በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐዋርያቱን ከእነርሱ ለሚለይበት ጊዜ አዘጋጃቸው

ሐዋርያቱን ከእነርሱ ለሚለይበት ጊዜ አዘጋጃቸው

ምዕራፍ 116

ሐዋርያቱን ከእነርሱ ለሚለይበት ጊዜ አዘጋጃቸው

የመታሰቢያው እራት ያበቃ ቢሆንም ኢየሱስና ሐዋርያቱ አሁንም ያሉት ደርብ ላይ በሚገኘው ክፍል ውስጥ ነው። ምንም እንኳ ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሚለያቸው ቢሆንም ብዙ የሚነግራቸው ነገር ነበረው። “ልባችሁ አይታወክ፤” ሲል አጽናናቸው። “በእግዚአብሔር እመኑ።” አክሎም “በእኔም ደግሞ እመኑ” ሲል ተናገረ።

“በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤” በማለት ኢየሱስ ንግግሩን ቀጠለ። “ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ . . . እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ . . . ወደምሄድበትም ታውቃላችሁ፣ መንገዱንም ታውቃላችሁ።” ሐዋርያቱ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ስለ መሄድ እየተናገረ እንዳለ አልገባቸውም፤ ስለዚህ ቶማስ “ጌታ ሆይ፣ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን?” ሲል ጠየቀው።

“እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” ሲል ኢየሱስ መለሰ። አዎን፣ ማንኛውም ሰው ወደ አብ ሰማያዊ ቤት ሊገባ የሚችለው ኢየሱስን በመቀበልና አኗኗሩን በመኮረጅ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሏል።

ፊልጶስ “ጌታ ሆይ፣ አብን አሳየንና ይበቃናል” ሲል ጠየቀው። ፊልጶስ ጥንት ለእነ ሙሴ፣ ኤልያስና ኢሳይያስ በራእይ እንደተገለጠላቸው ዓይነት የአምላክን የሚታይ መግለጫ እንዲያሳየው የፈለገ ይመስላል። ሆኖም ሐዋርያት ከእንዲህ ዓይነቶቹ ራእዮች የበለጠ አጋጣሚ ነበራቸው፤ ኢየሱስ ይህን እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “አንተ ፊልጶስ፣ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል።”

ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባረቀ በመሆኑ ከእሱ ጋር መኖርና እሱን መመልከት አብን እንደ መመልከት የሚቆጠር ነበር። ሆኖም ኢየሱስ “እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም” በማለት እንደገለጸው አብ ከወልድ ይበልጣል። ኢየሱስ ትምህርቱ ሁሉ ከሰማያዊ አባቱ የመነጨ እንደሆነ በመግለጽ ክብሩን ለአባቱ መስጠቱ ተገቢ ነበር።

ሐዋርያቱ ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ ሲነግራቸው ምንኛ ተበረታተው ይሆን:- “በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል”! ኢየሱስ ተከታዮቹ እሱ ካከናወናቸው ተአምራት የላቁ ተአምራት ይፈጽማሉ ማለቱ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአገልግሎቱን ሥራ ከእሱ በበለጠ ለረጅም ጊዜ፣ በጣም ሰፊ በሆነ ክልል ለብዙ ሰዎች ያከናውናሉ ማለቱ ነው።

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ከተለየ በኋላ አይተዋቸውም። “በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ” ሲል ቃል ገባላቸው። በተጨማሪም እንዲህ አላቸው:- “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ [“ረዳት፣” NW] ይሰጣችኋል፤ እርሱም . . . የእውነት መንፈስ ነው።” ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ይህን ሌላ ረዳት ማለትም መንፈስ ቅዱስን በደቀ መዛሙርቱ ላይ ያፈስስላቸዋል።

ኢየሱስ “ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዓለም አያየኝም” ሲል እንደገለጸው ከእነርሱ የሚለይበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። (የ1980 ትርጉም) ኢየሱስ ማንም ሰው ሊያየው የማይችል መንፈሳዊ ፍጡር ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስ እንደገና “እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ” በማለት ለታማኝ ሐዋርያቱ ቃል ገባላቸው። አዎን፣ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለእነርሱ ሰብዓዊ አካል ለብሶ የሚታይ ከመሆኑም በላይ ከጊዜ በኋላ ከሞት አስነስቶ መንፈሳዊ ፍጡራን ሆነው በሰማይ ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል።

ኢየሱስ በመቀጠል የሚከተለውን ቀላል ደንብ ሰጠ:- “ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።”

በዚህ ጊዜ ታዴዎስ እየተባለም የሚጠራው ሐዋርያው ይሁዳ ንግግሩን አቋረጠውና “ጌታ ሆይ፣ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ ልትገልጥ ያለህ እንዴት ነው?” ሲል ጠየቀው።

ኢየሱስ “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል . . . የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም” ሲል መለሰለት። ዓለም ታዛዥ ከሆኑት የኢየሱስ ተከታዮቹ የተለየ ነው፤ የክርስቶስን ትምህርቶች ወደ ጎን ገሸሽ ያደርጋል። ስለዚህ ኢየሱስ ራሱን ለዓለም አይገልጥም።

ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ሐዋርያቱን ብዙ ነገር አስተምሯቸዋል። እስከዚህ ወቅት ድረስ እንኳ ብዙ ነገር መረዳት የተሳናቸው በመሆኑ የተማሩትን ሁሉ እንዴት ሊያስታውሱት ይችላሉ? ኢየሱስ እንዲህ ሲል ቃል የገባላቸው መሆኑ የሚያስደስት ነው:- “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ [“ረዳት፣” NW] እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።”

ኢየሱስ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ . . . ልባችሁ አይታወክ” በማለት በድጋሚ አጽናናቸው። እርግጥ ኢየሱስ ሊለያቸው ነው፤ ሆኖም ኢየሱስ “የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር” ሲል ገልጿል።

ኢየሱስ ከዚህ በኋላ ከእነርሱ ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ አጭር ነው። “ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም” አላቸው፤ “የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም [“በእኔ ላይ ምንም ማድረግ አይችልም፣” የ1980 ትርጉም]።” የዚህ ዓለም ገዥ የተባለው ይሁዳ ውስጥ መግባትና እርሱን መቆጣጠር የቻለው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ሆኖም ኢየሱስ አምላክን ማገልገሉን እንዲያቆም ለማድረግ ሰይጣን እንደ መሣሪያ አድርጎ ሊጠቀምበት የሚችል የኃጢአት ድክመት የለበትም።

የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት

ኢየሱስ ከመታሰቢያው እራት በኋላ ከሐዋርያቱ ጋር ዘና ባለ መንገድ ልብ ለልብ በመወያየት ሲያበረታታቸው ቆይቷል። አሁን እኩለ ሌሊት ሳያልፍ አይቀርም። ስለዚህ ኢየሱስ “ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ” አላቸው። ይሁን እንጂ ከመሄዳቸው በፊት ኢየሱስ ለእነሱ ባለው ፍቅር ተገፋፍቶ አንድ ቀስቃሽ የሆነ ምሳሌ በመስጠት መናገሩን ቀጠለ።

ኢየሱስ “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው” በማለት ምሳሌውን መናገር ጀመረ። ታላቁ ገበሬ ይሖዋ አምላክ ይህን ምሳሌያዊ ወይን የተከለው ኢየሱስ በ29 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የመከር ወራት ሲጠመቅ በመንፈስ ቅዱስ በቀባው ጊዜ ነው። ሆኖም ኢየሱስ በመቀጠል ወይኑ የሚያመለክተው እሱን ብቻ አለመሆኑን እንዲህ ሲል ገለጸ:- “ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል። . . . ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፣ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ።”

ሐዋርያቱና ሌሎች ሰዎች ከ51 ቀናት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በወረደባቸው ጊዜ የወይኑ ቅርንጫፎች ሆነዋል። በመጨረሻ 144,000 ሰዎች የምሳሌያዊው ወይን ቅርንጫፎች ይሆናሉ። እነዚህ ሰዎች ከወይኑ ግንድ ማለትም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ ላይ ሆነው የአምላክን መንግሥት ፍሬዎች የሚያፈራ ምሳሌያዊ ወይን ይሆናሉ።

ኢየሱስ “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል” በማለት ፍሬ ለማፍራት ቁልፉ ምን እንደሆነ ገልጿል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ፍሬ ካላፈራ “እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፣ ያቃጥሉአቸውማል” ሲል ኢየሱስ ተናግሯል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል:- “በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል።”

በተጨማሪም ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እንዲህ አለ:- “ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል።” አምላክ ከቅርንጫፎቹ የሚፈልገው ፍሬ የክርስቶስን ዓይነት ባሕርያት በተለይም ፍቅር ማሳየታቸውን ነው። ከዚህም በተጨማሪ ክርስቶስ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪ እንደነበረ ሁሉ ከእነርሱ የሚፈለገው ፍሬ እሱ እንዳደረገው ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መሳተፍ ይጠይቅባቸዋል።

ኢየሱስ በመቀጠል “በፍቅሬ ኑሩ” ሲል አጥብቆ አሳሰበ። ሆኖም ሐዋርያቱ ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? “ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ” ሲል ተናገረ። ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።”

ኢየሱስ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሕይወቱን ለሐዋርያቱና በእሱ ለሚያምኑ ሌሎች ሰዎች በሙሉ አሳልፎ በመስጠት ይህን ከሁሉ የላቀ ፍቅር ያሳያል። የእሱ ምሳሌ ተከታዮቹ ይህን የራስን ጥቅም በመሠዋት የሚገለጽ ፍቅር አንዳቸው ለሌላው እንዲያሳዩ ሊገፋፋቸው ይገባል። ቀደም ሲል ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” በማለት እንደገለጸው ይህ ፍቅር ማንነታቸውን ለይቶ ያሳውቃል።

ኢየሱስ ወዳጆቹን ለይቶ በመግለጽ እንዲህ አለ:- “እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፣ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።”

የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች መሆን እንዴት ያለ ውድ ዝምድና ነው! ሆኖም ተከታዮቹ ይህን ዝምድና እንደያዙ ለመቀጠል እንዲችሉ ‘ፍሬ ማፍራታቸውን መቀጠል’ አለባቸው። ኢየሱስ ፍሬ ማፍራታቸውን ከቀጠሉ ‘አብ በስሙ የለመኑትን ሁሉ እንደሚሰጣቸው’ ተናግሯል። በእርግጥም ይህ የመንግሥቱን ፍሬ በማፍራት የሚገኝ ታላቅ ወሮታ ነው! ኢየሱስ ሐዋርያቱ ‘እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ’ በድጋሚ አጥብቆ ካሳሰባቸው በኋላ ዓለም እንደሚጠላቸው ገለጸ። ሆኖም “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ” በማለት አጽናናቸው። ኢየሱስ በመቀጠል ዓለም ተከታዮቹን ለምን እንደሚጠላቸው ሲገልጽ “እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል” ብሏል።

ኢየሱስ ዓለም እነርሱን የሚጠላበትን ምክንያት ይበልጥ በማብራራት እንዲህ ሲል መናገሩን ቀጠለ:- “የላከኝን [ይሖዋ አምላክን] አያውቁምና ይህን ሁሉ ስለ ስሜ ያደርጉባችኋል።” ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት በገለጸው መሠረት የፈጸማቸው ተአምራት እርሱን የሚጠሉትን ሰዎች ጥፋተኛ ሆነው እንዲቆጠሩ ያደርጓቸዋል:- “ሌላ ሰው ያላደረገውን ሥራ በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ይህን ሁሉ ካዩ በኋላ እኔንም አባቴንም ጠልተዋል።” (የ1980 ትርጉም) ስለዚህ ኢየሱስ እንደተናገረው “በከንቱ ጠሉኝ” የሚለው ጥቅስ ተፈጽሟል።

ኢየሱስ ቀደም ሲል እንዳደረገው አሁንም ረዳት የሆነውን የአምላክን ከፍተኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ማለትም መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ቃል በመግባት አጽናናቸው። “እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተም ደግሞ . . . ትመሰክራላችሁ” አላቸው።

ተጨማሪ የስንብት ማሳሰቢያ

ኢየሱስና ሐዋርያቱ ደርብ ላይ ከሚገኘው ክፍል ወጥተው ለመሄድ ተዘጋጅተዋል። “እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬአችኋለሁ” በማለት ኢየሱስ መናገሩን ቀጠለ። ከዚያም የሚከተለውን ከበድ ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው:- “ከምኵራባቸው ያወጡአችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል።”

ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ሐዋርያቱ በዚህ ማስጠንቀቂያ በጣም ተረብሸዋል። ምንም እንኳ ኢየሱስ ዓለም እንደሚጠላቸው ቀደም ሲል የነገራቸው ቢሆንም ሊገደሉ እንደሚችሉ በቀጥታ አልገለጸላቸውም ነበር። “ከእናንተም ጋር ስለ ነበርሁ በመጀመሪያ ይህን አልነገርኋችሁም” ሲል ኢየሱስ ገለጸ። ሆኖም ከእነርሱ ከመለየቱ በፊት ይህን መረጃ በመስጠት አስቀድመው እንዲዘጋጁ ማድረጉ እንዴት ጥሩ ነው!

“አሁን ግን” በማለት ኢየሱስ መናገሩን ቀጠለ፤ “ወደ ላከኝ እሄዳለሁ ከእናንተም:- ወዴት ትሄዳለህ? ብሎ የሚጠይቀኝ የለም።” ቀደም ሲል በዚያው ምሽት የሚሄድበትን ቦታ በተመለከተ ጥያቄ አቅርበው ነበር፤ ሆኖም አሁን በነገራቸው ነገር በጣም ስለደነገጡ ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ ጥያቄ አላቀረቡም። ኢየሱስ “ይህን ስለ ተናገርኋችሁ ኀዘን በልባችሁ ሞልቶአል” አለ። ሐዋርያቱ ያዘኑት ከባድ ስደት እንደሚደርስባቸውና እንደሚገደሉ ስላወቁ ብቻ ሳይሆን ጌታቸውም ከእነርሱ ሊለይ በመሆኑ ነው።

ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸ:- “እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ [“ረዳቱ፣” NW] ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።” ኢየሱስ ሰው በነበረበት ጊዜ በአንድ ጊዜ ከአንድ ቦታ በላይ መሆን አይችልም፤ ሆኖም ወደ ሰማይ ሲሄድ ተከታዮቹ በየትኛውም የምድር ክፍል ቢሆኑ ረዳት የሆነውን የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ሊልክላቸው ይችላል። ስለዚህ የኢየሱስ መሄድ ጠቃሚ ነው።

ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ “ስለ ኃጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ለዓለም አሳማኝ ማስረጃ ያቀርባል” ሲል ተናገረ። (NW) የዓለም ኃጢአት ማለትም በአምላክ ልጅ አለማመኑ ይጋለጣል። በተጨማሪም ኢየሱስ ወደ አባቱ ሲያርግ የኢየሱስ ጽድቅ አሳማኝ ማስረጃ ይታያል። ሰይጣንና የእሱ ክፉ ዓለም የኢየሱስን የጸና አቋም ለማስለወጥ አለመቻላቸው የዓለም ገዥ እንደተፈረደበት የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ነው።

ኢየሱስ በመቀጠል “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ” ሲል ተናገረ፤ “ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም” አላቸው። ስለዚህ ኢየሱስ የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል የሆነውን መንፈስ ቅዱስ በሚያፈስበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች መረዳት የሚችሉትን ያህል ማስተዋል እንዲችሉ እንደሚያደርጋቸው ቃል ገባላቸው።

ሐዋርያቱ በተለይ ኢየሱስ እንደሚሞትና ከዚያም ከሞት ከተነሣ በኋላ እንደሚገለጥላቸው አልተረዱም። ስለዚህ እርስ በርሳቸው እንዲህ ሲሉ ተጠያየቁ:- “ጥቂት ጊዜ አለ፣ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፣ ታዩኛላችሁም፤ ደግሞ:- ወደ አብ እሄዳለሁና የሚለን ይህ ምንድር ነው?”

ኢየሱስ ሊጠይቁት እንደፈለጉ ስለተረዳ እንዲህ ሲል ገለጸላቸው:- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ እናንተ ታለቅሳላችሁ ሙሾም ታወጣላችሁ፣ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተም ታዝናላችሁ፣ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።” በዚያው ቀን ከሰዓት በኋላ ኢየሱስ ሲገደል ዓለማዊዎቹ የሃይማኖት መሪዎቹ ደስ ይላቸዋል፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ያዝናሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ ሐዘናቸው ወደ ደስታ ይለወጣል! በተጨማሪም ምሥክሮቹ እንዲሆኑ በጰንጠቆስጤ ዕለት የአምላክን ቅዱስ መንፈስ በእነርሱ ላይ በማፍሰስ ኃይል ሲሰጣቸው ደስታቸው ይቀጥላል!

ኢየሱስ የሐዋርያቱን ሁኔታ በምጥ ላይ ካለች ሴት ሁኔታ ጋር በማነጻጸር “ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራትዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች” ሲል ተናገረ። ሆኖም ኢየሱስ አንዴ ልጅዋን ከወለደች በኋላ መከራዋን እንደማታስታውሰው በመግለጽ ሐዋርያቱን እንዲህ ሲል አበረታታቸው:- “እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን [ከሞት ስነሳ] እንደ ገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል፣ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።”

ሐዋርያቱ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በኢየሱስ ስም ልመና አላቀረቡም። አሁን ግን እንዲህ አላቸው:- “አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። . . . እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና። ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ።”

የኢየሱስ ቃላት ለሐዋርያቱ ትልቅ ማበረታቻ ናቸው። “ስለዚህ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን” አሉት። “አሁን ታምናላችሁን?” ሲል ኢየሱስ ጠየቃቸው። “እነሆ፣ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤት የምትበታተኑበት እኔንም ለብቻዬ የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፣ አሁንም ደርሶአል።” ሁኔታው ለማመን የሚያስቸግር ቢመስልም ሌሊቱ ገና ሳይገባደድ ይህ ነገር ተፈጽሟል!

“በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ።” ኢየሱስ እንዲህ ሲል ደመደመ:- “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” ኢየሱስ፣ ሰይጣንና የሰይጣን ዓለም የያዘውን የጸና አቋም ለማስለወጥ ያደረጉትን ሙከራ ሁሉ ተቋቁሞ በታማኝነት የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ዓለምን አሸንፏል።

ደርብ ላይ በሚገኘው ክፍል የተደረገ የመደምደሚያ ጸሎት

ኢየሱስ ለሐዋርያቱ በነበረው የጠለቀ ፍቅር በመገፋፋት በጣም እየተቃረበ ላለው ከእነርሱ ለሚለይበት ጊዜ እያዘጋጃቸው ነበር። አሁን ረዘም ላለ ጊዜ አጥብቆ ሲመክራቸውና ሲያጽናናቸው ከቆየ በኋላ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ የሚከተለውን ልመና ለአባቱ አቀረበ:- “ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፣ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፣ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው።”

ኢየሱስ ያስተዋወቀው የዘላለም ሕይወት የሚለው ጭብጥ ምንኛ ስሜት ቀስቃሽ ነው! ኢየሱስ ‘በሥጋ ሁሉ ላይ ሥልጣን የተሰጠው’ በመሆኑ የቤዛዊ መሥዋዕቱን ጥቅሞች ሟች ለሆኑት የሰው ልጆች በሙሉ መስጠት ይችላል። ሆኖም “የዘላለምን ሕይወት” የሚሰጠው በአብ ዘንድ ተቀባይነት ላገኙት ብቻ ነው። ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት በሚለው በዚህ ጭብጥ ላይ በመመርኮዝ ጸሎቱን ቀጠለ:-

“እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” አዎን፣ መዳናችን አምላክንና ልጁን በማወቃችን ላይ የተመካ ነው። ሆኖም ከጭንቅላት እውቀት የበለጠ ነገርም ይፈለጋል።

አንድ ሰው ከእነርሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት በመመሥረት በቅርብ ሊያውቃቸው ይገባል። አንድ ሰው ለነገሮች ያለው አመለካከት እነርሱ ካላቸው አመለካከት ጋር አንድ መሆን አለበት፤ በተጨማሪም ማንኛውንም ነገር በእነርሱ ዓይን መመልከት ይኖርበታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ ሰው ከሌሎች ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ተወዳዳሪ የማይገኝላቸውን የይሖዋንና የኢየሱስን ባሕርያት ለመኮረጅ መጣር አለበት።

ኢየሱስ በመቀጠል “እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ” ሲል ጸለየ። እስከዚህ ደረጃ ድረስ ያለውን ሥራውን በመፈጸሙና የተቀረውም እንደሚሳካለት በመተማመን “አባት ሆይ፣ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ” የሚል ልመና አቀረበ። አዎን፣ በትንሣኤ አማካኝነት ቀድሞ ወደነበረው ሰማያዊ ክብር ለመመለስ መጠየቁ ነበር።

ኢየሱስ በምድር ላይ ያከናወነውን ዋነኛ ሥራ ጠቅለል አድርጎ በመግለጽ እንዲህ አለ:- “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል።” ኢየሱስ፣ ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም በአገልግሎቱ ከመጠቀሙም በላይ የስሙን ትክክለኛ አጠራር አሳይቷል። ሆኖም የአምላክን ስም ለሐዋርያቱ ለመግለጽ ከዚህም የበለጠ ነገር አድርጓል። ስለ ይሖዋ፣ ስለ ባሕርያቱና ስለ ዓላማዎቹ ያላቸውን እውቀትና ግንዛቤ አስፍቶላቸዋል።

ኢየሱስ እሱ ከበታቹ ሆኖ የሚያገለግለውን ይሖዋን የበላዩ አድርጎ ክብር በመስጠት እንዲህ ሲል በትሕትና ተናግሯል:- “የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፣ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፣ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ።”

ኢየሱስ በተከታዮቹና በተቀረው የሰው ዘር መካከል ልዩነት እንዳለ በመግለጽ እንዲህ ሲል ጸለየ:- “ስለ ዓለም አልለምንም ስለ ሰጠኸኝ እንጂ፤ . . . ከእነርሱ ጋር በዓለም ሳለሁ . . . እኔ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም . . . ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም፤” እርሱም የአስቆሮቱ ይሁዳ ነው። በዚህ ወቅት ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ርካሽ የሆነ ተልዕኮውን እያከናወነ ነበር። በዚህ መንገድ ይሁዳ ሳያውቀው ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲፈጸሙ እያደረገ ነበር።

“ዓለም ጠላቸው” በማለት ኢየሱስ ጸሎቱን ቀጠለ። “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም።” የኢየሱስ ተከታዮች በዓለም ውስጥ ማለትም በሰይጣን በሚገዛው የተደራጀ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ውስጥ ናቸው። ሆኖም የኢየሱስ ተከታዮች ምን ጊዜም ከዚህ ዓለምና ከክፋቱ ራሳቸውን ገለልተኞች ያደርጋሉ፤ ማድረግም አለባቸው።

“በእውነትህ ቀድሳቸው” በማለት ኢየሱስ ቀጠለ፤ “ቃልህ እውነት ነው።” ኢየሱስ ብዙ ጊዜ የሚጠቅሳቸውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች እዚህ ላይ “እውነት” ብሎ ጠርቷቸዋል። ሆኖም እሱ ደቀ መዛሙርቱን ያስተማራቸው ትምህርቶችና ከጊዜ በኋላ በመንፈስ አነሳሽነት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች አድርገው የጻፋቸው ጽሑፎችም “እውነት” ናቸው። ይህ እውነት አንድን ሰው መቀደስ፣ ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ መለወጥና ከዓለም የተለየ ሰው ማድረግ ይችላል።

አሁን ኢየሱስ ‘ስለ እነዚህ ብቻ ሳይሆን በእነርሱ ቃል አማካኝነት በእሱ ስለሚያምኑ ሰዎችም ጭምር’ ጸለየ። ስለዚህ ኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮቹ ስለሚሆኑትና ወደፊት ወደ ‘አንዱ መንጋ’ ተሰብስበው ደቀ መዛሙርቱ ስለሚሆኑት ሌሎች ሰዎች ጸልዮአል። ለእነዚህ ሁሉ ሰዎች የጠየቀው ነገር ምንድን ነው?

“አንተ፣ አባት ሆይ፣ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፣ . . . አንድ ይሆኑ ዘንድ . . . እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ።” ኢየሱስና አባቱ ቃል በቃል አንድ አካል አይደሉም፤ ሆኖም በሁሉም ነገሮች ስምም ናቸው። ኢየሱስ “ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው” ያውቅ ዘንድ ተከታዮቹ ይህን አንድነት እንዲያገኙ ጸልዮአል።

ኢየሱስ ወደፊት ቅቡዓን ተከታዮቹ ስለሚሆኑት ሰዎች ለሰማያዊ አባቱ ልመና አቀረበ። ያቀረበው ልመና ምንድን ነው? “ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት . . . እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ” ሲል ልመና አቅርቧል። ዓለም ሳይፈጠር ሲል አዳምና ሔዋን ልጅ ከመውለዳቸው በፊት ማለቱ ነበር። ይህ ከመሆኑ ከረጅም ጊዜ በፊት አምላክ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነውን አንድያ ልጁን ወዶታል።

ኢየሱስ ጸሎቱን ሲደመድም እንዲህ በማለት በድጋሚ ጠበቅ አድርጎ ገለጸ:- “እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፣ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ።” የአምላክን ስም ማወቅ ሲባል ሐዋርያቱ በግለሰብ ደረጃ የአምላክን ፍቅር ማወቅ ይጠይቅባቸው ነበር ማለት ነው። ዮሐንስ 14:​1 እስከ 17:​26፤ 13:​27, 35, 36፤ 10:​16፤ ሉቃስ 22:​3, 4፤ ዘጸአት 24:​10፤ 1 ነገሥት 19:​9-13፤ ኢሳይያስ 6:​1-5፤ ገላትያ 6:​16፤ መዝሙር 35:​19፤ 69:​4፤ ምሳሌ 8:​22, 30

▪ ኢየሱስ የሚሄደው ወዴት ነው? ወደዚያ ቦታ ስለሚኬድበት መንገድስ ቶማስ የተሰጠው መልስ ምንድን ነው?

▪ ፊልጶስ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ኢየሱስ ምን እንዲያደርግለት ፈልጎ የነበረ ይመስላል?

▪ ኢየሱስን ያየ አብንም አይቷል የሚባለው ለምንድን ነው?

▪ የኢየሱስ ተከታዮች እሱ ካከናወነው ሥራ የበለጠ የሚያከናውኑት እንዴት ነው?

▪ ሰይጣን በኢየሱስ ላይ ምንም ማድረግ የማይችለው ከምን አንጻር ነው?

▪ ይሖዋ ምሳሌያዊውን ወይን የተከለው መቼ ነው? ሌሎች የወይኑ ክፍል የሆኑት መቼና እንዴት ነው?

▪ በመጨረሻ ምሳሌያዊው ወይን ምን ያህል ቅርንጫፎች ይኖሩታል?

▪ አምላክ ከቅርንጫፎቹ ምን ዓይነት ፍሬ ይፈልጋል?

▪ የኢየሱስ ወዳጆች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

▪ ዓለም የኢየሱስን ተከታዮች የሚጠላቸው ለምንድን ነው?

▪ ሐዋርያቱን የረበሻቸው የትኛው የኢየሱስ ማስጠንቀቂያ ነው?

▪ ሐዋርያቱ ኢየሱስ ወዴት እንደሚሄድ ሳይጠይቁት የቀሩት ለምንድን ነው?

▪ ሐዋርያቱ በተለይ ያልተረዱት ነገር ምን ነበር?

▪ ኢየሱስ የሐዋርያቱ ሁኔታ ከሐዘን ወደ ደስታ እንደሚለወጥ በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ሐዋርያቱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ምን እንደሚያደርጉ ተናግሯል?

▪ ኢየሱስ ዓለምን ያሸነፈው እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ “በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን” የተሰጠው በምን መንገድ ነው?

▪ አምላክንና ልጁን ማወቅ ማለት ምን ማለት ነው?

▪ ኢየሱስ የአምላክን ስም የገለጠው በምን መንገዶች ነው?

▪ “እውነት” ምንድን ነው? አንድን ክርስቲያን ‘የሚቀድሰውስ’ እንዴት ነው?

▪ አምላክ፣ ልጁና እውነተኛ አምላኪዎች በሙሉ አንድ የሆኑት እንዴት ነው?

▪ “ዓለም ሳይፈጠር” የሚለው አነጋገር የሚያመለክተው የትኛውን ጊዜ ነው?