በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ይቅር ባይነት የተሰጠ ትምህርት

ስለ ይቅር ባይነት የተሰጠ ትምህርት

ምዕራፍ 64

ስለ ይቅር ባይነት የተሰጠ ትምህርት

ኢየሱስ አሁንም ያለው ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በቅፍርናሆም በሚገኘው ቤት ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። በወንድሞች መካከል ግጭት ሲፈጠር ምን ማድረግ እንደሚገባ እየነገራቸው ነበር። ስለዚህ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት?” ሲል ጠየቀው። የአይሁድ ሃይማኖታዊ አስተማሪዎች እስከ ሦስት ጊዜ ይቅር ማለት ጥሩ እንደሆነ ያስተምሩ ስለነበር ጴጥሮስ “እስከ ሰባት ጊዜን?” ብሎ መናገሩ ትልቅ ደግነት እንደሆነ አድርጎ አስቦ ይሆናል።

ሆኖም መቁጠሩ ራሱ ትክክል አይደለም። ኢየሱስ “እስከ ሰባ ሰባት ጊዜ እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም” (NW) በማለት ጴጥሮስን አርሞታል። ጴጥሮስ ወንድሙን ምን ያህል ጊዜ ይቅር ማለት እንዳለበት የሚወስን ገደብ መበጀት እንደሌለበት አመልክቷል።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ይቅር የማለት ግዴታ እንዳለባቸው በአጽንኦት ለማስገንዘብ አንድ ምሳሌ ነገራቸው። ምሳሌው ከባሪያዎቹ ጋር ያሉትን ሒሳብ ነክ ጉዳዮች ለማወራረድ ስለፈለገ አንድ ንጉሥ የሚገልጽ ነው። 60,000,000 ዲናር ዕዳ ውስጥ የተዘፈቀ አንድ ባሪያ ወደ እሱ አመጡ። ዕዳውን መክፈል የሚችልበት ምንም መንገድ አልነበረውም። ስለዚህ ንጉሡ እሱ፣ ሚስቱና ልጆቹ ተሸጠው ዕዳው እንዲከፈል እንዳዘዘ ኢየሱስ ገለጸ።

በዚህ ጊዜ ባሪያው በጌታው እግር ሥር ወድቆ “ታገሠኝ፣ ሁሉንም እከፍልሃለሁ” አለው።

ጌታው አዘነለትና ባሪያው የነበረበትን ከፍተኛ ዕዳ በመሰረዝ ምሕረት አደረገለት። ሆኖም ወዲያውኑ ይህ ባሪያ ወጥቶ እየሄደ እያለ ከእሱ 100 ዲናር ብቻ የተበደረ ሌላ ባሪያ እንዳገኘ በመግለጽ ኢየሱስ ታሪኩን ቀጠለ። ሰውየው ባልንጀራው የሆነውን ባሪያ ጉሮሮ አነቀና “ዕዳህን ክፈለኝ” አለው።

ሆኖም ይህ ባሪያ ዕዳውን ለመክፈል የሚያስችል ገንዘብ አልነበረውም። ስለዚህ በአበዳሪው ባሪያ እግር ላይ ወድቆ “ታገሠኝ፣ ሁሉንም እከፍልሃለሁ” ብሎ ለመነው። ባሪያው እንደ ጌታው መሐሪ አልነበረም። ባልንጀራው የሆነውን ባሪያ እንዲታሰር አደረገው።

ኢየሱስ በመቀጠል የተፈጸመውን ነገር ያዩ ሌሎቹ ባሮች ሄደው ለጌታቸው እንደነገሩት ገለጸ። ጌታቸውም ተቆጥቶ ባሪያውን አስጠራው። “አንተ ክፉ ባሪያ፣ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን?” አለው። ጌታው በሁኔታው በጣም በመናደዱ ምሕረት ያላደረገው ባሪያ ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለወኅኒ ቤት ጠባቂዎች አሳልፎ ሰጠው።

ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ደመደመ:- “ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፣ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።”

የይቅር ባይነትን አስፈላጊነት የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው! አንድ ክርስቲያን ወንድማችን ምንም ዓይነት በደል ቢፈጽምብን አምላክ ይቅር ብሎ ከተወልን ከፍተኛ የኃጢአት ዕዳ ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ነው። ከዚህም በላይ ይሖዋ አምላክ በሺህ ለሚቆጠሩ ጊዜያት ደጋግሞ ይቅር ብሎናል። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ በእሱ ላይ ኃጢአት እንደሠራን እንኳ አይታወቀንም። እንግዲያው ትክክለኛ የሆነ ቅሬታ ቢያድርብን እንኳ ወንድማችንን ለጥቂት ጊዜያት ደጋግመን ይቅር ማለት ሊከብደን ይገባልን? ኢየሱስ በተራራው ስብከት ላይ እንዳስተማረው አምላክ “የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር” እንደሚለን አስታውስ። ማቴዎስ 18:​21-35፤ 6:​12፤ ቆላስይስ 3:​13

▪ ጴጥሮስ ወንድሙን ይቅር ስለማለት ጥያቄ እንዲያቀርብ ያነሳሳው ምንድን ነው? አንድን ሰው ሰባት ጊዜ ይቅር ለማለት ያቀረበው ሐሳብ ትልቅ ደግነት ነው ብሎ እንዲያስብ ያደረገው ምን ሊሆን ይችላል?

▪ ንጉሡ ምሕረት እንዲያደርግለት ባሪያው ሲለምነው የሰጠው ምላሽ ባሪያው ባልንጀራው የሆነ ሌላ ባሪያ ላቀረበለት ልመና ከሰጠው ምላሽ የሚለየው እንዴት ነው?

▪ ከኢየሱስ ምሳሌ ምን እንማራለን?