በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ፍቺና ልጆችን ስለ ማፍቀር የተሰጡ ትምህርቶች

ስለ ፍቺና ልጆችን ስለ ማፍቀር የተሰጡ ትምህርቶች

ምዕራፍ 95

ስለ ፍቺና ልጆችን ስለ ማፍቀር የተሰጡ ትምህርቶች

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በተከበረው የማለፍ በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ኢየሩሳሌም እያመሩ ነው። የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው በፍርጊያ አውራጃ በኩል በሚወስደው መንገድ ተጓዙ። ኢየሱስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በፍርጊያ ነበር፤ ሆኖም እዚያ ሳለ ወዳጁ አልዓዛር በመታመሙ ወደ ይሁዳ ተጠራ። ኢየሱስ በፍርጊያ በነበረበት ወቅት ከፈሪሳውያን ጋር ስለ ፍቺ ተነጋግሮ ነበር። አሁንም ፈሪሳውያን ይህንኑ ጉዳይ እንደገና አነሱ።

ፈሪሳውያን ፍቺን በተመለከተ የተለያየ አስተሳሰብ ነበራቸው። ሙሴ አንዲት ሴት ‘የእፍረት ነገር ከተገኘባት’ ልትፈታ እንደምትችል ተናግሯል። አንዳንዶቹ ይህ የሚያመለክተው ድንግል አለመሆንን ብቻ ነው ብለው ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ “የእፍረት ነገር” የሚለው አነጋገር በጣም ቀላል የሆኑ በደሎችንም ይጨምራል ብለው ያስባሉ። ስለዚህ ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለመፈተን “ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስ የሚሰጠው መልስ ምንም ሆነ ምን ፈሪሳውያን የያዙት አመለካከት የተለያየ በመሆኑ ከአንዱ አመለካከት ጋር መጋጨቱ እንደማይቀር ተማምነው ነበር።

ኢየሱስ ለጥያቄው የሰጠው መልስ ከፍተኛ ችሎታ የተንጸባረቀበት ነበር። መልሱን የሰጠው የትኛውንም ሰብዓዊ አመለካከት በመደገፍ ሳይሆን ወደ ኋላ ተመልሶ የመጀመሪያውን የጋብቻ ዓላማ በመጥቀስ ነበር። እንዲህ ሲል ጠየቃቸው:- “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፣ አለም:- ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው።”

የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ የትዳር ጓደኛሞች ሳይፋቱ አንድ ላይ ሆነው እንዲኖሩ እንደሆነ ኢየሱስ አመልክቷል። ፈሪሳውያን እንደዚያ ከሆነ ታዲያ “ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ?” ሲሉ መልሰው ጠየቁት።

“ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ [“በአስተያየት፣” NW] ፈቀደላችሁ” በማለት ኢየሱስ መለሰላቸው፤ “ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም።” አዎን፣ አምላክ በኤደን የአትክልት ሥፍራ እውነተኛውን የትዳር መሥፈርት ባወጣ ጊዜ ለፍቺ የሚሆን ምንም ዓይነት ደንብ አልሰጠም።

ኢየሱስ በመቀጠል ፈሪሳውያንን እንዲህ አላቸው:- “እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ያለ ዝሙት [ፖርኒያ ከተባለው የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው] ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።” በዚህ መንገድ ኢየሱስ በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው ለፍቺ ምክንያት የሚሆነው ነገር ከባድ የጾታ ብልግና የሆነው ፖርኒያ ብቻ እንደሆነ አመልክቷል።

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጋብቻ በዚህ ምክንያት ብቻ ካልሆነ በስተቀር ፍቺ የሌለበት ዘላቂ ጥምረት መሆን እንዳለበት በመገንዘብ “የባልና የሚስት ሁኔታ እንዲህ ከሆነ አለማግባት የተሻለ ነው” አሉ። (የ1980 ትርጉም) ለማግባት የሚያስብ ሰው ስለ ትዳሩ ዘላቂነት በቁም ነገር ሊያስብ እንደሚገባ ምንም አያጠያይቅም!

ኢየሱስ በመቀጠል ስለ ነጠላነት ተናገረ። አንዳንድ ወንዶች ልጆች ጃንደረቦች ሆነው ይወለዳሉ፤ አባላዘራቸው ባለመዳበሩ ለጋብቻ ብቃት የሌላቸው ይሆናሉ። ሌሎች ደግሞ በሰዎች አረመኔያዊ ድርጊት ተሰልበው ጃንደረቦች ይሆናሉ። በመጨረሻ ደግሞ አንዳንዶች ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን ከመንግሥተ ሰማያት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ማዋል እንዲችሉ ለማግባት ያላቸውን ፍላጎት ወይም የጾታ ስሜታቸውን አፍነው ይይዛሉ። ኢየሱስ “[ነጠላነትን] ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው” በማለት ደመደመ።

በዚህ ጊዜ ሰዎች ሕፃናት ልጆቻቸውን ወደ ኢየሱስ ይዘው መጡ። ይሁን እንጂ ደቀ መዛሙርቱ ሕፃናቱን ገስጸው ሊመልሷቸው ሞከሩ፤ ይህን ያደረጉት ኢየሱስን አላስፈላጊ ከሆነ ውጥረት ለመጠበቅ ብለው እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም።”

ኢየሱስ እንዴት ግሩም የሆኑ ትምህርቶች ሰጥቷል! የአምላክን መንግሥት ለመውረስ ልክ እንደ ትንንሽ ልጆች ትሑቶችና ለመማር ዝግጁዎች መሆን አለብን። ሆኖም የኢየሱስ ምሳሌነት በተለይ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ጊዜ ማሳለፋቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነም የሚያሳይ ነው። ኢየሱስ ሕፃናቱን በማቀፍና በመባረክ ለእነርሱ ያለውን ፍቅር አሳይቷል። ማቴዎስ 19:​1-15፤ ዘዳግም 24:​1፤ ሉቃስ 16:​18፤ ማርቆስ 10:​1-16፤ ሉቃስ 18:​15-17

▪ ፈሪሳውያን ፍቺን በተመለከተ ምን የተለያዩ አመለካከቶች ነበሯቸው? በመሆኑም ኢየሱስን የፈተኑትስ እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ፈሪሳውያን እሱን ለመፈተን ላደረጉት ጥረት ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? ኢየሱስ የጠቀሰው ለፍቺ ምክንያት የሚሆነው ብቸኛ ነገርስ ምንድን ነው?

▪ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አለማግባት የተሻለ ነው ብለው የተናገሩት ለምንድን ነው? ኢየሱስስ ለምን ነገር የድጋፍ ሐሳብ ሰጠ?

▪ ኢየሱስ ለሕፃናት ባሳየው ባሕርይ ምን ትምህርት ሰጥቶናል?