በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መከራከሪያ ርዕስ ሆነ

መከራከሪያ ርዕስ ሆነ

ምዕራፍ 41

መከራከሪያ ርዕስ ሆነ

ኢየሱስ በስምዖን ቤት ከተጋበዘ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በገሊላ ሁለተኛውን የስብከት ዙር ጀመረ። ቀደም ሲል በዚህ ክልል እየተዘዋወረ ባካሄደው ስብከት ከእርሱ ጋር የነበሩት ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ የተባሉት የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። አሁን ግን አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እንዲሁም አንዳንድ ሴቶች አብረውት ነበሩ። ከእነዚህም መካከል መግደላዊት ማርያም፣ ሶስናና የንጉሥ ሄሮድስ ሹም ሚስት የሆነችው ዮሐና ይገኙበታል።

የኢየሱስ አገልግሎት እየተጠናከረ ሲሄድ ሥራውን በተመለከተ የሚነሳውም ክርክር እንደዚያው እየጨመረ ሄደ። አንድ ጋኔን የያዘው ሰው ወደ ኢየሱስ አመጡ። ይህ ሰው ዓይነ ስውርና መናገር የተሳነው ሰው ነበር። ኢየሱስ ፈውሶት ከጋኔን ሲያላቅቀውና መናገርና ማየት ሲችል ሰዎቹ በጣም ተገረሙ። “ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ።

ኢየሱስ ባረፈበት ቤት ዙሪያ በጣም ብዙ ሰዎች ስለተሰበሰቡ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ምግብ እንኳ መብላት አልቻሉም። ኢየሱስ ይመጣል ተብሎ ቃል የተገባለት “የዳዊት ልጅ” ሊሆን ይችላል ብለው ካሰቡት ሰዎች ሌላ ጻፎችና ፈሪሳውያንም ኢየሱስን አመኔታ ለማሳጣት ከኢየሩሳሌም መጥተው ነበር። የኢየሱስ ዘመዶች በኢየሱስ ዙሪያ የተፈጠረውን ሁከት ሲሰሙ ሊይዙት መጡ። ሊይዙት የመጡት ለምን ነበር?

የኢየሱስ ወንድሞች ራሳቸው ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ ገና አላመኑም ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ የፈጠረው ሁከትና ግጭት በልጅነቱ ናዝሬት በነበረበት ጊዜ እነሱ ያውቁት ከነበረው የኢየሱስ ባሕርይ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ አእምሮው ተነክቶ መሆን አለበት ብለው አሰቡ። “አበደ” ብለው በማሰብ ይዘውት ሊሄዱ ፈለጉ።

ሆኖም ኢየሱስ ጋኔን የነበረበትን ሰው እንደፈወሰው ማስረጃው በግልጽ ያሳያል። ጻፎችና ፈሪሳውያን ይህን ማስተባበል እንደማይችሉ ያውቃሉ። ስለዚህ ኢየሱስን አመኔታ ለማሳጣት ሕዝቡን “ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም” አሏቸው።

ኢየሱስ አስተሳሰባቸውን በመረዳት ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ወደእሱ ጠራቸውና እንዲህ አላቸው:- “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፣ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፣ እርስ በርሱ ተለያየ፣ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች?”

አስተሳሰባቸውን ውድቅ የሚያደርግ እንዴት ያለ ምክንያታዊ ነጥብ ነው! ፈሪሳውያን በእነሱ መካከል የሚገኙ ሰዎች አጋንንትን እንዳወጡ ይናገሩ ስለነበረ ኢየሱስ “እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፣ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል?” ሲል ጠየቃቸው። በሌላ አነጋገር በኢየሱስ ላይ ያነሱት ክስ በእነሱም ላይ ሊሠራ ይገባል ማለት ነው። ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ ሲል አስጠነቀቃቸው:- “እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፣ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት [“ሳትዘጋጁ፣” NW] ወደ እናንት ደርሳለች።”

ኢየሱስ አጋንንትን ማስወጣቱ በሰይጣን ላይ ያለውን የበላይነት የሚያሳይ ማስረጃ መሆኑን በምሳሌ ለማስረዳት እንዲህ አለ:- “ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል? ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል። ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፣ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል።” ፈሪሳውያን የኢየሱስ ጠላቶች በመሆን የሰይጣን ወኪሎች መሆናቸውን አሳይተዋል። እስራኤላውያን ከእርሱ እንዲርቁና እንዲበተኑ እያደረጉ ነበር።

በዚህም ምክንያት ኢየሱስ እነዚህን ሰይጣናዊ መንፈስ የተጠናወታቸውን ተቃዋሚዎች “መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም” ሲል አስጠነቀቃቸው። እንዲህ ሲል ገለጸ:- “በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።” እነዚህ ጻፎችና ፈሪሳውያን የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በግልጽ የፈጸመውን ተአምራዊ ሥራ ሆን ብለው ሰይጣን የፈጸመው ነው በማለት ይቅርታ የማይደረግለት ኃጢአት ሠርተዋል። ማቴዎስ 12:​22-32፤ ማርቆስ 3:​19-30፤ ሉቃስ 8:​1-3፤ ዮሐንስ 7:​5

▪ ኢየሱስ በገሊላ ያካሄደው ሁለተኛው የስብከት ዙር ከመጀመሪያው የሚለየው እንዴት ነው?

▪ የኢየሱስ ዘመዶች ኢየሱስን ሊይዙት የቃጡት ለምንድን ነው?

▪ ፈሪሳውያን የኢየሱስን ተአምራት ሊያጣጥሉ የሞከሩት እንዴት ነው? ኢየሱስ ትክክል እንዳልሆኑ ያስረዳው እንዴት ነው?

▪ እነዚህ ፈሪሳውያን በምን በደል ተጠያቂዎች ናቸው? ለምንስ?