በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስን ለመምሰል የሚያስችሉ ባሕርያት

ኢየሱስን ለመምሰል የሚያስችሉ ባሕርያት

ርኅራኄ

ኢየሱስ ፍጹም በመሆኑ፣ ሌሎች ሰዎች የሚያስጨንቋቸው ወይም የሚያሳስቧቸው ብዙዎቹ ነገሮች አልደረሱበትም። ያም ቢሆን ለሰዎች በጥልቅ እንደሚያዝን አሳይቷል። ሌሎችን ለመርዳት ሲል የራሱን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ ይኸውም ከሚጠበቅበት አልፎ ለመሄድ ፈቃደኛ ነበር። በእርግጥም ሌሎችን ለመርዳት ያነሳሳው ርኅራኄ ነው። በሚከተሉት ምዕራፎች ላይ ያሉትን ምሳሌዎች ተመልከት፦ 32, 37, 57, 99

በቀላሉ የሚቀረብ

ልጅ አዋቂ ሳይል በማንኛውም ዕድሜ ያሉ ሰዎች ኢየሱስን ይቀርቡት ነበር፤ ምክንያቱም ሰዎች፣ በሥራ የተወጠረና ትልቅ ቦታ ያለው እንደሆነ እንዲሰማቸው አላደረገም። ኢየሱስ ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ስለሚሰጥ ከእሱ ጋር መሆን አልከበዳቸውም። ይህን ለማስተዋል የሚከተሉትን ምዕራፎች ተመልከት፦ 25, 27, 95

የጸሎት ሰው

ኢየሱስ ብቻውንም ሆነ ከሌሎች የይሖዋ አገልጋዮች ጋር ሆኖ ለአባቱ ልባዊ ጸሎት የማቅረብ ልማድ ነበረው። ምግብ ሲቀርብ ብቻ ሳይሆን በቀን ውስጥ ብዙ ጊዜ ይጸልይ ነበር። አባቱን ለማመስገን፣ ለማወደስ እንዲሁም ከባድ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት የእሱን አመራር ለማግኘት ጸልዮአል። ምሳሌዎች ለማግኘት የሚከተሉትን ምዕራፎች ተመልከት፦ 24, 34, 91, 122, 123

ራስ ወዳድ አለመሆን

ኢየሱስ እረፍት ወይም ዘና ማለት ቢያስፈልገውም እንኳ ለሌሎች ሲል የራሱን ጥቅም መሥዋዕት ያደረገባቸው ጊዜያት አሉ። እሱ ብቻ ቅድሚያ እንዲሰጠው የሚፈልግ ሰው አልነበረም። በዚህ ረገድም ቢሆን ልንከተለው የምንችል አርዓያ ትቶልናል። ኢየሱስ የተወውን አርዓያ በሚከተሉት ምዕራፎች ላይ አንብብ፦ 19, 41, 52

ይቅር ባይነት

ኢየሱስ፣ ይቅር ባይ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ በማስተማር ብቻ አልተወሰነም፤ ከደቀ መዛሙርቱም ሆነ ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ይቅር ባይ ነበር። የሚከተሉት ምዕራፎች በያዟቸው ምሳሌዎች ላይ አሰላስል፦ 26, 40, 64, 85, 131

ቅንዓት

አብዛኞቹ አይሁዳውያን መሲሑን እንደማይቀበሉትና ጠላቶቹ እንደሚገድሉት በትንቢት ተነግሮ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ሰዎችን ለመርዳት ያን ያህል ጥረት ባያደርግ የሚያስገርም አይሆንም ነበር። እሱ ግን እውነተኛውን አምልኮ በቅንዓት አራምዷል። ሰዎች፣ ቸልተኛ ይባስ ብሎም ተቃዋሚ በሆኑባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ተከታዮቹ ሁሉ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። የሚከተሉትን ምዕራፎች ተመልከት፦ 16, 72, 103

ትሕትና

ኢየሱስ እውቀትንና ጥበብን ጨምሮ ስፍር ቁጥር በሌላቸው መንገዶች፣ ፍጹም ካልሆኑ የሰው ልጆች ይበልጣል። ፍጹም መሆኑ አብረውት ከነበሩት ሰዎች ሁሉ በአካላዊ ሁኔታም ሆነ በአስተሳሰቡ የላቀ እንዲሆን እንዳደረገው ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ቢሆን በትሕትና ሌሎችን አገልግሏል። በሚከተሉት ምዕራፎች ላይ ምሳሌዎች ማግኘት ትችላለህ፦ 10, 62, 66, 94, 116

ትዕግሥት

ሐዋርያቱም ሆነ ሌሎች ሰዎች የእሱን አርዓያ ሳይከተሉ ወይም የተናገረውን በተግባር ሳያውሉ በሚቀሩበት ጊዜ ሁሉ በትዕግሥት ይይዛቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ እንዲችሉ ሲል የሚያስፈልጓቸውን ትምህርቶች ደጋግሞ ይነግራቸው ነበር። ኢየሱስ ትዕግሥት ያሳየባቸውን ምሳሌዎች ለማግኘት የሚከተሉትን ምዕራፎች ተመልከት፦ 74, 98, 118, 135