በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ምሕረት የተሰጠ ትምህርት

ስለ ምሕረት የተሰጠ ትምህርት

ምዕራፍ 40

ስለ ምሕረት የተሰጠ ትምህርት

ኢየሱስ አሁንም ያለው ከጥቂት ጊዜ በፊት የአንዲትን መበለት ልጅ ከሞት ባስነሳበት በናይን ከተማ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም፤ ወይም ደግሞ በአቅራቢያዋ ወደምትገኝ አንዲት ከተማ ሄዶ ይሆናል። ስምዖን የተባለ አንድ ፈሪሳዊ እነዚህን አስደናቂ ሥራዎች እያከናወነ ያለውን ሰው ይበልጥ ቀረብ ብሎ ለማወቅ ፈለገ። ስለዚህ ኢየሱስን ወደ ቤቱ ጋበዘው።

ኢየሱስ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኃጢአተኞች ከእነርሱ ጋር እንዲበላ ያቀረቡለትን ግብዣ እንደተቀበለ ሁሉ ይህንንም ግብዣ በዚያ የሚገኙትን ሰዎች ለማገልገል የሚያስችል አጋጣሚ እንደሆነ አድርጎ በመመልከት ጥሪውን ተቀበለ። ሆኖም ኢየሱስ ወደ ስምዖን ቤት ሲገባ ብዙውን ጊዜ ለእንግዶች የሚደረገው ወዳጃዊ አቀባበል አልተደረገለትም።

አቧራማ በሆኑ መንገዶች ላይ በነጠላ ጫማ መጓዝ እግር እንዲቆሽሽና በጣም እንዲሞቅ ስለሚያደርግ የእንግዶችን እግር በቀዝቃዛ ውኃ ማጠብ የተለመደ የእንግዳ ተቀባይነት ተግባር ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ሲመጣ እግሩን አላጠቡትም። እንኳን ደህና መጣህ ብሎ በመቀበል የሳመውም አልነበረም፤ ይህም ቢሆን የተለመደ ሥነ ሥርዓት ነበር። አብዛኛውን ጊዜ እንደሚደረገውም በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ፀጉሩን ዘይት አልቀቡትም።

እንግዶቹ ሁሉ በማዕድ ዙሪያ ቀርበው ምግቡ እየተበላ ሳለ አንዲት ያልተጋበዘች ሴት ቀስ ብላ ወደ ክፍሉ ገባች። ሴትዮዋ ሥነ ምግባር በጎደለው አኗኗሯ በከተማይቱ ውስጥ የታወቀች ነበረች። ኢየሱስ ‘ሸክማቸው የከበደ ሁሉ ወደርሱ መጥተው ዕረፍት እንዲያገኙ’ ያቀረበውን ጥሪ ጨምሮ ያስተማረውን ትምህርት ሳትሰማ አትቀርም። ባየችውና በሰማችው ነገር ልቧ በጣም ስለተነካ ኢየሱስን ፈልጋ አገኘችው።

ሴትዮዋ በጀርባው በኩል ወደ ማዕዱ መጣችና ከኢየሱስ እግር አጠገብ ተንበረከከች። እንባዋን እግሩ ላይ እያፈሰሰች በፀጉሯ ትጠርገው ጀመር። ከዚያም ከብልቃጧ ውስጥ ሽቶ አውጥታ እግሩን እየሳመች ሽቶውን አፈሰሰችበት። ስምዖን ሁኔታውን አየ፤ አድራጎቱ ግን ትክክል መስሎ አልታየውም። “ይህስ ነቢይ ቢሆን፣ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፣ ኃጢአተኛ ናትና” ብሎ አሰበ።

ኢየሱስ ምን እያሰበ እንዳለ በመረዳት “ስምዖን ሆይ፣ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው።

“መምህር ሆይ፣ ተናገር” ሲል መለሰለት።

“ለአንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት” በማለት ኢየሱስ ንግግሩን ጀመረ። “በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት በሁለተኛውም አምሳ። የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው?”

ስምዖን “ብዙ የተወለቱ ይመስለኛል” ሲል መለሰ፤ ምናልባትም ጥያቄው ትርጉም የለሽ ስለሚመስል መልስ የሰጠው በግዴለሽነት መንፈስ ሳይሆን አይቀርም።

ኢየሱስም “በእውነት ፈረድህ” አለው። ከዚያም ወደ ሴቲቱ ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው:- “ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፣ ውኃ ስንኳ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች በጠጉርዋም አበሰች። አንተ አልሳምኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች።”

በዚህ መንገድ ሴትዮዋ ቀደም ሲል ለፈጸመችው ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ንስሐ መግባቷን አሳየች። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ደመደመ:- “ስለዚህ እልሃለሁ፣ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል።”

ኢየሱስ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ለመፈጸም የሚያበቃ ጥሩ ምክንያት አለ ማለቱ ወይም ድርጊቱን ችላ ብሎ ማለፉ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይህ ሁኔታ ኢየሱስ በሕይወታቸው ውስጥ ስሕተት ከፈጸሙ በኋላ በፈጸሙት ድርጊት እንዳዘኑ በማሳየት ዕረፍት ለማግኘት ወደ ክርስቶስ የሚመጡትን ሰዎች ችግር በርኅራኄ መንፈስ የሚረዳላቸው መሆኑን ያሳያል። ኢየሱስ ለሴትዮዋ እውነተኛ ዕረፍት በመስጠት “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል . . . እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” አላት። ሉቃስ 7:​36-50፤ ማቴዎስ 11:​28-30

▪ ኢየሱስ በጋባዡ በስምዖን የተደረገለት አቀባበል ምን ይመስል ነበር?

▪ ኢየሱስን ፈልጋ ያገኘችው ማን ነበረች? ለምንስ?

▪ ኢየሱስ ምን ምሳሌ አቀረበ? ምሳሌውን የተጠቀመበትስ እንዴት ነው?