በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሳታገባ ፀነሰች

ሳታገባ ፀነሰች

ምዕራፍ 4

ሳታገባ ፀነሰች

ማርያም ከፀነሰች ሦስት ወር ሆኗታል። የመጀመሪያዎቹን የእርግዝና ወራት ያሳለፈችው ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ በሄደችበት ወቅት እንደሆነ ታስታውሳለህ፤ አሁን ግን ናዝሬት ወደሚገኘው መኖሪያዋ ተመልሳለች። ብዙም ሳይቆይ በምትኖርበት ከተማ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ መፀነሷን ሊያውቁ ነው። በእርግጥም ማርያም በጣም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ውስጥ ወድቃለች!

ሁኔታውን ይበልጥ ያከበደው ነገር ማርያም የአናጢው ዮሴፍ ሚስት ለመሆን የታጨች መሆኗ ነው። አምላክ ለእስራኤላውያን ባወጣው ሕግ መሠረት ደግሞ ለአንድ ወንድ የታጨች ሴት በፈቃደኝነት ከሌላ ወንድ ጋር የጾታ ግንኙነት ከፈጸመች በድንጋይ ተወግራ እንደምትሞት ታውቃለች። ማርገዟን ለዮሴፍ እንዴት ብላ ትገልጽለት ይሆን?

ማርያም ሦስት ወር ቆይታ የመጣች በመሆኑ ዮሴፍ እሷን እንደናፈቀ ምንም ጥርጥር የለውም። ሲገናኙ ማርያም ታሪኩን እንደምትነግረው የታወቀ ነው። የፀነሰችው በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አማካኝነት እንደሆነ ለማስረዳት የተቻላትን ሁሉ ጥረት ማድረጓ አይቀርም። ሆኖም ዮሴፍ ይህን ለማመን በጣም እንደሚከብደው አንተም ከሁኔታው መገመት ትችላለህ።

ማርያም በሰዎች ዘንድ ጥሩ ስም ያላት ሴት እንደሆነች ዮሴፍ ያውቃል። ከዚህም በላይ በጣም ይወዳት የነበረ ይመስላል። ሆኖም እሷ ምንም አለች ምን ከሆነ ሰው ያረገዘች ይመስል ነበር። ያም ሆኖ ግን ዮሴፍ ተወግራ እንድትሞት ወይም በሕዝብ ፊት እንድትዋረድ አልፈለገም። ስለዚህ በምስጢር ሊፈታት አሰበ። በዚያ ዘመን የተጫጩ ሰዎች ልክ እንደተጋቡ ይቆጠር ነበር፤ የተጫጩ ሰዎች እንዲለያዩ ከተፈለገ ደግሞ በይፋ መፋታት ነበረባቸው።

በኋላ፣ ዮሴፍ ጉዳዩን ሲያወጣና ሲያወርድ ቆይቶ ተኛ። የይሖዋ መልአክ በሕልም ተገለጠለትና እንዲህ አለው:- “ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።”

ዮሴፍ ሲነቃ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! ምንም ጊዜ ሳያጠፋ መልአኩ ያለውን አደረገ። ማርያምን ወደ ቤቱ ወሰዳት። ይህ በሕዝብ ፊት የተፈጸመ ድርጊት ዮሴፍና ማርያም በይፋ እንደተጋቡ የሚያሳይ ልክ እንደ ጋብቻ ሥነ ሥርዓት የሚያገለግል ነበር። ሆኖም ኢየሱስን እስክትወልድ ድረስ ዮሴፍ ከማርያም ጋር የጾታ ግንኙነት አልፈጸመም።

ተመልከት! ማርያም ሆዷ እየገፋ የመጣ ቢሆንም ዮሴፍ በአህያ ላይ እያስቀመጣት ነው። ወዴት ሊሄዱ ነው? ማርያም የምትወልድበት ጊዜ ተቃርቦ እያለ ጉዞ የሚያደርጉትስ ለምንድን ነው? ሉቃስ 1:​39-41, 56፤ ማቴዎስ 1:​18-25፤ ዘዳግም 22:​23, 24

▪ ዮሴፍ ማርያም መፀነሷን ሲያውቅ ምን ለማድረግ አስቦ ነበር? ለምንስ?

▪ ገና ያልተጋቡ ሰዎች ሆነው ሳለ ዮሴፍ ማርያምን እንዴት ሊፈታት ይችላል?

▪ የዮሴፍና የማርያም የጋብቻ ሥርዓት ሆኖ የሚያገለግለው የትኛው በሕዝብ ፊት የተፈጸመ ድርጊት ነው?