በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 122

ኢየሱስ ያቀረበው የመደምደሚያ ጸሎት

ኢየሱስ ያቀረበው የመደምደሚያ ጸሎት

ዮሐንስ 17:1-26

  • አምላክንና ልጁን ማወቅ የሚያስገኘው ጥቅም

  • ይሖዋ፣ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ያላቸው አንድነት

ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ባለው ጥልቅ ፍቅር ተነሳስቶ በቅርቡ ከእነሱ ለሚለይበት ጊዜ ሲያዘጋጃቸው ቆይቷል። አሁን ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ለአባቱ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤ ይህም በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደሰጠኸው ሁሉ እሱም አንተ ለሰጠኸው ሰው ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲሰጥ ነው።”—ዮሐንስ 17:1, 2

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ፣ ለአምላክ ክብር መስጠት ከምንም በላይ አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቧል። ኢየሱስ የጠቀሰው ተስፋ ይኸውም የዘላለም ሕይወት ምንኛ የሚያጽናና ነው! ኢየሱስ “በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ሥልጣን” ስለተሰጠው፣ የሰው ዘር በሙሉ ከቤዛው እንዲጠቀም ማድረግ ይችላል። ይሁንና ይህን በረከት የሚያገኙት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው” ብሏል፤ ኢየሱስ ከቤዛው እንዲጠቀሙ የሚያደርገው እንዲህ ዓይነት እውቀት ያላቸውን ሰዎች ብቻ ነው።—ዮሐንስ 17:3

አንድ ሰው፣ አብንና ወልድን በቅርበት ማወቅ በሌላ አባባል ከእነሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ይኖርበታል። ለነገሮች ያለው አመለካከት እነሱ ካላቸው አመለካከት ጋር መስማማት አለበት። በተጨማሪም ተወዳዳሪ የማይገኝላቸውን የይሖዋና የኢየሱስ ባሕርያት ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ለማንጸባረቅ መጣር አለበት። ከዚህም ሌላ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ከማግኘታቸው ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር የአምላክ መከበር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገዋል። ኢየሱስ ይህን ርዕሰ ጉዳይ እንደገና አነሳ፦

“እንድሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርኩህ። ስለዚህ አባት ሆይ፣ ዓለም ከመመሥረቱ በፊት በጎንህ ሆኜ ክብር እንደነበረኝ ሁሉ አሁንም በጎንህ አድርገህ አክብረኝ።” (ዮሐንስ 17:4, 5) ኢየሱስ ይህን ሲል ቀድሞ በሰማይ የነበረውን ክብር በትንሣኤ አማካኝነት ለማግኘት እየጠየቀ ነው።

ይሁንና ኢየሱስ በአገልግሎቱ አማካኝነት ያከናወነውን ነገር አልረሳውም። “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። እነሱ የአንተ ነበሩ፤ አንተም ለእኔ ሰጠኸኝ፤ ደግሞም ቃልህን ጠብቀዋል” ሲል ጸለየ። (ዮሐንስ 17:6) ኢየሱስ በአገልግሎቱ ላይ ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም ከመጥራት ያለፈ ነገር አከናውኗል። ሐዋርያቱ የአምላክ ስም የሚወክለውን ነገር ይኸውም የይሖዋን ባሕርያትና ሰዎችን የሚይዝበትን መንገድ እንዲያውቁ ረድቷቸዋል።

ሐዋርያቱ ይሖዋን እንዲሁም ልጁ የሚጫወተውን ሚና ብሎም ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች አውቀዋል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል በትሕትና ተናገረ፦ “የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁ፤ እነሱም ተቀብለውታል፤ እንዲሁም የአንተ ተወካይ ሆኜ መምጣቴን በእርግጥ አውቀዋል፤ አንተ እንደላክኸኝም አምነዋል።”—ዮሐንስ 17:8

ከዚያም ኢየሱስ በተከታዮቹና በተቀረው የሰው ዘር መካከል ያለውን ልዩነት ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “ስለ እነሱ እለምንሃለሁ፤ የምለምንህ ስለ ዓለም ሳይሆን አንተ ስለሰጠኸኝ ሰዎች ነው፤ ምክንያቱም እነሱ የአንተ ናቸው፤ . . . ቅዱስ አባት ሆይ፣ እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ፣ ስለሰጠኸኝ ስለ ራስህ ስም ስትል ጠብቃቸው። እኔ . . . ጠብቄአቸዋለሁ፤ . . . ከጥፋት ልጅ በቀር አንዳቸውም አልጠፉም።” የጥፋት ልጅ የተባለው ኢየሱስን አሳልፎ ሊሰጥ የሄደው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነው።—ዮሐንስ 17:9-12

ኢየሱስ “ዓለም ጠላቸው” በማለት ጸሎቱን ቀጠለ። አክሎም “የምለምንህ ከዓለም እንድታወጣቸው ሳይሆን ከክፉው እንድትጠብቃቸው ነው። እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም” አለ። (ዮሐንስ 17:14-16) ሐዋርያቱና ሌሎች ተከታዮቹ በዓለም ውስጥ ይኸውም ሰይጣን በሚመራው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ውስጥ ናቸው፤ ሆኖም የኢየሱስ ተከታዮች ከዚህ ዓለምም ሆነ በዓለም ላይ ካለው ክፋት ምንጊዜም መራቅ ይኖርባቸዋል። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው?

በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን እንዲሁም ኢየሱስ ያስተማራቸውን እውነቶች ተግባራዊ በማድረግ ቅዱስ መሆን ወይም አምላክን ለማገልገል ራሳቸውን መለየት ይጠበቅባቸዋል። ኢየሱስ “በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው” በማለት ጸለየ። (ዮሐንስ 17:17) ከጊዜ በኋላ አንዳንድ ሐዋርያት በመንፈስ መሪነት መጻሕፍት ይጽፋሉ፤ እነዚህ መጻሕፍትም ቅዱስ ለመሆን በሚረዳው “እውነት” ውስጥ ይካተታሉ።

ውሎ አድሮ ‘እውነትን’ የሚቀበሉ ሌሎችም ይኖራሉ። በመሆኑም ኢየሱስ “የምለምንህ ስለ እነዚህ [አብረውት ስላሉት] ብቻ ሳይሆን በእነሱ ቃል አማካኝነት በእኔ ለሚያምኑ ጭምር ነው” በማለት ጸለየ። ኢየሱስ እነዚህን ሁሉ አስመልክቶ የጠየቀው ነገር ምንድን ነው? “ይህን ልመና የማቀርበውም ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ . . . አባት ሆይ፣ አንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለህና እኔም ከአንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ ሁሉ እነሱም ከእኛ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:20, 21) ኢየሱስና አባቱ ቃል በቃል አንድ አካል አይደሉም። አንድ የተባሉት በሁሉም ነገር ስለሚስማሙ ነው። ኢየሱስ፣ ተከታዮቹም ከእነሱ ጋር እንዲህ ዓይነት አንድነት እንዲኖራቸው ጸለየ።

ከዚህ ጥቂት ቀደም ብሎ ኢየሱስ ለጴጥሮስና ለሌሎቹ ሐዋርያት፣ ለእነሱ በሰማይ ቦታ ለማዘጋጀት እንደሚሄድ ነግሯቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:2, 3) አሁን ይህን ሐሳብ እንደገና በጸሎት ጠቀሰው፦ “አባት ሆይ፣ እነዚህ የሰጠኸኝ፣ እኔ ባለሁበት እነሱም ከእኔ ጋር እንዲሆኑ እፈልጋለሁ፤ ይህም ዓለም ከመመሥረቱ በፊት ስለወደድከኝ የሰጠኸኝን ክብር እንዲያዩ ነው።” (ዮሐንስ 17:24) ኢየሱስ ይህን ሲል ከረጅም ጊዜ በፊት ይኸውም አዳምና ሔዋን ልጅ ከመውለዳቸው በፊት አምላክ፣ በኋላ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለውን አንድያ ልጁን እንደወደደው መግለጹ ነው።

ኢየሱስ ጸሎቱን ሲደመድም የአምላክን ስም እንዲሁም አምላክ ለሐዋርያቱም ሆነ ወደፊት ‘እውነትን’ ለሚቀበሉ ሰዎች ያለውን ፍቅር በድጋሚ ጎላ አድርጎ ገለጸ፦ “እኔን የወደድክበት ፍቅር እነሱም እንዲኖራቸው እንዲሁም እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት እንዲኖረኝ ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ።”—ዮሐንስ 17:26