በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለማርታ የተሰጠ ምክርና ስለ ጸሎት የተሰጠ ትምህርት

ለማርታ የተሰጠ ምክርና ስለ ጸሎት የተሰጠ ትምህርት

ምዕራፍ 74

ለማርታ የተሰጠ ምክርና ስለ ጸሎት የተሰጠ ትምህርት

ኢየሱስ በይሁዳ ያገለግል በነበረበት ወቅት ቢታንያ ወደምትባለው መንደር ገባ። ቢታንያ ማርታ፣ ማርያምና ወንድማቸው አልዓዛር የሚኖሩባት መንደር ናት። ኢየሱስ እነዚህን ሦስት ሰዎች ቀደም ሲል አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ጊዜ ሳያገኛቸው አይቀርም፤ ስለዚህ የቅርብ ወዳጃቸው ሆኗል። ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ ወደ ማርታ ቤት ሄደ፤ እርስዋም ጥሩ አቀባበል አደረገችለት።

ማርታ የምትችለውን ያህል ኢየሱስን ጥሩ አድርጋ ለማስተናገድ ጓጉታለች። በእርግጥም ተስፋ የተሰጠበትን መሲሕ ቤት ውስጥ በእንግድነት መቀበል ትልቅ ክብር ነው! ስለዚህ ማርታ ትልቅ ግብዣ በማዘጋጀት እንዲሁም ኢየሱስ ይበልጥ እንዲደሰትና እንዲመቸው ለማድረግ ሌሎች ብዙ ጥቃቅን ጉዳዮችን በመከታተል በሥራ ተወጥራ ነበር።

በሌላ በኩል ደግሞ የማርታ እህት ማርያም ኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጣ እያዳመጠችው ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ማርታ ወደ ኢየሱስ መጣችና “ጌታ ሆይ፣ እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ አያገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት” አለችው።

ሆኖም ኢየሱስ ማርያምን ምንም ሊላት አልፈለገም። ከዚህ ይልቅ ማርታ ለቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ በመጨነቋ ምክር ሰጣት። “ማርታ፣ ማርታ፣ በብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ ትታወኪማለሽ፣ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው” በማለት በለሰለሰ አነጋገር ገሰጻት። ኢየሱስ አንድ ምሳ ወይም እራት ለማዘጋጀት ብዙ ዓይነት ምግብ በመሥራት ረዘም ያለ ጊዜ ማጥፋት አስፈላጊ እንዳልሆነ መናገሩ ነበር። ጥቂት ዓይነት ምግቦች ወይም አንድ ዓይነት ምግብ በቂ ነው።

ማርታ ሐሳቧ ጥሩ ነው፤ ጥሩ እንግዳ ተቀባይ ሆና ለማስተናገድ ፈልጋ ነበር። ሆኖም ለቁሳዊ ነገሮች ስትጨነቅ በግለሰብ ደረጃ ከአምላክ ልጅ መማር የምትችልበት አጋጣሚ እያመለጣት ነበር! ስለዚህ ኢየሱስ “ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም” ሲል ደምድሟል።

ከጊዜ በኋላ በሌላ ወቅት አንድ ደቀ መዝሙር ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን” ብሎ ጠየቀው። ይህ ደቀ መዝሙር ኢየሱስ ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት በተራራው ስብከቱ ላይ የጸሎት ናሙና በሰጠ ጊዜ በቦታው አልነበረ ይሆናል። ስለዚህ ኢየሱስ ያንኑ ትምህርት ከደገመ በኋላ በጸሎት የመጽናትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ለመግለጽ አንድ ምሳሌ ሰጠ።

ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ከእናንተ ማናቸውም ወዳጅ ያለው፣ በእኩል ሌሊትስ ወደ እርሱ ሄዶ:- ወዳጄ ሆይ፣ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፣ አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት የለኝምና ይላልን? ያም ከውስጥ መልሶ:- አታድክመኝ አሁን ደጁ ተቈልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ አሉ፤ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም ይላልን? እላችኋለሁ፣ ወዳጅ ስለ ሆነ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፣ ስለ ንዝነዛው ተነሥቶ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል።”

ኢየሱስ ሁኔታውን በዚህ መልኩ ያነጻጸረው ይሖዋ አምላክ በታሪኩ ላይ እንደተገለጸው ወዳጅ ልመናን ሰምቶ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም ለማለት ፈልጎ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልነበረ ወዳጅ ያለማቋረጥ ለሚቀርብለት ልመና ጥሩ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ከዚህ የበለጠ የሚያደርግ መሆኑን ለማስረዳት ብሎ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “እኔም እላችኋለሁ:- [“ሳታቋርጡ፣” NW] ለምኑ፣ ይሰጣችሁማል፤ [“ሳታቋርጡ፣” NW] ፈልጉ፣ ታገኙማላችሁ፤ [“ሳታቋርጡ፣” NW] መዝጊያን አንኳኩ፣ ይከፍትላችሁማል። የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፣ የሚፈልግም ያገኛል፣ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል።”

ከዚያም ኢየሱስ ፍጽምና የሌላቸውን ኃጢአተኛ ሰብዓዊ አባቶች በመጥቀስ እንዲህ አለ:- “አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ ዓሣ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? ወይስ እንቊላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፣ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው!” (NW) በእርግጥም ኢየሱስ በጸሎት ለመጽናት የሚያነሳሳ ግሩም ማበረታቻ ሰጥቷል። ሉቃስ 10:​38 እስከ 11:​13

▪ ማርታ ኢየሱስን ለማስተናገድ ሰፋ ያለ ዝግጅት ስታደርግ የነበረው ለምንድን ነው?

▪ ማርያም ምን አደረገች? ኢየሱስ ከማርታ ይልቅ ማርያምን ያመሰገነውስ ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ስለ ጸሎት የሰጠውን ትምህርት ለመድገም ያነሳሳው ምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ በጸሎት የመጽናትን አስፈላጊነት በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?