በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንገድ ጠራጊው ተወለደ

መንገድ ጠራጊው ተወለደ

ምዕራፍ 3

መንገድ ጠራጊው ተወለደ

ኤልሳቤጥ ልጅዋን የምትወልድበት ጊዜ ደርሷል። ላለፉት ሦስት ወራት ማርያም እሷ ጋር ቆይታለች። አሁን ግን ማርያም ተሰናብታ ናዝሬት ወደሚገኘው መኖሪያዋ ለመመለስ ረጅሙን ጉዞ የምትያያዝበት ጊዜ ደረሰ። እሷም በስድስት ወር ውስጥ ልጅ ትወልዳለች።

ማርያም ከሄደች በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኤልሳቤጥ ወለደች። ልጁን በተሳካ ሁኔታ መገላገሏና የኤልሳቤጥም ሆነ የሕፃኑ ጤንነት በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑ ምንኛ አስደስቷቸው ይሆን! ኤልሳቤጥ ሕፃኑን ለጎረቤቶቿና ለዘመዶቿ ስታሳያቸው እነሱም ተደሰቱ።

በአምላክ ሕግ መሠረት በእስራኤል የሚወለድ አንድ ወንድ ልጅ በተወለደ በስምንተኛው ቀን መገረዝ ነበረበት። በዚህ ጊዜ ወዳጅ ዘመዶች ለመጠየቅ መጡ። ልጁ ልክ እንደ አባቱ ዘካርያስ ተብሎ እንዲጠራ ሐሳብ አቀረቡ። ሆኖም ኤልሳቤጥ በነገሩ አልተስማማችም። “አይሆንም፣ ዮሐንስ ይባል” አለች። መልአኩ ገብርኤል ለልጁ መሰጠት አለበት ያለው ስም ይህ ስም እንደሆነ አስታውስ።

ይሁን እንጂ ወዳጆቻቸው “ከወገንሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም” ሲሉ ተቃወሙ። ከዚያም በምልክት ቋንቋ በመጠቀም አባቱ ልጁ ማን ተብሎ እንዲጠራ እንደሚፈልግ ጠየቁት። ዘካርያስ ብራና እንዲሰጡት ጠየቀና “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ሲጽፍ ሁሉም ተደነቁ።

በዚህ ጊዜ ዘካርያስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንደገና መናገር ቻለ። ዘካርያስ የመናገር ችሎታውን ያጣው መልአኩ ኤልሳቤጥ ልጅ ትወልዳለች ብሎ ሲነግረው ባለማመኑ ምክንያት እንደነበረ ታስታውሳለህ። ዘካርያስ መናገር ሲጀምር ጎረቤቶቹ ሁሉ ተገርመው “ይህ ሕፃን ምን ይሆን?” ብለው አሰቡ።

ከዚያ በኋላ ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ደስታውን ገለጸ:- “የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፣ ጎብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ . . . በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነሥቶልናል።” ይህ “የመዳን ቀንድ” በወቅቱ ገና ያልተወለደው ጌታ ኢየሱስ ነው። ዘካርያስ ሲናገር አምላክ በእሱ በኩል “ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን” ብሏል።

ከዚያም ዘካርያስ ልጁን ዮሐንስን አስመልክቶ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል:- “ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፣ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፣ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጎበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል።”

በዚህ ጊዜ ገና ያላገባችው ማርያም ናዝሬት ወደሚገኘው መኖሪያዋ ደረሰች። መፀነሷ ሲታወቅ ምን ይደርስባት ይሆን? ሉቃስ 1:​56-80፤ ዘሌዋውያን 12:​2, 3

▪ ዮሐንስ ከኢየሱስ በዕድሜ ምን ያህል ይበልጣል?

▪ ዮሐንስ ከተወለደ ስምንት ቀን ሲሆነው ምን ነገሮች ተከናወኑ?

▪ አምላክ ትኩረቱን ወደ ሕዝቡ ያዞረው እንዴት ነው?

▪ ዮሐንስ ምን ሥራ እንደሚያከናውን በትንቢት ተነግሯል?