በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 127

ሳንሄድሪን ፊት ቀረበ፤ ከዚያም ወደ ጲላጦስ ተወሰደ

ሳንሄድሪን ፊት ቀረበ፤ ከዚያም ወደ ጲላጦስ ተወሰደ

ማቴዎስ 27:1-11 ማርቆስ 15:1 ሉቃስ 22:66–23:3 ዮሐንስ 18:28-35

  • ማለዳ ላይ የሳንሄድሪን ሸንጎ ያካሄደው ችሎት

  • የአስቆሮቱ ይሁዳ ራሱን ለመስቀል ሞከረ

  • ኢየሱስ፣ ጲላጦስ እንዲፈርድበት ወደ እሱ ተላከ

ጴጥሮስ ኢየሱስን ለሦስተኛ ጊዜ የካደው ሌሊቱ ሊነጋ ሲል ነው። የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት፣ ለይምሰል ያካሄዱትን ችሎት አጠናቀው ተበትነዋል። ዓርብ ጎህ ሲቀድ ሸንጎው እንደገና ተሰበሰበ፤ አሁን የተገናኙት ሌሊት ያካሄዱት ሕገ ወጥ ችሎት ሕጋዊ መልክ እንዲኖረው ለማድረግ ይመስላል። በመሆኑም ኢየሱስ ሸንጎው ፊት ቀረበ።

በዚህ ጊዜ የሸንጎው አባላት “አንተ ክርስቶስ ከሆንክ ንገረን” በማለት በድጋሚ ጠየቁት። ኢየሱስ “ብነግራችሁም እንኳ ፈጽሞ አታምኑም። ብጠይቃችሁም አትመልሱም” አለ። ያም ቢሆን ኢየሱስ በዳንኤል 7:13 ላይ ትንቢት የተነገረው ስለ እሱ መሆኑን በድፍረት ገለጸ። “ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በኃያሉ አምላክ ቀኝ ይቀመጣል” አላቸው።—ሉቃስ 22:67-69፤ ማቴዎስ 26:63

እነሱም “ስለዚህ የአምላክ ልጅ ነህ ማለት ነው?” በማለት አጥብቀው ጠየቁት። እሱም “የአምላክ ልጅ መሆኔን እናንተው ራሳችሁ እየተናገራችሁ ነው” አላቸው። ይህን በማለቱ ‘አምላክን ተሳድቧል’ በሚል ክስ ሊገደል እንደሚገባ ወሰኑ። “ከዚህ በላይ ምን ማስረጃ ያስፈልገናል?” አሉ። (ሉቃስ 22:70, 71፤ ማርቆስ 14:64) ስለዚህ ኢየሱስን አስረው ወደ ሮማዊው አገረ ገዢ ጳንጥዮስ ጲላጦስ ወሰዱት።

የአስቆሮቱ ይሁዳ፣ ኢየሱስ ወደ ጲላጦስ ሲወሰድ አይቶ ሊሆን ይችላል። ይሁዳ ኢየሱስ እንደተፈረደበት ባወቀ ጊዜ የጸጸትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት አደረበት። ይሁንና እውነተኛ ንስሐ ገብቶ አምላክን ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ 30ዎቹን የብር ሳንቲሞች ለመመለስ ሄደ። ይሁዳ ለካህናት አለቆቹ “ንጹሕ ሰው አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” አላቸው። እነሱ ግን በጭካኔ “ታዲያ እኛ ምን አገባን? የራስህ ጉዳይ ነው!” አሉት።—ማቴዎስ 27:4

ይሁዳ 30ዎቹን የብር ሳንቲሞች ቤተ መቅደሱ ውስጥ በትኖ ወጣ፤ ከዚያም ራሱን ለመግደል በመሞከር ሌላ ኃጢአት ፈጸመ። ይሁዳ ታንቆ ለመሞት ቢሞክርም ገመዱን ያሰረበት ቅርንጫፍ የተሰበረ ይመስላል። በመሆኑም ከታች ያለው ዓለት ላይ ሲወድቅ ሰውነቱ ፈነዳ።—የሐዋርያት ሥራ 1:17, 18

ኢየሱስ ወደ ጳንጥዮስ ጲላጦስ ቤተ መንግሥት የተወሰደው ገና በማለዳ ነው። ሆኖም ኢየሱስን ወደዚያ የወሰዱት አይሁዶች ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመግባት ፈቃደኞች አልሆኑም። አይሁዶች ከአሕዛብ ጋር እንዲህ ያለ ግንኙነት ማድረግ እንደሚያረክሳቸው ያምናሉ። በዚህ መንገድ ከረከሱ ደግሞ ኒሳን 15 ላይ ከሚቀርበው ማዕድ መብላት አይችሉም፤ ይህ ዕለት የቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን ሲሆን ከፋሲካ ጋር የተያያዘ በዓል እንደሆነ ይቆጠራል።

ጲላጦስ ወደ ውጭ ወጣና “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ክስ ምንድን ነው?” አላቸው። እነሱም መልሰው “ይህ ሰው ጥፋተኛ ባይሆን ኖሮ ለአንተ አሳልፈን አንሰጠውም ነበር” አሉት። ጲላጦስ ጫና ሊያሳድሩበት እየሞከሩ እንደሆነ ስለተሰማው ሳይሆን አይቀርም “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት” አላቸው። አይሁዳውያኑም “እኛ ማንንም ሰው ለመግደል ሕግ አይፈቅድልንም” በማለት ዓላማቸው ኢየሱስን መግደል እንደሆነ ጠቆሙ።—ዮሐንስ 18:29-31

ኢየሱስን በፋሲካ በዓል ላይ ከገደሉት ሕዝባዊ ዓመፅ ሊቀሰቀስ ይችላል። ሆኖም ከሳሾቹ፣ በፖለቲካዊ ክስ ተጠቅመው ሮማውያን ኢየሱስን እንዲገድሉት ማድረግ ከቻሉ በሕዝቡ ዘንድ ከተጠያቂነት ነፃ ይሆናሉ፤ ምክንያቱም ሮማውያን እንዲህ ዓይነት ክስ የቀረበባቸውን ሰዎች የመግደል ሥልጣን አላቸው።

የሃይማኖት መሪዎቹ፣ ኢየሱስ ላይ የፈረዱበት ‘አምላክን ሰድቦአል’ በሚል ክስ እንደሆነ ለጲላጦስ አልነገሩትም። አሁን የሚከተሉትን የሐሰት ክሶች አቀረቡ፦ “ይህ ሰው [1] ሕዝባችንን ሲያሳምፅ፣ [2] ለቄሳር ግብር እንዳይከፈል ሲከለክልና [3] ‘እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ’ ሲል አግኝተነዋል።”—ሉቃስ 23:2

ጲላጦስ የሮም ተወካይ እንደመሆኑ መጠን ‘ኢየሱስ ንጉሥ እንደሆነ ተናግሯል’ በሚል የተመሠረተው ክስ ቢያሳስበው የሚያስገርም አይደለም። ስለዚህ ጲላጦስ እንደገና ወደ ቤተ መንግሥቱ ገብቶ ኢየሱስን አስጠራውና “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?” ብሎ ጠየቀው። በሌላ አነጋገር፣ ‘ቄሳርን ተቃውመህ ንጉሥ እንደሆንክ በመግለጽ የሮምን ሕግ ተላልፈሃል?’ ማለቱ ነው። ኢየሱስም “ይህ የራስህ ጥያቄ ነው ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነግረውህ ነው?” አለው፤ ምናልባትም ይህን ያለው ጲላጦስ ስለ እሱ ምን ያህል እንደሰማ ማወቅ ፈልጎ ሊሆን ይችላል።—ዮሐንስ 18:33, 34

ጲላጦስ ስለ ኢየሱስ የሚያውቀው ነገር እንደሌለና እውነታውን ማወቅ እንደሚፈልግ ሲገልጽ “እኔ አይሁዳዊ ነኝ እንዴ?” አለ። አክሎም “ለእኔ አሳልፈው የሰጡህ የራስህ ሕዝብና የካህናት አለቆች ናቸው። ያደረግከው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።—ዮሐንስ 18:35

ኢየሱስ ንግሥናን በተመለከተ የተነሳውን ጉዳይ እንዲሁ አድበስብሶ ለማለፍ አልሞከረም። ኢየሱስ የሰጠው መልስ አገረ ገዢውን ጲላጦስን በጣም ሳያስገርመው አልቀረም።