በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በምሳሌዎች ማስተማር

በምሳሌዎች ማስተማር

ምዕራፍ 43

በምሳሌዎች ማስተማር

ኢየሱስ ፈሪሳውያንን ያወገዘው በቅፍርናሆም ውስጥ በነበረበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። በኋላ በዚያው ቀን ከቤት ወጣና ብዙ ሰዎች ወደ ተሰበሰቡበት በአቅራቢያው ወደሚገኘው የገሊላ ባሕር ዳርቻ ሄደ። እዚያ ሲደርስ አንድ ጀልባ ላይ ተቀመጠና ጀልባውን ፈቀቅ አድርጎ በባሕሩ ዳርቻ የተሰበሰቡትን ሰዎች ስለ መንግሥተ ሰማያት ማስተማር ጀመረ። ትምህርቱን ይሰጥ የነበረው ተከታታይ የሆኑ ምሳሌዎችን በማቅረብ ነበር። እያንዳንዱ ምሳሌም ሰዎቹ በሚያውቁት ነገር ላይ የተመሠረተ ነበር።

በመጀመሪያ ኢየሱስ ዘርን ስለሚዘራ ሰው ነገራቸው። አንዳንዶቹ ዘሮች በመንገድ ዳር ወደቁና ወፎች በሏቸው። ሌሎቹ ዘሮች በአፈር ላይ ወደቁ፤ ሆኖም ከሥር ትልቅ ዓለት አለ። ገና ለጋ የሆኑት ተክሎች ሥሮቻቸው ጥልቀት ስላልነበራቸው ኃይለኛ ፀሐይ አጠወለጋቸው። ሌሎቹ ዘሮች ደግሞ በእሾህ መካከል ወደቁና ብቅ ሲሉ እሾኹ አነቃቸው። በመጨረሻ አንዳንዶቹ ዘሮች ጥሩ መሬት ላይ ወደቁና መቶ እጥፍ፣ አንዳንዶቹ ስልሳ እጥፍ፣ ሌሎቹ ደግሞ ሠላሳ እጥፍ አፈሩ።

በሌላ ምሳሌ ደግሞ ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ዘር ከሚዘራ ሰው ጋር አመሳስሎታል። ከጊዜ በኋላ ግን ሰውየው ተኝቶ ሲነሳ ዘሩ አድጎ ያገኘዋል። ሰውየው እንዴት እንዳደገ አያውቅም። ራሱ አድጎ ፍሬ ያፈራል። ፍሬው ሲበስል ሰውየው ይሰበስበዋል።

ኢየሱስ ትክክለኛውን ዓይነት ዘር ስለዘራ ሰው የሚገልጽ ሦስተኛ ምሳሌ ተናግሯል። “ሰዎቹ ሲተኙ” ጠላት መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘራ። የሰውየው አገልጋዮች እንክርዳዱን እንቀለው ወይ ብለው ጠየቁት። ሆኖም ሰውየው እንዲህ ሲል መለሰላቸው:- ‘አይሆንም፣ እንክርዳዱን ስትነቅሉ ከስንዴው መካከል አንዳንዱን አንድ ላይ ትነቅሉታላችሁ። እስከ መከር ጊዜ ድረስ አብረው ይደጉ። ከዚያ በኋላ አጫጆቹ እንክርዳዶቹን ለይተው እንዲያቃጥሉና ስንዴውን ወደ ጎተራ እንዲያስገቡ እነግራቸዋለሁ።’

ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ለተሰበሰቡት ሰዎች ንግግሩን በመቀጠል ሁለት ተጨማሪ ምሳሌዎች ተናገረ። “መንግሥተ ሰማያት” ሰው ወስዶ የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት እንደምትመስል ገለጸ። የሰናፍጭ ዘር ከማንኛውም ዘር ያነሰች ብትሆንም ስታድግ ከሁሉም አትክልቶች እንደምትበልጥ ተናገረ። ወፎች በቅርንጫፎችዋ ላይ ለመጠለል ወደ እርስዋ እስኪመጡ ድረስ ትልቅ ዛፍ ትሆናለች።

በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች ከሰናፍጭ ዘሮች የሚያንሱ ዘሮች አሉ በማለት ይህን ይቃወማሉ። ሆኖም ኢየሱስ ስለ አዝርዕትና ተክሎች ትምህርት እየሰጠ አልነበረም። በእሱ ዘመን የነበሩ የገሊላ ሰዎች ያውቋቸው ከነበሩት ዘሮች መካከል በጣም አነስተኛው የሰናፍጭ ዘር ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ አስደናቂ እድገትን አስመልክቶ እያብራራው የነበረውን ጉዳይ መገንዘብ አልተሳናቸውም።

በመጨረሻ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት”ን አንዲት ሴት በሦስት ትልልቅ መስፈሪያ የተሰፈረ ዱቄት ለመለወስ ከተጠቀመችበት እርሾ ጋር አነጻጽሮታል። ከጊዜ በኋላ እርሾው ሊጡን በሙሉ እንደሚያቦካው ገልጿል።

ኢየሱስ እነዚህን አምስት ምሳሌዎች ከሰጠ በኋላ የተሰበሰቡትን ሰዎች አሰናብቶ ወዳረፈበት ቤት ተመለሰ። ብዙም ሳይቆይ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያትና ሌሎች ሰዎች ወደ እሱ መጡ።

ከኢየሱስ ምሳሌዎች ጥቅም ማግኘት

ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ተሰብስበው ለነበሩት ሰዎች ንግግሩን ከሰጠ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ ሲመጡ ኢየሱስ ስለተጠቀመበት አዲስ የማስተማር ዘዴ ለማወቅ ጓጉተው ነበር። ከዚህ ቀደምም በምሳሌዎች ሲጠቀም ሰምተዋል፤ ሆኖም እንደዚህ በስፋት የተጠቀመበት ጊዜ አልነበረም። ስለዚህ “ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” ብለው ጠየቁት።

ይህን ያደረገበት አንዱ ምክንያት “በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ” የሚሉትን የነቢዩን ቃላት ለመፈጸም ነው። ይሁን እንጂ ሌላም ተጨማሪ ምክንያት ነበረው። በምሳሌዎች መጠቀሙ ሰዎች የልብ ዝንባሌያቸውን ገሃድ እንዲያወጡ ለማድረግ መሣሪያ ሆኖ ያገለግል ነበር።

አብዛኞቹ ሰዎች በኢየሱስ የተማረኩት የተዋጣለት ተረት ተናጋሪና ተአምር ሠሪ እንደሆነ አድርገው በመመልከት እንጂ ሊገለገል የሚገባው ጌታ እንደሆነና ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ሊከተሉት እንደሚገባ በማስተዋል አልነበረም። ለነገሮች ያላቸው አመለካከትም ሆነ የአኗኗር መንገዳቸው እንዲለወጥ ፍላጎት አልነበራ​ቸውም። መልእክቱ ያን ያህል ጠልቆ እንዲነካቸው አልፈለጉም።

ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። . . . የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና . . . የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል።”

ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፣ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም።”

አዎን፣ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያትና ከእነርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ተቀባይ ልብ ነበራቸው። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፣ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም” ሲል ተናግሯል። ደቀ መዛሙርቱ ትርጉሙን ማወቅ ፈልገው ስለነበረ ኢየሱስ የዘሪውን ምሳሌ አብራራላቸው።

ኢየሱስ “ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው” አለ፤ አፈሩ ደግሞ ልብ ነው። በመንገድ ዳር በጠጣሩ መሬት ላይ ስለተዘራው ዘር ሲገልጽ እንዲህ አለ:- “ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።”

በሌላ በኩል ደግሞ ከሥሩ ትልቅ ዓለት ባለበት መሬት ላይ የተዘራው ዘር ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ሰዎችን ያመለክታል። ይሁን እንጂ ቃሉ በእንዲህ ዓይነት ልቦች ውስጥ ሥር መስደድ ስለማይችል እነዚህ ሰዎች ፈተና ወይም ስደት ሲመጣ ይወድቃሉ።

ኢየሱስ በመቀጠል በእሾህ መካከል ስለወደቀው ዘር ሲናገር ይህ ቃሉን የሰሙ ሰዎችን እንደሚያመለክት ገልጿል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ባለው የኑሮ ጭንቀት፣ ሀብትና ተድላ ስለሚታለሉ ሙሉ በሙሉ ይታነቃሉ፤ በመሆኑም ለፍሬ የሚያበቁት ምንም ነገር የለም።

በመጨረሻም በመልካም መሬት ላይ የተዘራው ዘር ቃሉን በመልካምና በጥሩ ልብ ሰምተው በልቦናቸው የሚያሳድሩና ጸንተው ፍሬ የሚያፈሩ ሰዎች እንደሆኑ ኢየሱስ ገልጿል።

የኢየሱስን ትምህርቶች ማብራሪያ ለማግኘት ሲሉ እሱን ፍለጋ የሄዱት እነዚህ ደቀ መዛሙርት ምንኛ ተባርከዋል! ኢየሱስ ሰዎች ምሳሌዎቹን ተረድተው እውነትን እንዲያውቁ ይፈልግ ነበር። “መብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን?” ሲል ጠይቋል። እንደዚያ አያደርጉም፤ ከዚህ ይልቅ ‘በመቅረዝ ላይ ያኖሩታል።’ በመሆኑም ኢየሱስ “እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ” ሲል አክሎ ተናግሯል።

ተጨማሪ ትምህርት በማግኘት ተባርከዋል

ኢየሱስ ስለ ዘሪው ምሳሌ የሰጠውን ማብራሪያ ካዳመጡ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ፈለጉ። “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጉምልን” ብለው ጠየቁት።

የደቀ መዛሙርቱ ሁኔታ በባሕሩ ዳርቻ ተሰብስበው የነበሩት ሌሎች ሰዎች ከነበራቸው ሁኔታ ምንኛ የተለየ ነበር! እነዚያ ሰዎች በደፈናው በምሳሌዎቹ ብቻ በመርካት ከበስተጀርባ ያለውን ትርጉም የማወቅ ጉጉት ሳያሳዩ ቀርተዋል። ኢየሱስ በባሕሩ አጠገብ ሆነው ያዳምጡት የነበሩትን ሰዎች እሱ ወዳለበት ቤት ከመጡት የማወቅ ጉጉት ከነበራቸው ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማወዳደር እንዲህ አለ:-

“በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል ለእናንተም ይጨመርላችኋል።” ደቀ መዛሙርቱ ለኢየሱስ ልባዊ ፍላጎትና ትኩረት አሳይተውት ወይም ሰፍረውለት ነበር፤ በመሆኑም ተጨማሪ ትምህርት በማግኘት ተባርከዋል። ስለዚህ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ላቀረቡት ጥያቄ መልስ በመስጠት እንዲህ ሲል ገለጸ:-

“መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፣ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፣ አጫጆችም መላእክት ናቸው።”

ኢየሱስ እያንዳንዱን የምሳሌውን ገጽታ ለይቶ ከገለጸ በኋላ ውጤቱን ተናገረ። በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ላይ አጫጆቹ ወይም መላእክት እንክርዳድ መሰል የሆኑትን አስመሳይ ክርስቲያኖች ከእውነተኛዎቹ “የመንግሥት ልጆች” ይለዩአቸዋል። ከዚያም “የክፉው ልጆች” ጥፋት ይደርስባቸዋል፤ “ጻድቃን” የሆኑት የአምላክ መንግሥት ልጆች ግን በአባታቸው መንግሥት በድምቀት ያበራሉ።

ኢየሱስ በመቀጠል ሦስት ተጨማሪ ምሳሌዎችን በመስጠት የማወቅ ጉጉት የነበራቸውን ደቀ መዛሙርቱን ባርኳቸዋል። በመጀመሪያ እንዲህ አለ:- “መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተሰወረን መዝገብ ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሰወረው፣ ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያን እርሻ ገዛ።”

ቀጥሎም እንዲህ አለ:- “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።”

ኢየሱስ ራሱ የተሰወረ መዝገብ ያገኘው ሰውና ከፍተኛ ዋጋ ያለው ዕንቁ ያገኘው ነጋዴ ያሳዩትን ዓይነት አቋም አሳይቷል። በሰማይ የነበረውን የተከበረ ቦታ ትቶ ተራ ሰው ሲሆን ያለውን ነገር ሁሉ ሸጧል ማለት ይቻላል። ከዚያም ሰው ሆኖ በምድር ላይ ሲኖር ዘለፋና በጥላቻ የተጠነሰሰ ስደት በመቀበል የአምላክ መንግሥት ገዥ የመሆን ብቃት እንዳለው አስመስክሯል።

የኢየሱስ ተከታዮችም ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች ወይም ደግሞ የመንግሥቱ ምድራዊ ተገዥ የመሆን ታላቅ ሽልማት ለማግኘት ያላቸውን ነገር ሁሉ የመሸጥ ፈተና ከፊታቸው ተቀምጧል። በአምላክ መንግሥት ውስጥ ተካፋይ መሆን በሕይወት ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ዋጋማ የሆነ ውድ ሀብት ወይም ውድ ዕንቁ እንደሆነ አድርገን እንመለከተዋለንን?

በመጨረሻም ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት” ሁሉንም ዓይነት ዓሣ ከሰበሰበ መረብ ጋር እንደሚመሳሰል ገልጿል። ዓሦቹ በሚለዩበት ጊዜ ተስማሚ ያልሆኑት ይጣላሉ፤ ጥሩዎቹ ግን ይቀመጣሉ። ኢየሱስ በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ላይ ይህ እንደሚፈጸም ተናግሯል። መላእክት ክፉዎችን ከጻድቃን በመለየት ክፉዎቹ ለጥፋት ተጠብቀው እንዲቆዩ ያደርጋሉ።

ኢየሱስ የመጀመሪያዎቹን ደቀ መዛሙርት “ሰዎችን አጥማጆች” እንዲሆኑ በመጥራት ይህን ዓሣ የማጥመድ ሥራ ራሱ ጀምሯል። ዓሣ የማጥመዱ ሥራ በመላእክት የበላይ ተቆጣጣሪነት ለብዙ ዘመናት ሲካሄድ ቆይቷል። በመጨረሻ የቅቡዓን ክርስቲያኖችን ጉባኤ ጨምሮ ክርስቲያን ነን የሚሉ በምድር ላይ ያሉ ድርጅቶችን ሁሉ የሚወክለው “መረብ” ተጎትቶ የሚወጣበት ጊዜ ደረሰ።

ተስማሚ ያልሆኑት ዓሦች ወደ ጥፋት የሚጣሉ ቢሆንም እንኳ ‘መልካሞቹ ዓሦች’ የሚቀመጡ መሆናቸው የሚያስደስት ነው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተጨማሪ እውቀትና ማብራሪያ ለማግኘት ያሳዩትን ዓይነት ልባዊ ፍላጎት በማሳየት ተጨማሪ ትምህርት በማግኘት ብቻ ሳይሆን አምላክ የሚሰጠውን ዘላለማዊ ሕይወት በማግኘትም እንባረካለን። ማቴዎስ 13:​1-52፤ ማርቆስ 4:​1-34፤ ሉቃስ 8:​4-18፤ መዝሙር 78:​2፤ ኢሳይያስ 6:​9, 10

▪ ኢየሱስ ምሳሌዎች በመጠቀም ለሕዝቡ ንግግር የሰጠው መቼና የት ነበር?

▪ ኢየሱስ ለሕዝቡ የትኞቹን አምስት ምሳሌዎች ተናግሯል?

▪ ኢየሱስ የሰናፍጭ ዘር ከሁሉም ዘሮች አነስተኛ ነው ያለው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ በምሳሌዎች የተናገረው ለምንድን ነው?

▪ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከሕዝቡ የተለዩ እንደሆኑ ያሳዩት እንዴት ነበር?

▪ ኢየሱስ የዘሪውን ምሳሌ በተመለከተ ምን ማብራሪያ ሰጠ?

▪ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በባሕሩ ዳርቻ ተሰብስበው ከነበሩት ሰዎች የተለየ ዝንባሌ ያሳዩት እንዴት ነው?

▪ በዘሪው፣ በእርሻው፣ በመልካሙ ዘር፣ በጠላት፣ በመከሩና በአጫጆቹ የተመሰሉት እነማን ወይም ምን ነገሮች ናቸው?

▪ ኢየሱስ የትኞቹን ሦስት ተጨማሪ ምሳሌዎች ተናገረ? ከእነዚህ ምሳሌዎችስ ምን ልንማር እንችላለን?