በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስደት ለመቀበል መዘጋጀት

ስደት ለመቀበል መዘጋጀት

ምዕራፍ 50

ስደት ለመቀበል መዘጋጀት

ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ እንዴት ማከናወን እንዳለባቸው ለሐዋርያቱ መመሪያዎች ከሰጣቸው በኋላ ከተቃዋሚዎች እንዲጠበቁ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው። እንዲህ አላቸው:- “እነሆ፣ እኔ እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ . . . ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፣ በምኩራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤ ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፣ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ።”

ኢየሱስ ተከታዮቹ ከባድ ስደት የሚደርስባቸው ቢሆንም እንኳ የሚከተለውን መንፈስን የሚያረጋጋ ተስፋ ሰጥቷቸዋል:- “አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፣ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፣ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና።”

ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፣ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ ይገድሉአቸውማል።” አክሎም እንዲህ አለ:- “እናንተም በእኔ ምክንያት በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ ነገር ግን እስከ መጨረሻው በትዕግሥት የሚጸና ይድናል።”​—የ1980 ትርጉም

የስብከቱ ሥራ ከሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው ነው። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ከእስራት ነፃ ሆኖ ሥራውን ለማከናወን እንዲቻል ጥበብ የመጠቀምን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። “በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፣ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም” ብሏል።

ኢየሱስ ይህን መመሪያ፣ ማስጠንቀቂያና ማበረታቻ የሰጠው ለአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እንደሆነ አይካድም፤ ሆኖም ከእሱ ሞትና ትንሣኤ በኋላ በዓለም ዙሪያ በሚካሄደው የስብከት ሥራ የሚካፈሉትንም ሰዎች ይመለከታል። ምክንያቱም ደቀ መዛሙርቱ የሚጠሉት ሐዋርያቱ እንዲሰብኩ በተላኩባቸው ቦታዎች ባሉት እስራኤላውያን ብቻ ሳይሆን ‘በሁሉም ሕዝቦች’ ዘንድ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ ሐዋርያቱን ለአጭር ጊዜ ለሚቆየው የስብከት ዘመቻ ሲልካቸው በገዥዎችና በነገሥታት ፊት እንዳልቀረቡ ግልጽ ነው። ከዚህም በላይ በዚያን ጊዜ አማኞች በቤተሰብ አባሎቻቸው አልተገደሉም።

ስለዚህ ኢየሱስ “የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ” ደቀ መዛሙርቱ ስብከታቸውን አዳርሰው እንደማይጨርሱ መናገሩ፣ ከፍተኛ ክብር የተቀዳጀው ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚ ሆኖ በአርማጌዶን ከመምጣቱ በፊት፣ ደቀ መዛሙርቱ ስለተቋቋመው የአምላክ መንግሥት በመላዋ ምድር ላይ የሚያከናውኑትን የስብከት ሥራ እንደማያጠናቅቁ ትንቢታዊ በሆነ መንገድ መግለጹ ነበር።

ኢየሱስ ስለ ስብከቱ ሥራ የሚሰጠውን መመሪያ በመቀጠል “ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፣ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም” አለ። ስለዚህ የኢየሱስ ተከታዮች የአምላክን መንግሥት በመስበካቸው በኢየሱስ ላይ የደረሰውን ዓይነት ግፍና ስደት እንደሚቀበሉ መጠበቅ አለባቸው። ሆኖም እንዲህ ሲል አጥብቆ መከራቸው:- “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፣ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።”

በዚህ ረገድ ኢየሱስ ጥሩ ምሳሌ ሆኗል። ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ኃይል ላለው ለይሖዋ አምላክ ያለውን ታማኝነት ከማላላት ያላንዳች ፍርሃት ሞትን ለመቀበል መር⁠ጧል። አዎን፣ የአንድን ሰው “ነፍስ” ማጥፋት ወይም አንድ ሰው የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ ከሞት ማስነሳት የሚችለው ይሖዋ ነው። (እዚህ ላይ ነፍስ የሚለው ቃል የተሠራበት የአንድን ሰው ሕያው ነፍስ ሆኖ የመኖር የወደፊት ተስፋ ለመግለጽ ነው) ይሖዋ እንዴት ያለ አፍቃሪና ርኅሩኅ ሰማያዊ አባት ነው!

ኢየሱስ በመቀጠል ይሖዋ ለእነርሱ ያለውን ፍቅራዊ አሳቢነት ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ምሳሌ በመጥቀስ ደቀ መዛሙርቱን አበረታታቸው። “ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን?” ሲል ጠየቀ። “ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ ተቆጥሮአል። እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ።”

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲያውጁ ያዘዛቸው የመንግሥቱ መልእክት አንዳንድ የቤተሰብ አባላት ሲቀበሉት ሌሎቹ ስለማይቀበሉት ቤተሰብን ይከፋፍላል። “በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ” ሲል ኢየሱስ ገልጿል። “ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።” ስለዚህ አንድ የቤተሰብ አባል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመቀበል ድፍረት ይጠይቅበታል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።”

ኢየሱስ መመሪያዎቹን ሲያጠቃልል ደቀ መዛሙርቱን የሚቀበሉ እርሱን እንደሚቀበሉ ገልጿል። “ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ዋጋው አይጠፋበትም።” ማቴዎስ 10:​16-42

▪ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ማስጠንቀቂያዎችን ሰጠ?

▪ ምን ማበረታቻና ማጽናኛ ሰጥቷቸዋል?

▪ የኢየሱስ መመሪያዎች በዘመናችን ባሉ ክርስቲያኖችም ላይ የሚሠሩት ለምንድን ነው?

▪ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከአስተማሪው የማይበልጠው በምን መንገድ ነው?