በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጨረሻው የማለፍ በዓል ላይ የታየ ትሕትና

በመጨረሻው የማለፍ በዓል ላይ የታየ ትሕትና

ምዕራፍ 113

በመጨረሻው የማለፍ በዓል ላይ የታየ ትሕትና

ጴጥሮስና ዮሐንስ ኢየሱስ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት ለማለፍ በዓሉ ዝግጅት ለማድረግ ቀደም ብለው ኢየሩሳሌም ገብተዋል። ኢየሱስ፣ ከሌሎቹ አሥር ሐዋርያት ጋር ሆኖ ሳይሆን አይቀርም፣ ዘግየት ብሎ ቀኑ መገባደጃ ላይ ደረሰ። ኢየሱስና አብረውት ያሉት ሰዎች ከደብረ ዘይት ተራራ ሲወርዱ ፀሐይዋ በአድማስ በኩል እየጠለቀች ነበር። ኢየሱስ ከሞት እስከተነሣበት ጊዜ ድረስ ከተማዋን በቀን ከዚህ ተራራ ላይ ሆኖ ሲመለከት ይህ የመጨረሻው ጊዜ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስና አብረውት ያሉት ሐዋርያት ወደ ከተማዋ ገቡና የማለፍ በዓሉን ወደሚያከብሩበት ቤት አመሩ። ደረጃዎቹን ወጡና ደርብ ላይ ወደሚገኘው ትልቅ ክፍል ገቡ። በክፍሉ ውስጥ ብቻቸውን ሆነው ለሚያከብሩት የማለፍ በዓል የሚያስፈልጉት ዝግጅቶች ሁሉ ተደርገው ነበር። ኢየሱስ “ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር” ሲል እንደገለጸው ይህን በዓል በጉጉት ሲጠባበቀው ቆይቷል።

በባሕሉ መሠረት በማለፍ በዓሉ ላይ የሚጠጣው አራት ጽዋ ወይን ነው። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ሦስተኛውን ጽዋ ከተቀበለ በኋላ አመሰገነና እንዲህ አላቸው:- “ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት፤ እላችኋለሁና፣ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም።”

ኢየሱስ በእራቱ መካከል ተነሳና ከላይ የደረበውን ልብስ አስቀምጦ ማበሻ ጨርቅ ያዘ፤ ከዚያም በአንድ ጎድጓዳ ሳህን ውስጥ ውኃ ሞላ። በነበረው ልማድ መሠረት የእንግዶች እግር እንዲታጠብ የሚያደርገው ጋባዡ ነው። ሆኖም በዚህ ወቅት በቦታው ጋባዥ ስላልነበረ ኢየሱስ ይህን አገልግሎት ራሱ አከናወነ። ከሐዋርያቱ መካከል አንዳቸው አጋጣሚውን ተጠቅመው ይህን ሊያከናውኑ ይችሉ ነበር፤ ሆኖም አሁንም በመካከላቸው ትንሽ ፉክክር ስላለ ሳይሆን አይቀርም፣ ይህን ያደረገ የለም። አሁን ኢየሱስ እግራቸውን ማጠብ ሲጀምር አፈሩ።

ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ “አንተ የእኔን እግር ከቶ አታጥብም” በማለት ተቃወመው።​— የ1980 ትርጉም

ኢየሱስም “ካላጠብሁህ፣ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም” አለው።

ጴጥሮስ መልሶ “ጌታ ሆይ፣ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም” አለው።

ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰለት:- “የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፣ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፣ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም።” እንዲህ ብሎ የተናገረው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው እንዳሰበ ስላወቀ ነው።

ኢየሱስ አሳልፎ የሚሰጠውን ይሁዳን ጨምሮ የአሥራ ሁለቱንም እግር ካጠበ በኋላ ልብሱን ደርቦ እንደገና ወደ ማዕዱ ተመልሶ ተቀመጠ። ከዚያም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው:- “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ባርያ ከጌታው አይበልጥም፣ መልክተኛም ከላከው አይበልጥም። ይህን ብታውቁ፣ ብታደርጉትም ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናችሁ።”

የትሕትና አገልግሎትን ጎላ አድርጎ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው! ሐዋርያቱ ራሳቸውን በጣም ከፍ አድርገው በመመልከትና ሁልጊዜ በሌሎች ሊገለገሉ እንደሚገባቸው አድርገው በማሰብ ቀዳሚውን ቦታ ለማግኘት መጣጣር የለባቸውም። ኢየሱስ የተወላቸውን ምሳሌ መከተል ይገባቸዋል። ይህ አንድን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለመፈጸም ተብሎ የሚከናወን እግር አጠባ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሥራው ምንም ያህል ዝቅተኛ ወይም የማያስደስት ቢሆንም እንኳ ያላንዳች አድልዎ በፈቃደኝነት የማገልገልን መንፈስ የሚያሳይ ነው። ማቴዎስ 26:​20, 21፤ ማርቆስ 14:​17, 18፤ ሉቃስ 22:​14-18፤ 7:​44፤ ዮሐንስ 13:​1-17

▪ ኢየሱስ የማለፍ በዓልን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ከተማዋን የተመለከተበትን ሁኔታ ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው?

▪ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ የማለፍ በዓሉን በሚያከብሩበት ወቅት ካመሰገነ በኋላ ለአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ያሳለፈው የትኛውን ጽዋ ነው?

▪ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ለእንግዶች ምን አገልግሎት የማቅረብ ልማድ ነበር? ኢየሱስና ሐዋርያቱ የማለፍ በዓሉን ባከበሩበት ጊዜ ይህ አገልግሎት ያልቀረበው ለምን ነበር?

▪ ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ዝቅተኛ አገልግሎት ያከናወነበት ዓላማ ምንድን ነው?