በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጨረሻ የተገለጠባቸው ጊዜያትና በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የዋለው ጰንጠቆስጤ

በመጨረሻ የተገለጠባቸው ጊዜያትና በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የዋለው ጰንጠቆስጤ

ምዕራፍ 131

በመጨረሻ የተገለጠባቸው ጊዜያትና በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የዋለው ጰንጠቆስጤ

ኢየሱስ በሆነ ወቅት ላይ ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ገሊላ ውስጥ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ የሚገናኝበትን ዝግጅት አደረገ። ሌሎች ደቀ መዛሙርትም ስለ ስብሰባው ሳይነገራቸው አልቀረም፤ ስለዚህ ከ500 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተሰበሰቡ። ኢየሱስ ተገልጦ እነርሱን ማስተማር ሲጀምር ስብሰባው ምንኛ አስደሳች ሆኖ ይሆን!

ኢየሱስ በዚያ ለተሰበሰበው ብዙ ሕዝብ ከተናገራቸው ነገሮች መካከል አምላክ በሰማይና በምድር ሥልጣን እንደሰጠው የገለጸበት ሐሳብ ይገኝበታል። “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት አጥብቆ አሳሰባቸው።

እስቲ አስበው! ሁሉም ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ለመካፈል ይህንኑ ተልዕኮ ተቀብለዋል። ተቃዋሚዎች የስብከትና የማስተማር ሥራቸውን ለማስቆም ጥረት የሚያደርጉ ቢሆንም ኢየሱስ “እነሆም አኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት አጽናንቷቸዋል። ኢየሱስ ተከታዮቹ አገልግሎታቸውን መፈጸም እንዲችሉ ለመርዳት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ሁልጊዜ ከእነርሱ ጋር ይሆናል።

ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ሕያው ሆኖ ለደቀ መዛሙርቱ በጠቅላላ ለ40 ቀናት ታይቷል። ለደቀ መዛሙርቱ በተገለጠባቸው በእነዚህ ጊዜያት ስለ አምላክ መንግሥት አስተምሯቸዋል፤ በተጨማሪም የእሱ ደቀ መዛሙርት መሆናቸው የሚያስከትልባቸውን ኃላፊነቶች ጎላ አድርጎ ገልጿል። እንዲያውም አንድ ጊዜ ግማሽ ወንድሙ ለሆነው ለያዕቆብ በመገለጥ በአንድ ወቅት አማኝ ያልነበረው ይህ ሰው ኢየሱስ በእርግጥም ክርስቶስ እንደሆነ እንዲያምን አድርጎታል።

ሐዋርያቱ በገሊላ ሳሉ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ እንዳዘዛቸው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። በኢየሩሳሌም ባገኛቸው ጊዜ እንዲህ አላቸው:- “እኔ የነገርሁአችሁን ከአብ የተሰጠ ተስፋ ጠብቁ እንጂ ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።”

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር እንደገና ተገናኘና ከከተማይቱ አውጥቶ በደብረ ዘይት ተራራ ምሥራቃዊ ዐቀበት ላይ እስከምትገኘው እስከ ቢታንያ ድረስ ይዟቸው ሄደ። የሚያስገርመው ነገር ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተለይቷቸው ወደ ሰማይ እንደሚሄድ የነገራቸው ቢሆንም እንኳ በዚህም ወቅት መንግሥቱ በምድር ላይ ይቋቋማል ብለው ያምኑ ነበር። ስለዚህ “ጌታ ሆይ፣ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት።

ይህን የተሳሳተ አስተሳሰብ እንደገና ለማረም ከመሞከር ይልቅ ኢየሱስ “አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም” በማለት በአጭሩ መለሰላቸው። ከዚያም ሊሠሩት የሚገባውን ሥራ በድጋሚ ጠበቅ አድርጎ በመግለጽ እንዲህ አላቸው:- “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።”

ሐዋርያቱ እያዩ ሳለ ኢየሱስ ወደ ሰማይ መውጣት ጀመረ፤ ከዚያም ደመና ከዓይናቸው ሰወረው። ለብሶት የነበረውን ሥጋዊ አካል በመተው መንፈሳዊ አካል ሆኖ ወደ ሰማይ አረገ። አሥራ አንዱ ወደ ሰማይ ትኩር ብለው እየተመለከቱ ሳሉ ነጫጭ ልብስ የለበሱ 2 ሰዎች አጠገ​ባቸው ብቅ አሉ። እነዚህ ሥጋ የለበሱ መላእክት እንዲህ ሲሉ ጠየቋቸው:- “እናንተ የገሊላ ሰዎች፣ ስለምን ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ቆማችኋል? ይህ ወደ ሰማይ ሲወጣ ያያችሁት ኢየሱስ፣ ወደ ሰማይ ሲወጣ ባያችሁት ዐይነት ተመልሶ ይመጣል።”​— የ1980 ትርጉም

ኢየሱስ ምድርን ለቆ የሄደው በሕዝብ ሆታና እልልታ አይደለም፤ ሲሄድ ያዩት ታማኝ ተከታዮቹ ብቻ ናቸው። ስለዚህ የሚመለሰውም ልክ በዚሁ ዓይነት ሁኔታ ነው። ኢየሱስ ሲመለስ ከፍተኛ የሕዝብ አቀባበል አይደረግለትም። መመለሱንና በመንግሥቱ ሥልጣን ላይ መገኘቱን የሚያስተውሉት ታማኝ ተከታዮቹ ብቻ ናቸው።

አሁን ሐዋርያቱ ከደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወረዱና የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግረው እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ። የኢየሱስን ትእዛዝ በማክበር እዚያው ቆዩ። ከአሥር ቀናት በኋላ በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በተከበረው የአይሁዶች በዓል ላይ 120 ገደማ የሚሆኑ ደቀ መዛሙርት በኢየሩሳሌም በአንድ ደርብ ላይ በሚገኝ ክፍል ውስጥ ተሰብስበው ሳለ በድንገት ኃይለኛ ዓውሎ ነፋስ የመሰለ ድምፅ ቤቱን ሞላው። የእሳት ነበልባል የመሰሉ ነገሮች ታዩአቸው። ከዚያም እዚያ በነበሩት በእያንዳንዳቸው ላይ ሲቀመጡባቸው ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ በተለያዩ ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ። ኢየሱስ ቃል በገባላቸው መሠረት በዚህ መንገድ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው! ማቴዎስ 28:​16-20፤ ሉቃስ 24:​49-52፤ 1 ቆሮንቶስ 15:​5-7፤ ሥራ 1:​3-15፤ 2:​1-4

▪ ኢየሱስ በገሊላ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ የስንብት መመሪያዎች የሰጠው ለእነማን ነው? እነዚህ መመሪያዎችስ ምንድን ናቸው?

▪ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ማጽናኛ ሰጣቸው? ሁልጊዜ ከእነርሱ ጋር የሚሆነውስ እንዴት ነው?

▪ ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ የተገለጠላቸው ለምን ያህል ጊዜ ነው? ምን ትምህርትስ ሰጣቸው?

▪ ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ እሱ ከመሞቱ በፊት ደቀ መዝሙር ላልነበረ ለየትኛው ሰው ተገልጧል?

▪ ኢየሱስ በመጨረሻ ከሐዋርያቱ ጋር የተገናኘባቸው ሁለት ጊዜያት የትኞቹ ናቸው? በእነዚህ ጊዜያትስ ምን ነገር ተከናወነ?

▪ ኢየሱስ በሄደበት ሁኔታ የሚመለሰው እንዴት ነው?

▪ በ33 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ ምን ነገር ተፈጸመ?