በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለተጨነቁ ርኅራኄ ማሳየት

ለተጨነቁ ርኅራኄ ማሳየት

ምዕራፍ 57

ለተጨነቁ ርኅራኄ ማሳየት

ኢየሱስ ፈሪሳውያን ለራሳቸው ጥቅም የሚያገለግሉ ወጎችን በማውጣታቸው ካወገዛቸው በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሄደ። ከጥቂት ጊዜ በፊት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በመሄድ ትንሽ ለማረፍ አድርጎት የነበረው ሙከራ በሕዝቡ እንደተስተጓጎለ ታስታውስ ይሆናል። አሁን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ በሰሜን ብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኙት ወደ ጢሮስና ሲዶና ክልሎች ተጓዘ። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ ከእስራኤል ድንበር ውጪ ያደረገው ጉዞ ይህ ብቻ ሳይሆን አይቀርም።

ኢየሱስ የሚያርፍበት ቤት ካገኘ በኋላ ያሉበትን ቦታ ማንም እንዲያውቅ እንደማይፈልግ ገለጸ። ሆኖም ከእስራኤል ክልል ውጪ በሆነው በዚህ ሥፍራ እንኳ ከሰዎች ሊሰወር አልቻለም። ሶርያ ውስጥ በምትገኘው በፊንቄ የተወለደች አንዲት ግሪካዊት ሴት አገኘችውና “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል” እያለች ትለምነው ጀመር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ምንም መልስ አልሰጣትም።

በመጨረሻ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት” አሉት። ኢየሱስ “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በስተቀር አልተላክሁም” በማለት ለምን ዝም እንዳላት ገለጸ።

ሆኖም ሴትዮዋ ተስፋ አልቆረጠችም። ወደ ኢየሱስ ቀረበችና በፊቱ ሰገደች። “ጌታ ሆይ፣ እርዳኝ” ብላ ለመነችው።

የሴትዮዋ ልባዊ ልመና የኢየሱስን ልብ ምንኛ ነክቶት ይሆን! ሆኖም ኢየሱስ በድጋሚ የመጀመሪያ ኃላፊነቱ የአምላክ ሕዝብ የሆኑትን እስራኤላውያን ማገልገል እንደሆነ ገለጸ። በተጨማሪም የሴትዮዋን እምነት ለመፈተን ሳይሆን አይቀርም፣ አይሁዳውያን ለሌሎች ብሔራት ሕዝቦች ያላቸውን በወገናዊነት ላይ የተመሠረተ ጥላቻ በመጥቀስ “የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም” አላት።

ኢየሱስ ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት የድምፅ ቃናውና የፊቱ ገጽታ አማካኝነት አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች ያለውን አዘኔታ እንደገለጸ አያጠራጥርም። እንዲያውም አሕዛብን ውሾች ብሎ ሳይሆን “ቡችሎች” ወይም ትንንሽ ውሾች ብሎ በመጥራት ሁኔታውን ቀለል አድርጎ ገልጾታል። ሴትዮዋ አልተከፋችም፤ ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ አይሁዳውያን ያላቸውን በወገናዊነት ላይ የተመሠረተ ጥላቻ በመጥቀስ በሰጠው ሐሳብ ላይ በመመርኮዝ የሚከተለውን ትሕትና የተሞላበት አስተያየት ሰጠች:- “አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ።”

“አንቺ ሴት፣ እምነትሽ ታላቅ ነው” ሲል ኢየሱስ መለሰላት። “እንደ ወደድሽ ይሁንልሽ” አላት። እንዳለውም ሆነ! ወደ ቤቷ ስትመለስ ልጅዋ ሙሉ በሙሉ ተፈውሳ አልጋዋ ላይ ቁጭ ብላ አገኘቻት።

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በባሕር ዳርቻ ከሚገኘው የሲዶና ክልል ተነሥተው አገሩን በማቋረጥ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መነሻ አቀኑ። የዮርዳኖስን ወንዝ ከገሊላ ባሕር በላይ በኩል በመሻገር ከባሕሩ በስተ ምሥራቅ ወደ ዲካፖሊስ ክልል የገቡ ይመስላል። እዚያ ከደረሱ በኋላ አንድ ተራራ ላይ ወጡ፤ ሆኖም ሕዝቡ አገኟቸውና ሽባዎችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ዓይነ ስውሮችንና ዲዳዎችን እንዲሁም ሌሎች ብዙ በሽተኞችን ወደ ኢየሱስ አመጡ። በኢየሱስ እግር ሥር አስቀመጧቸው፤ ኢየሱስም ፈወሳቸው። ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፣ ሽባዎች ሲሄዱና ዓይነ ስውሮች ሲያዩ ተመለከቱና በጣም ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አመሰገኑ።

ኢየሱስ መስማት ለተሳነውና በደንብ መናገር ለማይችል አንድ ሰው ልዩ ትኩረት አድርጎ ነበር። ብዙውን ጊዜ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በተለይ በብዙ ሕዝብ መካከል ሲሆኑ በቀላሉ ያፍራሉ። ኢየሱስ ይህ ሰው ያለበትን ለየት ያለ ጭንቀት አስተውሎ ይሆናል። ስለዚህ ኢየሱስ በርኅራኄ መንፈስ ሰውየውን ከሕዝቡ ለይቶ ወሰደው። ብቻቸውን ሲሆኑ ኢየሱስ ምን ሊያደርግለት እንደሆነ አሳየ። ጣቶቹን ሰውየው ጆሮዎች ውስጥ ከተተ፤ ቀጥሎም እንትፍ ብሎ ምላሱን ዳሰሰ። ከዚያም ወደ ሰማይ ቀና ብሎ በኃይል ተነፈሰና “ተከፈት” አለ። በዚህ ጊዜ ሰውየው የመስማት ችሎታው ተመለሰለት፤ አጥርቶ መናገርም ቻለ።

ኢየሱስ ይህን ሁሉ ፈውስ ሲፈጽም ሕዝቡ ተደነቁ። “ሁሉን ደኅና አድርጎአል ደንቆሮችም እንዲሰሙ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል” አሉ። ማቴዎስ 15:​21-31፤ ማርቆስ 7:​24-37

▪ ኢየሱስ የግሪካዊቷን ሴት ልጅ ወዲያውኑ ያልፈወሰላት ለምንድን ነው?

▪ ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወዴት ወሰዳቸው?

▪ ኢየሱስ መስማት የተሳነውንና በደንብ መናገር የማይችለውን ሰው የርኅራኄ መንፈስ ያሳየው እንዴት ነው?