በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቅሶ ወደ ታላቅ ደስታ ተለወጠ

ለቅሶ ወደ ታላቅ ደስታ ተለወጠ

ምዕራፍ 47

ለቅሶ ወደ ታላቅ ደስታ ተለወጠ

ኢያኢሮስ ደም ይፈሳት የነበረችው ሴት እንደተፈወሰች ሲመለከት በኢየሱስ ተአምራዊ ኃይል ላይ ያለው ትምክህት እንደጨመረ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚያው ዕለት ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ ኢያኢሮስ በሞት አፋፍ ላይ የምትገኘውን በጣም የሚወዳትን የ12 ዓመት ልጁን መጥቶ እንዲረዳለት ኢየሱስን ለምኖት ነበር። ይሁን እንጂ ኢያኢሮስ የፈራው አልቀረም። ኢየሱስ ከሴትዮዋ ጋር እየተነጋገረ ሳለ ጥቂት ሰዎች መጡና ቀስ ብለው ኢያኢሮስን “ልጅህ ሞታለች፤ ስለ ምን መምህሩን አሁን ታደክመዋለህ?” አሉት።

ይህ እንዴት ያለ አስደንጋጭ መርዶ ነው! እስቲ አስበው:- በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ ያለው ይህ ሰው ልጁ እንደ ሞተች ሲሰማ ምንም ማድረግ የሚችለው ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሲነጋገሩ ሰማቸው። ስለዚህ ወደ ኢያኢሮስ ዞረና “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ” በማለት አበረታታው።

ኢየሱስ ሐዘን ላይ ከወደቀው ሰው ጋር ሆኖ ወደ ቤቱ አመራ። በቦታው ሲደርሱ ከፍተኛ ለቅሶና ጩኸት ይሰማ ነበር። ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ምርር ብለው እያለቀሱ ነበር። ኢየሱስ ወደ ውስጥ ሲገባ “ስለ ምን ትንጫጫላችሁ ታለቅሳላችሁም? ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው።

ሰዎቹ ይህን ሲሰሙ ልጅቷ በእርግጥ እንደሞተች ያውቁ ስለነበረ የንቀት ሳቅ ሳቁበት። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አለ። አምላክ የሰጠውን ኃይል በመጠቀም ሰዎች ከከባድ እንቅልፍ የመንቃትን ያህል በቀላሉ ከሞት ሊነሱ እንደሚችሉ ሊያሳይ ነው።

ኢየሱስ ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብ፣ ከዮሐንስና ከሞተችው ልጅ እናትና አባት በስተቀር ሁሉንም ወደ ውጪ አስወጣ። ከዚያም ከአምስቱ ሰዎች ጋር ሆኖ ልጅቷ ወዳለችበት ገባ። ኢየሱስ እጅዋን ያዘና “ጣሊታ ቁሚ” አላት፤ ፍችውም “አንቺ ብላቴና ተነሽ እልሻለሁ” ማለት ነው። ወዲያውኑ ልጅቷ ተነሳችና መራመድ ጀመረች! ወላጆቿ ባዩት ነገር በጣም ከመደሰታቸው የተነሳ ራሳቸውን ሊስቱ ምንም ያህል አልቀራቸውም።

ኢየሱስ ለልጅቷ የምትበላው ነገር እንዲሰጧት ከነገራቸው በኋላ የተፈጸመውን ነገር ለማንም እንዳይናገሩ ኢያኢሮስንና ሚስቱን አዘዛቸው። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ቢያዝዛቸውም እንኳ ወሬው በክልሉ ሁሉ ተዳረሰ። ይህ ኢየሱስ የፈጸመው ሁለተኛው ትንሣኤ ነበር። ማቴዎስ 9:​18-26፤ ማርቆስ 5:​35-43፤ ሉቃስ 8:​41-56

▪ ኢያኢሮስ ምን ወሬ ደረሰው? ኢየሱስ ያጽናናውስ እንዴት ነው?

▪ ኢያኢሮስ ቤት ሲደርሱ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

▪ ኢየሱስ የሞተችው ልጅ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም ያለው ለምንድን ነው?

▪ ከኢየሱስ ጋር ሆነው ትንሣኤው ሲፈጸም ያዩት አምስት ሰዎች እነማን ናቸው?