በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሰንበት መልካም ሥራ መሥራት

በሰንበት መልካም ሥራ መሥራት

ምዕራፍ 29

በሰንበት መልካም ሥራ መሥራት

ጊዜው 31 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የጸደይ ወራት ነው። ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እየተመለሰ በነበረበት ጊዜ በሰማርያ በሚገኘው የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ሴትዮዋን ካነጋገራት ጥቂት ወራት አልፈዋል።

ኢየሱስ በመላዋ ገሊላ በስፋት ሲያስተምር ከቆየ በኋላ አሁን ወደ ይሁዳ ተመልሶ ሄደ። እዚያም በምኩራቦች ውስጥ ሰበከ። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በገሊላ ስላከናወነው አገልግሎት ከሰጠው ትኩረት አንጻር ሲታይ ኢየሱስ በአሁኑ ጉዞውም ሆነ ቀደም ሲል ከተከበረው የማለፍ በዓል በኋላ ባሳለፋቸው ወራት በይሁዳ ስላከናወነው ነገር የሚሰጠው መግለጫ በጣም አነስተኛ ነው። የኢየሱስ አገልግሎት በገሊላ ውስጥ ያገኘውን ያህል ጥሩ ተቀባይነት በይሁዳ ውስጥ እንዳላገኘ ከዚህ መረዳት ይቻላል።

ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ በ31 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በሚከበረው የማለፍ በዓል ላይ ለመገኘት የይሁዳ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ። በዚያም በከተማይቱ የበጎች በር አጠገብ ቤተ ሳይዳ የሚባል አንድ ኩሬ ነበረ። ብዙ በሽተኞች፣ ዓይነ ስውሮችና አንካሶች ወደዚህ ኩሬ ይመጡ ነበር። ሰዎች ውኃው በሚናወጥበት ጊዜ ውኃው ውስጥ በመግባት ፈውስ ማግኘት ይቻላል ብለው ያምኑ ነበር።

ዕለቱ የሰንበት ቀን ነበር፤ ኢየሱስ ለ38 ዓመታት ታሞ የቆየ አንድ ሰው በኩሬው አጠገብ አየ። የሰውየው በሽታ ለረጅም ጊዜ የቆየ መሆኑን በመገንዘብ ኢየሱስ “ልትድን ትወዳለህን?” ሲል ጠየቀው።

ሰውየውም እንዲህ ሲል ለኢየሱስ መለሰለት:- “ጌታ ሆይ፣ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል።”

ኢየሱስም “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው። ሰውየው ወዲያውኑ ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ!

ሆኖም አይሁዶች ሰውየውን ሲያዩ “ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም” አሉት።

ሰውየውም “ያዳነኝ ያ ሰው:- አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” ብሎ መለሰላቸው።

“አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። በቦታው ብዙ ሕዝብ ስለነበረ ኢየሱስ ከአካበቢው ዞር ብሎ ነበር። የተፈወሰው ሰው ደግሞ የኢየሱስን ስም አያውቀውም ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ኢየሱስና ሰውየው በቤተ መቅደሱ ተገናኙ፤ በዚህ ጊዜ ሰውየው የፈወሰው ማን እንደሆነ አወቀ።

ሰውየው ያዳነው ኢየሱስ እንደሆነ ሄዶ ለአይሁድ ነገራቸው። አይሁድ ይህን ሲሰሙ ወደ ኢየሱስ ሄዱ። ወደእሱ የሄዱት ለምን ነበር? እነዚህን ተአምራት የሚፈጽመው በምን መንገድ እንደሆነ ለማወቅ ፈልገው ነውን? አይደለም። እነዚህን መልካም ነገሮች በሰንበት በመፈጸሙ እሱን ለመንቀፍ ብለው ነው። እንዲያውም እሱን ማሳደድ ጀመሩ! ሉቃስ 4:​44 የ1980 ትርጉምዮሐንስ 5:​1-16

▪ ኢየሱስ ይሁዳን ለቆ ከሄደ ምን ያህል ጊዜ ሆኖት ነበር?

▪ ቤተ ሳይዳ ወደተባለው ኩሬ ብዙ ሰው ይሄድ የነበረው ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ በኩሬው አጠገብ ምን ተአምር ፈጸመ? አይሁዶች ያሳዩት ምላሽስ ምን ነበር?