በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሊቀ ካህናቱ ግቢ የተፈጸመ ክህደት

በሊቀ ካህናቱ ግቢ የተፈጸመ ክህደት

ምዕራፍ 120

በሊቀ ካህናቱ ግቢ የተፈጸመ ክህደት

ጴጥሮስና ዮሐንስ ኢየሱስን በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ጥለውት ከሌሎቹ ሐዋርያት ጋር ከሸሹ በኋላ ሽሽታቸውን አቆሙ። ምናልባትም ኢየሱስን ወደ ሐና ቤት እየወሰዱት ሳለ ሳይደርሱበት አይቀሩም። ሐና ኢየሱስን ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ሲልከው ጴጥሮስና ዮሐንስ በቅርብ ርቀት ተከተሉት። በአንድ በኩል ለራሳቸው ሕይወት በመፍራት በሌላ በኩል ደግሞ ጌታቸው ስለሚደርስበት ነገር በመጨነቅ ልባቸው ለሁለት የተከፈለ ይመስላል።

ወደ ሰፊው የቀያፋ መኖሪያ ቤት ሲደርሱ ዮሐንስ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ስለሆነ ወደ ግቢው መግባት ቻለ። ጴጥሮስ ግን ውጪ በሩ ላይ ቆመ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ዮሐንስ ተመልሶ በር ጠባቂ የነበረችውን አገልጋይ አነጋገራትና ጴጥሮስም እንዲገባ ተፈቀደለት።

ብርድ ስለነበረ የቤቱ አገልጋዮችና የሊቀ ካህናቱ መኮንኖች የከሰል እሳት አንድደዋል። ጴጥሮስ እሳት እየሞቀ የኢየሱስን ጉዳይ እየተመለከተ ያለውን ችሎት ውጤት ለመጠባበቅ ከእነርሱ ጋር ተቀላቀለ። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስን ያስገባችው በር ጠባቂ በእሳቱ ብርሃን በደንብ ተመለከተችው። “አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው።

ጴጥሮስ ማንነቱ በመታወቁ ደንግጦ ኢየሱስን ጭራሽ እንደማያውቀው በመናገር በሁሉም ፊት ካደ። “የምትዪውን አላውቅም አላስተውልምም” አለ።

ከዚያም ጴጥሮስ ወደ በሩ ሄደ። እዚያም ሌላ ሴት አየችውና ቆመው ለነበሩት ሰዎች “ይህ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ” አለቻቸው። ጴጥሮስ “ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ በመማል አሁንም ካደ።

ጴጥሮስ በተቻለ መጠን ራሱን ለመደበቅ በመሞከር እዚያው ግቢው ውስጥ ቆየ። በዚህ ወቅት ሊነጋጋ አካባቢ ዶሮ ሲጮኽ ጴጥሮስ ሳይደነግጥ አልቀረም። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢየሱስን ጉዳይ የሚያየው ችሎት እየተካሄደ ነበር፤ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ችሎቱ እየተካሄደ የነበረው በግቢው ውስጥ ከፍ ብሎ በሚገኘው ቤት ውስጥ ባለ አንድ ክፍል ነው። ጴጥሮስና ሌሎች ከታች ሆነው ሲጠብቁ ምሥክርነት ለመስጠት ይገቡና ይወጡ የነበሩትን የተለያዩ ሰዎች ያዩ እንደነበረ ጥርጥር የለውም።

ሰዎች የጴጥሮስን ማንነት ለይተው ከኢየሱስ ጋር እንደነበረ ለመጨረሻ ጊዜ ከተናገሩ አንድ ሰዓት ገደማ አልፏል። አሁን በአካባቢው ቆመው ከነበሩት መካከል በርከት ያሉ ሰዎች ወደ እሱ መጥተው “አነጋገርህ ይገልጥሃልና በእውነት አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ” አሉት። ከሰዎቹ አንዱ ጴጥሮስ ጆሮውን የቆረጠው የማልኮስ ዘመድ ነበር። “በአትክልቱ ከእርሱ ጋር እኔ አይቼህ አልነበርሁምን?” አለው።

ጴጥሮስ “ሰውየውን አላውቀውም” በማለት አስረግጦ ተናገረ። እንዲያውም እየማለና እየተገዘተ ሁሉም እንደተሳሳቱ ሊያሳምናቸው ሞከረ። የተናገርኩት እውነት ካልሆነ መጥፎ ነገር ይድረስብኝ ማለቱ ነበር።

ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ እንደካደ ዶሮ ጮኸ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ዞር ብሎ አየው። ይህ ሲሆን ኢየሱስ በግቢው ውስጥ ከፍ ብሎ ወደሚገኘው ሰገነት ወጥቶ የነበረ ይመስላል። ወዲያውኑ ጴጥሮስ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ደርብ ላይ በሚገኘው ክፍል ውስጥ እያሉ ኢየሱስ “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለው ቃል ትዝ አለው። ጴጥሮስ በፈጸመው ከባድ ኃጢአት ቅስሙ ተሰብሮ ወደ ውጪ ወጣና ምርር ብሎ አለቀሰ።

ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ጴጥሮስ ስለ መንፈሳዊ ጥንካሬው በጣም እርግጠኛ አልነበረምን? እንዴት ጌታውን በተከታታይ ሦስት ጊዜ ሊክደው ቻለ? ሁኔታዎቹ ጴጥሮስ ፈጽሞ ያልጠበቃቸው እንደነበሩ ጥርጥር የለውም። እውነት ተዛብቶ ነበር፤ ኢየሱስ መጥፎ ወንጀለኛ እንደሆነ ተደርጎ ቀርቦ ነበር። ትክክል የሆነው ነገር ስህተት እንደሆነ ንጹሕ የሆነው ሰው ደግሞ ወንጀለኛ እንደሆነ ተደርጎ ቀርቦ ነበር። ስለዚህ ጴጥሮስ ሁኔታው በፈጠረበት ጭንቀት ሳቢያ ሚዛኑን ሳተ። ለታማኝነት የነበረው ትክክለኛ አመለካከት ድንገት ተናጋ፤ በሰው ፍርሃት ተሽመድምዶ ለከፍተኛ ጸጸት ተዳረገ። ይህ ፈጽሞ አይድረስብን! ማቴዎስ 26:​57, 58, 69-75፤ ማርቆስ 14:​30, 53, 54, 66-72፤ ሉቃስ 22:​54-62፤ ዮሐንስ 18:​15-18, 25-27

▪ ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ እንዲገቡ ሊፈቀድላቸው የቻለው እንዴት ነው?

▪ ጴጥሮስና ዮሐንስ በግቢው ውስጥ ሳሉ በቤቱ ውስጥ ምን እየተካሄደ ነበር?

▪ ዶሮ የጮኸው ስንት ጊዜ ነው? ጴጥሮስ ክርስቶስን አላውቀውም ብሎ የካደውስ ስንት ጊዜ ነው?

▪ ጴጥሮስ መማሉና መገዘቱ ምን ትርጉም አለው?

▪ ጴጥሮስ ኢየሱስን አላውቀውም ብሎ እንዲክድ ያደረገው ምንድን ነው?