በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቃና የፈጸመው ሁለተኛው ተአምር

በቃና የፈጸመው ሁለተኛው ተአምር

ምዕራፍ 20

በቃና የፈጸመው ሁለተኛው ተአምር

ኢየሱስ ረዘም ላለ ጊዜ በይሁዳ ሰፊ የስብከት ዘመቻ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ወደ መኖሪያ ክልሉ የተመለሰው ለዕረፍት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ባደገበት በገሊላ ምድር ከዚያ የበለጠ አገልግሎት ማከናወን ጀመረ። ደቀ መዛሙርቱ ግን ከእሱ ጋር ከመቆየት ይልቅ ወደየቤተሰቦቻቸውና ቤታቸው ተመልሰው የቀድሞ ሥራቸውን ማከናወን ቀጠሉ።

ታዲያ ኢየሱስ ምን የሚል መልእክት መስበክ ጀመረ? ኢየሱስ መስበክ የጀመረው “የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ” የሚለውን መልእክት ነበር። የተገኘውስ ምላሽ ምን ነበር? የገሊላ ሰዎች ኢየሱስን ተቀበሉት። ሁሉም በአክብሮት ይመለከቱት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ የሆነው ይሰብከው በነበረው መልእክት ምክንያት ሳይሆን ብዙዎቹ ከተወሰኑ ወራት በፊት በኢየሩሳሌም በተከበረው የማለፍ በዓል ላይ ተገኝተው ስለነበረ ኢየሱስ የፈጸማቸውን አስደናቂ ምልክቶች በማየታቸው ነው።

ኢየሱስ በገሊላ ያከናወነውን ታላቅ አገልግሎት የጀመረው በቃና ሳይሆን አይቀርም። ቀደም ሲል ከይሁዳ ሲመለስ እዚያ ተደግሶ በነበረ አንድ ሠርግ ላይ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ እንደለወጠ ታስታውስ ይሆናል። ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ቃና በመጣበት በዚህ ወቅት ደግሞ አንድ የንጉሥ ሄሮድስ አንጢጳስ የመንግሥት ባለ ሥልጣን ልጅ በጣም ታሞ ነበር። ባለ ሥልጣኑ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ቃና መምጣቱን ስለ ሰማ ኢየሱስን ለማግኘት ቅፍርናሆም ከሚገኘው ቤቱ ተነስቶ መጣ። በጣም ያዘነው ይህ ሰው ‘እባክህ ልጄ ሳይሞት በፍጥነት እንሂድ’ ብሎ ለመነው።

ኢየሱስም ‘ወደ ቤት ተመለስ። ልጅህ ተፈውሷል!’ አለው። የሄሮድስ ባለ ሥልጣን የኢየሱስን ቃል አምኖ ወደ ቤቱ ለመመለስ ረጅሙን ጉዞ ተያያዘው። ልጁ እንደ ዳነ ሊነግሩት የቸኮሉትን አገልጋዮቹን መንገድ ላይ አገኛቸው። ‘የተሻለው መቼ ነው?’ ሲል ጠየቃቸው።

‘ትናንት ከቀኑ በሰባት ሰዓት’ ብለው መለሱለት።

ባለ ሥልጣኑ ልጁ የዳነው ኢየሱስ ‘ልጅህ ተፈውሷል!’ ባለው ሰዓት እንደ ሆነ ተገነዘበ። ከዚያ በኋላ ሰውዬውና መላው ቤተሰቡ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆኑ።

በዚህ መንገድ ቃና ኢየሱስ ከይሁዳ መመለሱን የሚያመለክቱ ሁለት ተአምራት የፈጸመባት ልዩ አጋጣሚ ያገኘች ቦታ ለመሆን በቅታለች። እርግጥ፣ ኢየሱስ እስከዚህ ባለው ጊዜ ውስጥ የፈጸማቸው ተአምራት እነዚህ ብቻ አይደሉም። ሆኖም ወደ ገሊላ መመለሱን የሚያመለክቱ በመሆናቸው ጎላ ያለ ትርጉም አላቸው።

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወዳደገባት ከተማ ወደ ናዝሬት ሄደ። እዚያስ ምን ያጋጥመው ይሆን? ዮሐንስ 4:​43-54፤ ማርቆስ 1:​14, 15፤ ሉቃስ 4:⁠14, 15

▪ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሲመለስ ደቀ መዛሙርቱ ምን አደረጉ? ሰዎችስ እንዴት ተቀበሉት?

▪ ኢየሱስ ምን ተአምር ፈጸመ? ይህስ በሰዎቹ ላይ ምን ለውጥ አስከተለ?

▪ በዚህ መንገድ ቃና ልዩ አጋጣሚ ያገኘችው እንዴት ነው?