታቸውን ፊት ለፊት በማረም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ማስተዋል የጎደላችሁና ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን ልባችሁ የዘገየ! ክርስቶስ እነዚህን መከራዎች መቀበልና ክብር ማግኘት አይገባውም?” (ሉቃስ 24:25, 26) ከዚያም ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ በርካታ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎችን በሚገባ አብራራላቸው።

በመጨረሻ ሦስቱ ሰዎች ወደ ኤማሁስ ተቃረቡ። ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ይበልጥ እንዲያስረዳቸው ስለፈለጉ “ቀኑ እየተገባደደና ምሽቱ እየተቃረበ ስለሆነ እኛ ጋ እደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት። ግለሰቡም እነሱ ጋ ለማደር ተስማማ። ከዚያም ምግብ መብላት ጀመሩ። ግለሰቡ ዳቦውን አንስቶ ጸሎት ካቀረበ በኋላ ቆርሶ ሲሰጣቸው ማን መሆኑን አወቁ፤ እሱ ግን ከአጠገባቸው ተሰወረ። (ሉቃስ 24:29-31) ኢየሱስ ሕያው መሆኑን አሁን እርግጠኞች ሆነዋል!

ሁለቱ ደቀ መዛሙርት በጣም ተደስተው “በመንገድ ላይ ሲያነጋግረንና ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ሲገልጥልን ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረም?” ተባባሉ። (ሉቃስ 24:32) ወዲያውኑ ተነስተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በዚያም ሐዋርያቱንና ሌሎች ደቀ መዛሙርትን አገኙ። ቀለዮጳና ጓደኛው ገና ከመናገራቸው በፊት ሌሎቹ “ጌታ በእርግጥ ተነስቷል፤ ለስምዖንም ተገልጦለታል!” አሉ። (ሉቃስ 24:34) ከዚያም ሁለቱ ደቀ መዛሙርት፣ ኢየሱስ ለእነሱ እንዴት እንደተገለጠላቸው ተረኩ። እነሱም ኢየሱስን አይተውታል።

በዚህ መሃል ኢየሱስ ባሉበት ክፍል ውስጥ ድንገት ሲገለጥ ሁሉም በጣም ደነገጡ። ይህ ለማመን የሚከብድ ነው፤ ምክንያቱም አይሁዳውያንን ፈርተው በሮቹን ቆልፈዋቸዋል። ያም ቢሆን ኢየሱስ በመካከላቸው ቆመ። ከዚያም “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። እነሱ ግን ተረበሹ። በአንድ ወቅት ተሰምቷቸው እንደነበረው ሁሉ አሁንም “መንፈስ ያዩ መሰላቸው።”—ሉቃስ 24:36, 37፤ ማቴዎስ 14:25-27

ኢየሱስ፣ ምትሃት ወይም በአእምሯቸው የፈጠሩት ነገር ሳይሆን ሥጋዊ አካል ያለው መሆኑን እርግጠኞች እንዲሆኑ ሲል እጆቹንና እግሮቹን በማሳየት እንዲህ አላቸው፦ “ለምን ትረበሻላችሁ? ለምንስ በልባችሁ ውስጥ ጥርጣሬ ያድራል? እኔ ራሴ መሆኔን እንድታውቁ እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ ደግሞም ዳስሳችሁኝ እዩ፤ መንፈስ በእኔ ላይ እንደምታዩት ሥጋና አጥንት የለውምና።” (ሉቃስ 24:36-39) ደቀ መዛሙርቱ በጣም የተደሰቱና የተደነቁ ቢሆንም ነገሩን ለማመን አመነቱ።

ኢየሱስ እውን መሆኑን እንዲያስተውሉ ይበልጥ ለመርዳት ሲል “የሚበላ ነገር አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። የተጠበሰ ቁራሽ ዓሣ ሲሰጡት ተቀብሎ በላው። ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ [ከመሞቴ በፊት] ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙራት ስለ እኔ የተጻፉት ነገሮች ሁሉ መፈጸም አለባቸው’ ብዬ የነገርኳችሁ ቃሌ ይህ ነው።”—ሉቃስ 24:41-44

ኢየሱስ፣ ለቀለዮጳና ለጓደኛው በቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፈውን በሚገባ አብራርቶላቸዋል፤ አሁን ደግሞ ለተሰበሰቡት ሁሉ ይህን አደረገ። እንዲህ አላቸው፦ “እንደሚከተለው ተብሎ ተጽፏል፤ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሞት ይነሳል፤ በስሙም የኃጢአት ይቅርታ የሚያስገኝ ንስሐ ከኢየሩሳሌም አንስቶ ለብሔራት ሁሉ ይሰበካል። እናንተም ለእነዚህ ነገሮች ምሥክር ትሆናላችሁ።”—ሉቃስ 24:46-48

ምክንያቱ ባይታወቅም ሐዋርያው ቶማስ በዚያ አልተገኘም። በቀጣዮቹ ቀናት፣ ሌሎቹ በደስታ ፈንድቀው “ጌታን አየነው!” አሉት። ቶማስ ግን “በእጆቹ ላይ ምስማሮቹ የተቸነከሩበትን ምልክት ካላየሁ እንዲሁም ጣቴን ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ካላስገባሁና እጄን በጎኑ ካላስገባሁ ፈጽሞ አላምንም” አላቸው።—ዮሐንስ 20:25

ከስምንት ቀን በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንደገና የተሰባሰቡ ሲሆን በሮቹን ቆልፈዋቸዋል፤ አሁን ግን ቶማስም በቦታው አለ። ኢየሱስ ሥጋ ለብሶ በመካከላቸው ተገለጠና “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ከዚያም ቶማስን “ጣትህን እዚህ ክተት፤ እጆቼንም ተመልከት፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አስገባ። መጠራጠርህን ተውና እመን” አለው። ቶማስም መልሶ “ጌታዬ፣ አምላኬ!” አለ። (ዮሐንስ 20:26-28) ኢየሱስ ሕያውና ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር እንዲሁም የይሖዋ አምላክ ወኪል እንደሆነ ቶማስ አሁን እርግጠኛ ሆነ።

በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ስላየኸኝ አመንክ? ሳያዩ የሚያምኑ ደስተኞች ናቸው” አለው።—ዮሐንስ 20:29