በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልብሱን ነካች

ልብሱን ነካች

ምዕራፍ 46

ልብሱን ነካች

ኢየሱስ ከዲካፖሊስ እንደተመለሰ የሚገልጽ ወሬ በቅፍርናሆም ተዳረሰ። ኢየሱስን ለመቀበል ብዙ ሕዝብ በባሕሩ ዳርቻ ተሰበሰበ። ማዕበሉን ጸጥ ማሰኘቱንና አጋንንት የያዟቸውን ሰዎች መፈወሱን እንደሰሙ ጥርጥር የለውም። አሁን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሲመጣ በከፍተኛ ጉጉት ዙሪያውን ከበቡት።

የምኩራብ አለቃ የሆነው ኢያኢሮስ ኢየሱስን ለማግኘት ጓጉተው ከነበሩት ሰዎች አንዱ ነበር። በኢየሱስ እግር ላይ ወደቀና “ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት ብሎ አጥብቆ ለመነው።” ልጅቷ ብቸኛ ልጁ ስለነበረችና ገና የ12 ዓመት ልጅ ስለነበረች ለኢያኢሮስ በጣም ውድ ነበረች።

ኢየሱስ ልመናውን ተቀበለና በሕዝቡ ታጅቦ ወደ ኢያኢሮስ ቤት መሄድ ጀመረ። ሰዎቹ ሌላ ተአምር ሊያዩ በመሆኑ ምን ያህል እንደተደሰቱ መገመት እንችላለን። ሆኖም በሕዝቡ መካከል የነበረች አንዲት ሴት ትኩረት አድርጋ የነበረው ራሷ ባለባት ከባድ ችግር ላይ ነበር።

ይህች ሴት ለ12 ዓመታት ያህል ደም ይፈሳት ነበር። ከአንዱ ሐኪም ወደ ሌላው እየሄደች ለሕክምና ብዙ ገንዘብ አውጥታለች። ሆኖም ምንም እርዳታ አላገኘችም፤ ከዚህ ይልቅ ችግሯ ይበልጥ ተባብሶ ነበር።

በሽታዋ በጣም ያዳከማት ከመሆኑም በላይ አሳፋሪና የሚያዋርድ በሽታ እንደነበር መገመት አያቅትህም። ስለ እንዲህ ዓይነቱ ሥቃይ በሕዝብ ፊት አይወራም ነበር። ከዚህም በላይ በሙሴ ሕግ መሠረት ደም የሚፈሳት ሴት ርኩስ ትሆን ነበር፤ እሷን ወይም በደም የተበከለ ልብስዋን የነካ ሰው ደግሞ መታጠብ ይኖርበታል። እስከ ማታ ድረስም ርኩስ ሆኖ ይቆያል።

ሴትየዋ ኢየሱስ ስለፈጸማቸው ተአምራት ሰምታ ስለነበር አሁን ፈልጋ አገኘችው። “ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ” ብላ በልቧ በማሰብ ርኩስ ስለነበረች በተቻለ መጠን ቀስ ብላ ማንም ልብ ሳይላት በሕዝቡ መካከል አልፋ ሄደች። ልብሱን ስትነካ ወዲያውኑ ይፈሳት የነበረው ደም ሲደርቅ ተሰማት!

“የዳሰሰኝ ማን ነው?” ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ምንኛ አስደንግጠዋት ይሆን! እንዴት ሊያውቅ ቻለ? ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ተከራከረ:- ‘መምህር ሆይ፣ ሕዝቡ ሁሉ እያስጨነቁህና እየገፉህ ነው፤ የዳሰሰኝ ማን ነው ትላለህን?’

ኢየሱስ ዞር ብሎ ሴትዮዋን እየፈለገ “አንድ ሰው ዳስሶኛል፣ ኃይል ከእኔ እንደ ወጣ አውቃለሁና” አለ። ሴትዮዋ ፈውስ ያገኘችው ከኢየሱስ በወጣው ኃይል በመሆኑ በእርግጥም ኢየሱስ በዚህ ጊዜ የተዳሰሰው በተለመደ ሁኔታ አልነበረም።

ሴትዮዋ ልትሰወር እንዳልቻለች ስታውቅ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች መጣችና ኢየሱስ ፊት ተደፋች። በሰዉ ሁሉ ፊት ስለ በሽታዋ አንድ በአንድ እውነቱን ከተናገረች በኋላ አሁን እንዴት እንደተፈወሰች ገለጸች።

ኢየሱስ ሁሉን ነገር ግልጽልጽ አድርጋ በመናዘዟ ልቡ ተነካና በርኅራኄ መንፈስ እንዲህ ሲል አጽናናት:- “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ።” አምላክ ምድርን እንዲገዛ የመረጠው ሰው ለሰዎች የሚያስብና እነርሱን ለመርዳት የሚያስችል ኃይል ያለው፣ አፍቃሪና ሩኅሩኅ መሆኑን ማወቁ እንዴት ግሩም ነው! ማቴዎስ 9:​18-22፤ ማርቆስ 5:​21-34፤ ሉቃስ 8:​40-48፤ ዘሌዋውያን 15:​25-27

▪ ኢያኢሮስ ማን ነው? ወደ ኢየሱስ የመጣውስ ለምንድን ነው?

▪ አንዲት ሴት ምን ችግር ነበራት? የኢየሱስን እርዳታ ለማግኘት መምጣት ለእሷ በጣም አስቸጋሪ የነበረው ለምንድን ነው?

▪ ሴትዮዋ የተፈወሰችው እንዴት ነው? ኢየሱስ ያጽናናትስ እንዴት ነው?