በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሳንሄድሪን ፊት ቀረበ፤ ከዚያም ወደ ጲላጦስ ተወሰደ

ሳንሄድሪን ፊት ቀረበ፤ ከዚያም ወደ ጲላጦስ ተወሰደ

ምዕራፍ 121

ሳንሄድሪን ፊት ቀረበ፤ ከዚያም ወደ ጲላጦስ ተወሰደ

ሌሊቱ እየተገባደደ ነው። ጴጥሮስ ኢየሱስን ለሦስተኛ ጊዜ የካደው ሲሆን የሳንሄድሪን አባላት ሲያካሄዱት የቆዩትን የፌዝ ችሎት አጠናቀው ተበትነዋል። ይሁን እንጂ ዓርብ እንደነጋ እንደገና ተሰበሰቡ፤ አሁን የተሰበሰቡት በሳንሄድሪን ሸንጎ መሰብሰቢያ አዳራሻቸው ውስጥ ነው። የተሰበሰቡበት ዓላማ ሌሊት ያካሄዱት ችሎት ሕጋዊ መልክ እንዲኖረው ለማድረግ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ ፊታቸው ሲቀርብ ሌሊት እንዳደረጉት ሁሉ አሁንም “ክርስቶስ አንተ ነህን? ንገረን” አሉት።

ኢየሱስ “ብነግራችሁ አታምኑም” ሲል መለሰላቸው። “ብጠይቅም አትመልሱልኝም።” ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ይቀመጣል” በማለት በድፍረት ማንነቱን ገለጸላቸው።

ሁሉም “እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስ “እኔ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ” ሲል መለሰላቸው።

እነዚህ ሰዎች ዓላማቸው እሱን ለመግደል ስለሆነ ይህ መልስ ለእነርሱ በቂ ነበር። ልክ አምላክን እንደ ሰደበ አድርገው ቆጠሩት። “ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል?” አሉ። ስለዚህ ኢየሱስን አስረው ወሰዱትና ለሮማዊው ገዥ ለጴንጤናዊው ጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት።

ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ሲከናወን የነበረውን ነገር ይከታተል ነበር። ኢየሱስ እንደተፈረደበት ሲያውቅ ተጸጸተ። ስለዚህ ሠላሳውን ብር ለመመለስ ወደ ካህናት አለቆቹና ወደ ሕዝቡ ሽማግሌዎች ሄዶ “ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” አላቸው።

“ታዲያ እኛ ምን ቸገረን! የራስህ ጉዳይ ነው!” በማለት ደንታ ቢስነታቸውን በሚያሳይ መንገድ መለሱለት። (የ1980 ትርጉም) ስለዚህ ይሁዳ ብሩን ቤተ መቅደሱ ውስጥ በትኖ ሄደና ራሱን ለመስቀል ሞከረ። ይሁን እንጂ ይሁዳ ገመዱን አስሮበት የነበረው ቅርንጫፍ ሳይሰበር አይቀርም፤ ሲወድቅ ሰውነቱ ከታች ከነበሩት አለቶች ጋር በመላተሙ ተሰንጥቆ ሞተ።

የካህናት አለቆቹ ብሩን ምን እንደሚያደርጉበት ግራ ገባቸው። “የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም” አሉ። ስለዚህ አንድ ላይ ሆነው ከተማከሩ በኋላ ለእንግዶች መቃብር እንዲሆን የሸክላ ሠሪውን መሬት ገዙበት። ስለዚህ መሬቱ “የደም መሬት” ተባለ።

ኢየሱስ ወደ ገዥው ቤተ መንግሥት ሲወሰድ አሁንም ጊዜው ገና ማለዳ ነበር። ሆኖም ከኢየሱስ ጋር የመጡት አይሁዶች ከአሕዛብ ጋር እንዲህ ዓይነት የቅርብ ግንኙነት ማድረግ ያረክሰናል ብለው ስለሚያምኑ ለመግባት ፈቃደኞች አልሆኑም። ስለዚህ ጲላጦስ እነርሱን ለመርዳት ሲል ወደ ውጪ ወጣ። “ይህን ሰው ስለ ምን ትከሱታላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

እነርሱም “ይህስ ክፉ አድራጊ ባይሆን ወደ አንተ አሳልፈን ባልሰጠነውም ነበር” ሲሉ መለሱለት።

ጲላጦስ በዚህ ጉዳይ እጁን ማስገባት ስላልፈለገ “እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት” አላቸው።

አይሁዶቹ እርሱን ለመግደል ያላቸውን ፍላጎት በመግለጽ “ለእኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም” አሉት። በእርግጥም ኢየሱስን በማለፍ በዓል ላይ ቢገድሉት ኖሮ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን ከፍ አድርገው ይመለከቱት ስለነበረ የሕዝብ ዓመፅ ሊቀሰቀስ ይችል ነበር። ሆኖም ሮማውያን በፖለቲካ ክስ እንዲገድሉት ማድረግ ከቻሉ እነርሱ በሕዝቡ ዘንድ ከተጠያቂነት ነፃ ሊሆኑ ይችላሉ።

ስለዚህ የሃይማኖት መሪዎቹ አምላክን ሰድቦአል ብለው ኢየሱስን የወነጀሉበትን ችሎት ሳይጠቅሱ አሁን የተለያዩ ክሶች ፈጠሩ። ሦስት ክፍሎችን የያዘ ክስ መሠረቱ:- “ይህ [1] ሕዝባችንን ሲያጣምም [2] ለቄሣርም ግብር እንዳይሰጥ ሲከለክል ደግሞም:- [3] እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ ሲል አገኘነው።”

ጲላጦስን ይበልጥ ያሳሰበው ኢየሱስ እኔ ንጉሥ ነኝ ብሏል የሚለው ክስ ነበር። ስለዚህ እንደገና ወደ ቤተ መንግሥቱ ገብቶ ኢየሱስን አስጠራውና “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው። በሌላ አነጋገር፣ ቄሣርን በመቃወም እኔ ንጉሥ ነኝ ብለህ ሕጉን ተላልፈሃልን? ማለቱ ነበር።

ኢየሱስ ጲላጦስ ስለ እርሱ ምን ያህል እንደሰማ ማወቅ ስለፈለገ “አንተ ይህን የምትለው ከራስህ ነውን ወይስ ሌሎች ስለ እኔ ነገሩህን?” ሲል ጠየቀው።

ጲላጦስ ስለ እርሱ የሚያውቀው ነገር እንደሌለና እውነታውን ማወቅ እንደሚፈልግ ገለጸ። “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል?” አለው።

ኢየሱስ ንግሥናን በተመለከተ የተነሣውን ጉዳይ እንዲሁ አድበስብሶ ለማለፍ አልሞከረም። ኢየሱስ ቀጥሎ የሰጠው መልስ ጲላጦስን እንዳስገረመው ምንም አያጠራጥርም። ሉቃስ 22:​66 እስከ 23:​3፤ ማቴዎስ 27:​1-11፤ ማርቆስ 15:​1፤ ዮሐንስ 18:​28-35፤ ሥራ 1:​16-20

▪ የሳንሄድሪን ሸንጎ እንደገና ጠዋት የተሰበሰበው ለምን ዓላማ ነው?

▪ ይሁዳ የሞተው እንዴት ነው? በ30ው ብርስ ምን ተደረገበት?

▪ አይሁዶች ኢየሱስን ራሳቸው ከመግደል ይልቅ ሮማውያን እንዲገድሉት ለማድረግ የፈለጉት ለምንድን ነው?

▪ አይሁዶች በኢየሱስ ላይ ምን ክሶች መሠረቱ?