በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሰንበት የተፈቀደው ምንድን ነው?

በሰንበት የተፈቀደው ምንድን ነው?

ምዕራፍ 32

በሰንበት የተፈቀደው ምንድን ነው?

ኢየሱስ በሌላ የሰንበት ቀን በገሊላ ባሕር አቅራቢያ ወደሚገኝ አንድ ምኩራብ ሄደ። በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበር። ጻፎችና ፈሪሳውያን ኢየሱስ ይፈውሰው እንደሆነና እንዳልሆነ ለማየት በትኩረት ይከታተሉ ነበር። በመጨረሻም “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ብለው ጠየቁት።

የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በሰንበት መፈወስ የሚቻለው ሕይወት አስጊ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ጊዜ ብቻ ነው ብለው ያምኑ ነበር። ለምሳሌ ያህል በሰንበት አጥንትን መጠገን ወይም ወለምታን በጨርቅ ማሰር ክልክል ነው ብለው ያስተምሩ ነበር። ስለዚህ ጻፎችና ፈሪሳውያን ኢየሱስን የጠየቁት ሊከሱት ፈልገው ስለነበረ ነው።

ይሁን እንጂ ኢየሱስ አስተሳሰባቸውን አውቆ ነበር። በተጨማሪም ሥራን የሚከለክለው የሰንበት ቀን ሕግ ተጣሰ የሚባለው ምን ሲደረግ እንደሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነና ከልክ ያለፈ አመለካከት እንደያዙ ተገንዝቦ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ እጁ የሰለለበትን ሰው “ተነሥተህ ወደ መካከል ና” ብሎ በመጥራት የጦፈ ክርክር የሚካሄድበት መድረክ ከፈተ።

ኢየሱስ ወደ ጻፎችና ፈሪሳውያን ዞር ብሎ እንዲህ አለ:- “ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፣ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው?” በግ በድካም የሚገኝ ንብረት በመሆኑ እስከሚቀጥለው ቀን ድረስ እዚያው ጉድጓድ ውስጥ እንዲቆይ አይተዉትም፤ ምናልባትም ሊታመምና ሊሞትባቸው ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ቅዱሳን ጽሑፎች “ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል” ይላሉ።

ኢየሱስ ከዚህ ጋር በማነጻጸር እንዲህ አለ:- “እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል።” የሃይማኖት መሪዎቹ ይህን ምክንያታዊና ርኅራኄ የተሞላበት አነጋገር ማስተባበል ስላልቻሉ ዝም አሉ።

ኢየሱስ ክፉኛ በተጠናወታቸው ድንቁርና በማዘንና በቁጣ መንፈስ ዙሪያውን ተመለከተ። ከዚያም ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየው እጁን ዘረጋ፤ እጁም ተፈወሰ።

ፈሪሳውያን የሰውየው እጅ ወደ ቀድሞ ሁኔታው በመመለሱ መደሰት ሲገባቸው ወዲያውኑ ሄደው ከሄሮድስ የፖለቲካ ቡድን ተከታዮች ጋር ኢየሱስን ለመግደል አሴሩ። ይህ የፖለቲካ ቡድን ሰዱቃውያን የሚባሉትን የሃይማኖት ሰዎች በአባልነት ያቀፈ ነበር። ለነገሩ ይህ የፖለቲካ ቡድንና ፈሪሳውያን በመካከላቸው ግልጽ የሆነ ቅራኔ ነበራቸው፤ ሆኖም በኢየሱስ ላይ በነበራቸው ተቃውሞ ረገድ ጠንካራ አንድነት ፈጠሩ። ማቴዎስ 12:​9-14፤ ማርቆስ 3:​1-6፤ ሉቃስ 6:​6-11፤ ምሳሌ 12:​10፤ ዘጸአት 20:​8-10

▪ በኢየሱስና በአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች መካከል የተካሄደው የጦፈ ክርክር ምን ይመስል ነበር?

▪ እነዚህ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በሰንበት ቀን መፈወስን በተመለከተ ምን እምነት ነበራቸው?

▪ ኢየሱስ አመለካከታቸው ስህተት መሆኑን ለማስረዳት ምን ምሳሌ ተጠቀመ?