በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለይሖዋ አምልኮ ያሳየው ቅንዓት

ለይሖዋ አምልኮ ያሳየው ቅንዓት

ምዕራፍ 16

ለይሖዋ አምልኮ ያሳየው ቅንዓት

የኢየሱስ ግማሽ ወንድሞች የሆኑት ሌሎቹ የማርያም ወንዶች ልጆች ያዕቆብ፣ ዮሳ፣ ስምዖንና ይሁዳ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ከገሊላ ባሕር አጠገብ ወዳለችው ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ከመጓዛቸው በፊት ቤተሰቡ የሚያስፈልጉትን ነገሮች መያዝ እንዲችሉ ናዝሬት ወደሚገኘው ቤታቸው ጎራ ሳይሉ አይቀሩም።

ሆኖም ኢየሱስ አገልግሎቱን በቃና፣ በናዝሬት ወይም በገሊላ ኮረብታማ ሥፍራዎች በሚገኝ ሌላ ቦታ ከማከናወን ይልቅ ወደ ቅፍርናሆም የሄደው ለምንድን ነው? አንደኛ ቅፍርናሆም አማካይ ቦታ ላይ የምትገኝ ትልቅ ከተማ ነች። በተጨማሪም አብዛኞቹ የኢየሱስ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት በቅፍርናሆም ውስጥ ወይም በአቅራቢያዋ የሚኖሩ ናቸው። ስለዚህ ከኢየሱስ ሥልጠና ለማግኘት መኖሪያቸውን ለቅቀው መሄድ አላስፈለጋቸውም።

ኢየሱስ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ራሱም እንደመሰከረው በቅፍርናሆም በቆየባቸው ጊዜያት አስደናቂ ነገሮችን ፈጽሟል። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስና ጓደኞቹ እንደገና መጓዝ ጀመሩ። ወቅቱ የጸደይ ወራት ሲሆን በ30 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በሚከበረው የማለፍ በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ ነው። እዚያም ሳሉ በኢየሱስ ላይ ምናልባት ከዚህ ቀደም አይተውት የማያውቁትን ነገር አዩ።

የአምላክ ሕግ በሚያዘው መሠረት እስራኤላውያን የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር። ስለዚህ አመቺ እንዲሆንላቸው በኢየሩሳሌም የነበሩ ነጋዴዎች ለዚህ ዓላማ የሚያገለግሉ እንስሳትንና ርግቦችን ይሸጡ ነበር። ሆኖም ይሸጡ የነበረው ቤተ መቅደሱ ውስጥ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ዋጋ በማስከፈል ሕዝቡን ያጭበረብሩ ነበር።

ኢየሱስ በጣም በመናደዱ የገመድ ጅራፍ አበጀና ሻጮቹን አባረራቸው። የገንዘብ ለዋጮቹን ሳንቲሞች አፈሰሰ፤ ጠረጴዛዎቻቸውንም ገለባበጠ። ድምፁንም ከፍ አድርጎ ርግብ ሻጮቹን “ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት” አላቸው።

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን ሲመለከቱ ስለ አምላክ ልጅ የተጻፈውን “የቤትህ ቅናት ይበላኛል” የሚለውን ትንቢት አስታወሱ። ሆኖም አይሁዶች “ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፣ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ” ሲል መለሰላቸው።

አይሁዳውያን ኢየሱስ ቃል በቃል ስለ ቤተ መቅደሱ የተናገረ መስሏቸው “ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን?” አሉ። ኢየሱስ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ መናገሩ ነበር። ሦስት ዓመት ካለፈ በኋላ ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ ደቀ መዛሙርቱ ይህን የተናገረውን ቃል አስታወሱ። ዮሐንስ 2:​12-22፤ ማቴዎስ 13:​55፤ ሉቃስ 4:​23

▪ ኢየሱስ በቃና በተደረገው ሠርግ ላይ ከተገኘ በኋላ የት የት ቦታዎች ሄደ?

▪ ኢየሱስ የተናደደው ለምን ነበር? ምንስ አደረገ?

▪ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያደረገውን ነገር ሲመለከቱ ምን አስታወሱ?

▪ ኢየሱስ “ይህን ቤተ መቅደስ” ምን አደርገዋለሁ አለ? ምን ማለቱስ ነበር?