በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰውን የሚያረክሰው ምንድን ነው?

ሰውን የሚያረክሰው ምንድን ነው?

ምዕራፍ 56

ሰውን የሚያረክሰው ምንድን ነው?

በኢየሱስ ላይ የተነሳው ተቃውሞ እየጠነከረ መጣ። ብዙዎቹ ደቀ መዛሙርት ትተውት ከመሄዳቸውም በላይ በይሁዳ የሚኖሩ አይሁዶች በ31 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በተከበረው የማለፍ በዓል ላይ በኢየሩሳሌም በነበረበት ጊዜ እንዳደረጉት ሁሉ አሁንም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር።

አሁን ጊዜው 32 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ሲሆን የማለፍ በዓል የሚከበርበት ወቅት ነው። ኢየሱስ በማለፍ በዓል ላይ እንዲገኙ የሚያዘውን የአምላክ ሥርዓት በማክበር በበዓሉ ላይ ለመገኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። ይሁን እንጂ ሕይወቱ አደጋ አጥልቶበት ስለነበረ ይህን ያደረገው በጥንቃቄ ነበር። ከዚያ በኋላ ወደ ገሊላ ተመለሰ።

ጻፎችና ፈሪሳውያን ከኢየሩሳሌም ተነስተው ወደ እሱ በመጡበት ጊዜ ኢየሱስ የነበረው በቅፍርናሆም ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። የሃይማኖት ሕጎችን ይጥሳል ብለው ለመክሰስ የሚያስችል ነገር እየፈለጉበት ነበር። “ደቀ መዛሙርትህ ስለ ምን የሽማግሌዎችን ወግ ይተላለፋሉ?” ብለው ጠየቁት። ለምሳሌ “እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡም” አሉት። ይህ አምላክ ያዘዘው ነገር አይደለም፤ ሆኖም ፈሪሳውያን እስከ ክርን ድረስ መታጠብን የሚጨምረውን ይህ ባሕላዊ ሥርዓት አለመፈጸም ከባድ ጥፋት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ነበር።

ኢየሱስ ለክሳቸው መልስ ከመስጠት ይልቅ የአምላክን ሕግ ሆን ብለው እንደጣሱ ጠቆመ። “እናንተስ ወጋችሁን ለመጠበቅ ብላችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለምን ታፈርሳላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። “እግዚአብሔር ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ በአባቱ ወይም በእናቱ ላይ የስድብ ቃል የተናገረ በሞት ይቀጣል’ ብሎ አዝዞአል። እናንተ ግን፣ አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን ‘ከእኔ የምታገኙትን ዕርዳታ ለእግዚአብሔር መባ አድርጌ አቅርቤአለሁ’ ቢላቸው፤ ያ ሰው፣ አባቱን [ወይም እናቱን] ማክበር አያስፈልገውም ትላላችሁ።”​—የ1980 ትርጉም

በእርግጥም ፈሪሳውያን ለአምላክ በስጦታነት የተመደበ ገንዘብ፣ ንብረት ወይም ሌላ ማንኛውም ነገር የቤተ መቅደሱ ንብረት ስለሆነ ለሌላ ዓላማ ሊውል አይችልም ብለው ያስተምሩ ነበር። ሆኖም ለአምላክ በስጦታነት የተወሰነው ነገር አሁንም በሰውየው እጅ እንዳለ ነው። በዚህ መንገድ አንድ ልጅ ገንዘቡ ወይም ንብረቱ ለአምላክ ወይም ለቤተ መቅደሱ የተመደበ ስጦታ ማለትም “ቁርባን” እንደሆነ አድርጎ በመግለጽ በዕድሜ የገፉና ምናልባትም ከባድ ችግር ውስጥ የሚገኙ ወላጆቹን የመርዳት ኃላፊነቱን ከላዩ ላይ ሊያወርድ ይችላል።

ኢየሱስ ፈሪሳውያን የአምላክን ሕግ ሆን ብለው በማዛባታቸው ተገቢ በሆነ የቁጣ መንፈስ እንዲህ አላቸው:- “ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ። እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ ስለ እናንተ:- ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።”

ሕዝቡ ፈሪሳውያን ኢየሱስን መጠየቅ እንዲችሉ ወደ ኋላ ፈቀቅ ብለው የነበረ ይመስላል። አሁን ፈሪሳውያን ኢየሱስ ለሰነዘረባቸው ጠንካራ ወቀሳ የሚመልሱት ነገር ሲያጡ ኢየሱስ ሕዝቡን ወደ እሱ ጠራቸው። ከዚያም እንዲህ አላቸው:- “ስሙ አስተውሉም፤ ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፣ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው።”

በኋላ ወደ ቤት ሲገቡ ደቀ መዛሙርቱ “ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ አወቅህን?” አሉት።

ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ።”

ጴጥሮስ ደቀ መዛሙርቱን በመወከል ሰውን የሚያረክሰውን ነገር በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ሲጠይቀው ኢየሱስ በነገሩ የተገረመ ይመስላል። “እናንተ ደግሞ እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን?” አላቸው። “ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን? ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፣ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በውሸት መመስከር፣ ስድብ ይወጣልና። ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ፣ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም።”

ኢየሱስ እዚህ ላይ የተለመደውን የንጽሕና አጠባበቅ መኮነኑ አይደለም። አንድ ሰው ምግብ ከመሥራቱ ወይም ከመብላቱ በፊት እጆቹን መታጠብ አያስፈልገውም ማለቱ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ወጎች ላይ ችክ በማለት በዘዴ ራሳቸውን ከአምላክ የጽድቅ ሕግጋት ነፃ ለማድረግ የሚጥሩትን የሃይማኖት መሪዎች ግብዝነት ማውገዙ ነበር። አዎን፣ ሰውን የሚያረክሱት ክፉ ሥራዎች ናቸው። እነዚህም ከሰው ልብ የሚመነጩ መሆናቸውን ኢየሱስ አመልክቷል። ዮሐንስ 7:​1፤ ዘዳግም 16:​16፤ ማቴዎስ 15:​1-20፤ ማርቆስ 7:​1-23፤ ዘጸአት 20:​12፤ 21:​17፤ ኢሳይያስ 29:​13

▪ አሁን ኢየሱስ ምን ተቃውሞ ገጠመው?

▪ ፈሪሳውያን ምን ክስ ሰነዘሩ? ሆኖም ኢየሱስ በገለጸው መሠረት ፈሪሳውያን የአምላክን ሕግ ሆን ብለው የሚጥሱት እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ሰውን የሚያረክሱት ነገሮች ምን እንደሆኑ ገልጿል?