በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቅፍርናሆም የተፈጸሙ ተጨማሪ ተአምራት

በቅፍርናሆም የተፈጸሙ ተጨማሪ ተአምራት

ምዕራፍ 23

በቅፍርናሆም የተፈጸሙ ተጨማሪ ተአምራት

ኢየሱስ የመጀመሪያዎቹን አራት ደቀ መዛሙርት ማለትም ጴጥሮስን፣ እንድርያስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ከጠራ በኋላ በነበረው የሰንበት ቀን ሁሉም በቅፍርናሆም ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ምኩራብ ሄዱ። በዚያም ኢየሱስ ማስተማር ጀመረ። እንደ ጻፎች ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ስለነበር ሰዎቹ በጣም ተገረሙ።

በዚህ የሰንበት ቀን አንድ ጋኔን የያዘው ሰው በቦታው ተገኝቶ ነበር። ትንሽ እንደቆየ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፣ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፣ የእግዚአብሔር ቅዱሱ” ብሎ በኃይል ጮኸ።

ሰውየውን የያዘው ጋኔን ከሰይጣን መላእክት አንዱ ነበር። ኢየሱስ ጋኔኑን በመገሰጽ “ዝም በል ከእርሱም ውጣ!” አለው።

ጋኔኑ ሰውየውን ጥሎ አንፈራገጠውና በኃይል ጮኸ። ሆኖም ሰውየውን ምንም ሳይጎዳው ለቀቀው። በዚያ የነበሩት ሰዎች በሙሉ በጣም ተገረሙ! “ይህ ምንድር ነው?” ብለው ተጠያየቁ። “በሥልጣን ርኩሳን መናፍስትን ያዝዛል እነርሱም ይታዘዙለታል።” ወሬው በአካባቢው ሁሉ ተዳረሰ።

ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከምኩራቡ ወጥተው ወደ ስምዖን ወይም ጴጥሮስ ቤት ሄዱ። እዚያም የጴጥሮስ አማት በጣም ታማ ኃይለኛ ትኩሳት ይዟት ነበር። ‘እባክህ እርዳት’ ብለው ለመኑት። ስለዚህ ኢየሱስ ወደ እሷ ሄደና እጅዋን ይዞ አስነሣት። ወዲያው ተፈወሰችና ለእነርሱ ምግብ ማዘጋጀት ጀመረች!

ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ከየቦታው ብዙዎች የታመሙባቸውን ሰዎች እየያዙ ወደ ጴጥሮስ ቤት መጉረፍ ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ የከተማው ሰው ሁሉ ደጃፉ ላይ ተሰበሰበ! ኢየሱስ በሽታቸው ምንም ይሁን ምን የታመሙትን ሁሉ ፈወሰ። አልፎ ተርፎም ጋኔን የያዛቸውን ነፃ አወጣ። አጋንንቱን ሲያስወጣቸው “የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” እያሉ ይጮኹ ነበር። ሆኖም ክርስቶስ እንደሆነ አውቀው ስለነበር ኢየሱስ ገሠጻቸውና እንዳይናገሩ ከለከላቸው። ማርቆስ 1:​21-34፤ ሉቃስ 4:​31-41፤ ማቴዎስ 8:​14-17

▪ ኢየሱስ አራቱን ደቀ መዛሙርቱን ከጠራ በኋላ በነበረው የሰንበት ቀን በምኩራቡ ውስጥ ምን ተከናወነ?

▪ ኢየሱስ ከምኩራቡ ከወጣ በኋላ ወዴት ሄደ? እዚያስ ምን ተአምር ፈጸመ?

▪ በዚያው ምሽት ቆየት ብሎ ምን ነገር ተከናወነ?