በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 110

ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ያሳለፈው የመጨረሻ ቀን

ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ያሳለፈው የመጨረሻ ቀን

ማቴዎስ 23:25–24:2 ማርቆስ 12:41–13:2 ሉቃስ 21:1-6

  • ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹን እንደገና አወገዘ

  • ቤተ መቅደሱ ይጠፋል

  • አንዲት ድሃ መበለት ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች መዋጮ አደረገች

ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ባሳለፈው የመጨረሻ ቀን የጸሐፍትንና የፈሪሳውያንን ግብዝነት ማጋለጡን የቀጠለ ሲሆን ፊት ለፊት “ግብዞች” በማለት ጠራቸው። በምሳሌያዊ አነጋገር በመጠቀም እንዲህ አለ፦ “ጽዋውንና ሳህኑን ከውጭ በኩል ታጸዳላችሁ፤ ውስጡ ግን ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት የሞላበት ነው። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፣ በመጀመሪያ ጽዋውንና ሳህኑን ከውስጥ በኩል አጽዳ፤ ከዚያ በኋላ ከውጭ በኩልም ንጹሕ ይሆናል።” (ማቴዎስ 23:25, 26) ፈሪሳውያን፣ ሕጉ ርኩስ ስለሆኑ ነገሮች የሚሰጠውን መመሪያ ምንም ሳያዛንፉ የሚከተሉና ከውጭ ለሚታዩ ነገሮች ጥንቃቄ የሚያደርጉ ቢሆንም ውስጣዊ ማንነታቸውን ችላ ብለዋል፤ እንዲሁም ምሳሌያዊ ልባቸውን አላጸዱም።

ለነቢያት መቃብሮች መሥራታቸውና መቃብሮቹን ማስጌጣቸውም ግብዝነታቸውን ያሳያል። ሆኖም ኢየሱስ እንደገለጸው “የነቢያት ገዳዮች ልጆች” ናቸው። (ማቴዎስ 23:31) ኢየሱስን ለመግደል የሚያደርጉት ጥረት ለዚህ ማስረጃ ነው።—ዮሐንስ 5:18፤ 7:1, 25

ቀጥሎም ኢየሱስ፣ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ንስሐ ካልገቡ ምን እንደሚያጋጥማቸው ሲገልጽ “እናንተ እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች፣ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?” አላቸው። (ማቴዎስ 23:33) በአቅራቢያው ያለው የሂኖም ሸለቆ (ገሃነም) ቆሻሻ የሚቃጠልበት ስፍራ ነው፤ በመሆኑም ኢየሱስ ይህን ማለቱ ክፉ የሆኑት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የሚደርስባቸውን ዘላለማዊ ጥፋት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ‘ነቢያት፣ ጥበበኞችና የሕዝብ አስተማሪዎች’ በመሆን እሱን ወክለው ይናገራሉ። ታዲያ ሰዎች እንዴት ይቀበሏቸው ይሆን? ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “[ከደቀ መዛሙርቴ] መካከል አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ እንዲሁም በእንጨት ላይ ትሰቅላላችሁ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ በምኩራቦቻችሁ ትገርፋላችሁ፤ ከከተማ ወደ ከተማም ታሳድዷቸዋላችሁ፤ በዚህም ምክንያት ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ . . . እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ ለፈሰሰው የጻድቃን ደም ሁሉ ተጠያቂ ትሆናላችሁ።” ከዚያም “እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳሉ” በማለት አስጠነቀቀ። (ማቴዎስ 23:34-36) በ70 ዓ.ም. የሮማውያን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ሲያጠፋና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ሲያልቁ ኢየሱስ የተናገረው ነገር ፍጻሜውን አግኝቷል።

ኢየሱስ ይህን አሰቃቂ ሁኔታ ሲያስበው በጣም ተጨነቀ። በመሆኑም በሐዘን እንዲህ አለ፦ “ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም፣ ነቢያትን የምትገድል! ወደ እሷ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግር! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ እኔም ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግኩ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም። እነሆ፣ ቤታችሁ ለእናንተ የተተወ ይሆናል።” (ማቴዎስ 23:37, 38) ይህን ሲል የሰሙት ሰዎች ስለ የትኛው ‘ቤት’ እየተናገረ እንዳለ ግራ ተጋብተው ይሆናል። በኢየሩሳሌም ስላለውና አምላክ የሚጠብቀው ስለሚመስለው አስደናቂ ቤተ መቅደስ መናገሩ ይሆን?

ኢየሱስ አክሎም “እላችኋለሁ፣ ‘በይሖዋ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!’ እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ አታዩኝም” አላቸው። (ማቴዎስ 23:39) ይህን ሲል በመዝሙር 118:26 ላይ የሚገኘውን “በይሖዋ ስም የሚመጣው የተባረከ ነው፤ በይሖዋ ቤት ሆነን እንባርካችኋለን” የሚለውን ትንቢት መጥቀሱ ነው። ይህ ቤተ መቅደስ ከጠፋ በኋላ በአምላክ ስም ወደዚህ ቦታ የሚመጣ ሰው እንደማይኖር ግልጽ ነው።

ከዚህ ቀጥሎ ኢየሱስ፣ የመለከት ቅርጽ ያላቸው የመዋጮ ሣጥኖች ወደሚቀመጡበት የቤተ መቅደሱ ክፍል ሄደ። ሕዝቡ የሚሰጡትን ገንዘብ በሣጥኑ አናት ላይ ባለው ትንሽ ቀዳዳ ማስገባት ይችላሉ። ኢየሱስ የተለያዩ አይሁዳውያን ይህን ሲያደርጉ ተመለከተ፤ ሀብታሞቹ “ብዙ ሳንቲሞች” መባ አድርገው እየከተቱ ነው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ አንዲት ድሃ መበለት “በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች” ስትከት ተመለከተ። (ማርቆስ 12:41, 42) አምላክ በዚህች መበለት ስጦታ ምን ያህል እንደሚደሰት ኢየሱስ ያውቃል።

በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ በመዋጮ ሣጥኖቹ ውስጥ ገንዘብ ከጨመሩት ሁሉ የበለጠ የሰጠችው ይህች ድሃ መበለት ነች።” ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ኢየሱስ “ሁሉም የሰጡት ከትርፋቸው ነውና፤ እሷ ግን በድሃ አቅሟ ያላትን ሁሉ፣ መተዳደሪያዋን በጠቅላላ ሰጥታለች” በማለት አብራራ። (ማርቆስ 12:43, 44) የዚህች ሴት አስተሳሰብም ሆነ ድርጊት ከሃይማኖት መሪዎቹ ምንኛ የተለየ ነው!

ኒሳን 11 እየተገባደደ ሲሄድ ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ቤተ መቅደሱን ለቆ ወጣ። በዚህ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “መምህር፣ እንዴት ያሉ ግሩም ድንጋዮችና ሕንጻዎች እንደሆኑ ተመልከት!” አለው። (ማርቆስ 13:1) በእርግጥም ቤተ መቅደሱ ከተገነባባቸው ድንጋዮች መካከል አንዳንዶቹ በጣም ትላልቅ በመሆናቸው ቤተ መቅደሱ ጠንካራና የማይፈርስ እንዲመስል አድርገውታል። በመሆኑም ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት መመለሱ ግራ የሚያጋባ ይመስላል፦ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህ? ይህ ሁሉ ሳይፈርስ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ ከቶ አይኖርም።”—ማርቆስ 13:2

ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ከሐዋርያቱ ጋር የቄድሮንን ሸለቆ አቋርጦ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጣ። ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ አጠገቡ ናቸው። ከተራራው ላይ ሆነው አስደናቂውን ቤተ መቅደስ ቁልቁል መመልከት ይችላሉ።