በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ትሕትና የተሰጠ ትምህርት

ስለ ትሕትና የተሰጠ ትምህርት

ምዕራፍ 62

ስለ ትሕትና የተሰጠ ትምህርት

ኢየሱስ በፊልጶስ ቂሣርያ አቅራቢያ በሚገኝ ክልል ጋኔን ይዞት የነበረውን ልጅ ከፈወሰ በኋላ መኖሪያው ወደሆነችው ወደ ቅፍርናሆም መመለስ ፈለገ። ይሁን እንጂ ለሚሞትበት ጊዜና ከዚያ በኋላ ለሚሸከሟቸው ኃላፊነቶች ይበልጥ ሊያዘጋጃቸው እንዲችል ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻ መጓዝ ፈልጎ ነበር። “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፣ ይገድሉትማል፣ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል” አላቸው።

ኢየሱስ ከዚህ በፊት ስለዚህ ጉዳይ ተናግሮ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሦስቱ ሐዋርያት ኢየሱስ ተአምራዊ ለውጥ ባደረገበት ጊዜ ስለ “መውጣቱ” ውይይት ሲደረግ አይተዋል። ያም ሆኖ ግን ተከታዮቹ ነገሩ አሁንም አልገባቸውም ነበር። ቀደም ሲል ጴጥሮስ እንዳደረገው ኢየሱስ የሚገደል መሆኑን አምኖ ለመቀበል ያንገራገረ ባይኖርም እንኳ ስለ ጉዳዩ ተጨማሪ ጥያቄ ለማቅረብ አልደፈሩም።

በመጨረሻ በኢየሱስ አገልግሎት ወቅት እንደ መኖሪያውና የእንቅስቃሴው ማዕከል ሆና ታገለግል ወደነበረችው ወደ ቅፍርናሆም ደረሱ። ቅፍርናሆም የጴጥሮስና የሌሎች በርከት ያሉ ሐዋርያት የትውልድ ከተማ ናት። እዚያ ሲደርሱም የቤተ መቅደስ ግብር የሚሰበስቡ ሰዎች ጴጥሮስን ቀርበው አነጋገሩት። “መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር [የቤተ መቅደስ ግብር] አይገብርምን?” ብለው ጠየቁት። ይህን ያደረጉት ኢየሱስ ተቀባይነት አግኝቶ የሚሠራበትን ልማድ እንዲጥስ ለማድረግ ሳይሆን አይቀርም።

ጴጥሮስ “አዎን ይገብራል” በማለት ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሰጠ።

ኢየሱስ ወደ ቤት የደረሰው ትንሽ ዘግየት ብሎ ሳይሆን አይቀርም፤ ሆኖም የተከናወነውን ነገር አውቆ ነበር። ስለዚህ ጴጥሮስ ጉዳዩን ከማንሳቱ በፊት ኢየሱስ “ስምዖን ሆይ፣ ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸውን ወይስ ከእንግዶች?” ብሎ ጠየቀው።

ጴጥሮስ “ከእንግዶች” ብሎ መለሰ።

“እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው” ሲል ኢየሱስ ተናገረ። በቤተ መቅደሱ የሚመለከው የኢየሱስ አባት የጽንፈ ዓለሙ ንጉሥ ስለሆነ የአምላክን ልጅ የቤተ መቅደስ ግብር እንዲከፍል መጠየቅ ሕጋዊ ደንብ አይደለም። ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ነገር ግን እንዳናሰናክላቸው፣ ወደ ባሕር ሂድና መቃጥን ጣል፣ መጀመሪያም የሚወጣውን ዓሣ ውሰድና አፉን ስትከፍት እስታቴር [አራት ዲናር] ታገኛለህ፤ ያን ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ስጣቸው።”

ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆም ከተመለሱ በኋላ፣ በጴጥሮስ ቤት ሳይሆን አይቀርም፣ አንድ ላይ ሲሰባሰቡ “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ ከፊልጶስ ቂሣርያ ሲመለሱ ከኋላው እየተከተሉት ምን ይነጋገሩ እንደነበረ ስላወቀ ይህን ጥያቄ እንዲጠይቁ ያነሳሳቸው ነገር ምን እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ስለዚህ “በመንገድ እርስ በርሳችሁ ምን ተነጋገራችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። ደቀ መዛሙርቱ ይነጋገሩ የነበረው ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሚሆን ስለነበር መልስ ለመስጠት አፍረው ዝም አሉ።

ኢየሱስ ወደ ሦስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ በደቀ መዛሙርቱ መካከል እንዲህ ያለ ክርክር መነሳቱ አያስገርምም? ሰብዓዊ አለፍጽምና እንዲሁም ያደጉበት ሃይማኖት ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳሳደረባቸው የሚያሳይ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ያደጉበት የአይሁድ እምነት በማንኛውም ሁኔታ ረገድ ለሥልጣንና ለማዕረግ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጥ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ጴጥሮስ የተወሰኑ “መክፈቻዎች” እንደሚሰጡት ኢየሱስ ቃል የገባለት በመሆኑ ከሌሎቹ የላቀ እንደሆነ ተሰምቶት ይሆናል። ያዕቆብና ዮሐንስም የኢየሱስን ተአምራዊ ለውጥ የማየት መብት በማግኘታቸው ተመሳሳይ አስተሳሰብ አድሮባቸው ይሆናል።

ብቻ ምንም ሆነ ምን ኢየሱስ አስተሳሰባቸውን ለማረም ሲል አንድ ስሜት የሚነካ ሠርቶ ማሳያ አቀረበ። አንድ ሕፃን ጠራና በመካከላቸው አቆመው፤ ከዚያም አቀፈውና እንዲህ አለ:- “ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፣ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፣ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው። እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል።”

ደቀ መዛሙርቱን ለማረም የተጠቀመበት መንገድ በጣም አስደናቂ ነው! ኢየሱስ ተቆጥቶ ትዕቢተኞች፣ ስግብግቦች ወይም የሥልጣን ጥመኞች ናችሁ አላላቸውም። ከዚህ ይልቅ ራሳቸውን ከፍ ከፍ የማድረግና ለሥልጣን የመጓጓት ጠባይ የሌላቸውንና በጥቅሉ ማዕረግ የሚባል ነገር የማያሳስባቸውን ሕፃናት ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም እርማት ያዘለ ትምህርት ሰጥቷቸዋል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ትሑት የሆኑ ልጆች የሚያሳዩአቸውን እነዚህን ባሕርያት ማዳበር እንዳለባቸው አመልክቷል። ኢየሱስ ሲደመድም “ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነው” አላቸው። ማቴዎስ 17:​22-27፤ 18:​1-5፤ ማርቆስ 9:​30-37፤ ሉቃስ 9:​43-48

▪ ከቅፍርናሆም እየተመለሱ ሳለ ኢየሱስ የትኛውን ትምህርት ደገመላቸው? ያሳዩት ምላሽስ ምን ነበር?

▪ ኢየሱስ የቤተ መቅደሱን ግብር የመክፈል ግዴታ የሌለበት ለምንድን ነው? ሆኖም የከፈለው ለምን ነበር?

▪ ደቀ መዛሙርቱ እንዲከራከሩ አስተዋጽኦ ያደረገው ነገር ምን ሊሆን ይችላል? ኢየሱስ ያረማቸውስ እንዴት ነው?