በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቤተ መቅደሱ ያከናወነው አገልግሎት ተፈጸመ

በቤተ መቅደሱ ያከናወነው አገልግሎት ተፈጸመ

ምዕራፍ 110

በቤተ መቅደሱ ያከናወነው አገልግሎት ተፈጸመ

ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ በቤተ መቅደሱ የተገኘው በዚህ ዕለት ነው። እንዲያውም በምድር ላይ ያከናወነውን ሕዝባዊ አገልግሎት እያጠናቀቀ ነው፤ ከዚህ በኋላ የቀሩ ነገሮች ቢኖሩ ከሦስት ቀናት በኋላ ፍርድ ፊት ቀርቦ ሲገደል የሚፈጸሙት ሁኔታዎች ናቸው። አሁን ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ማውገዙን ቀጠለ።

እንደገና ሦስት ጊዜ “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፣ . . . ወዮላችሁ” ሲል ተናገረ። በመጀመሪያ ወዮላችሁ ያላቸው “በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ” ያጠሩ ስለነበረ ነው። ስለዚህ “ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ” በማለት አጥብቆ መከራቸው።

ከዚህ በመቀጠል ጻፎችና ፈሪሳውያን በውስጥ ያለውን የተበላሸና የበሰበሰ ነገር ከውጪ በሚታይ የሃይማኖተኛነት ሽፋን ለመደበቅ በመሞከራቸው ወዮላችሁ ሲል አስጠነቀቃቸው። “በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጥ ግን የሙታን አጥንት ርኲሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን” ትመስላላችሁ አላቸው።

በመጨረሻም፣ ምጽዋታቸው የሰዎችን ትኩረት እንዲስብ ለማድረግ ሲሉ ለነቢያት መቃብሮች መሥራታቸውና መቃብሮቹን ማስጌጣቸው ግብዝነታቸውን የሚያንጸባርቅ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እንደገለጸው እነርሱ “የነቢያት ገዳዮች ልጆች” ናቸው። በእርግጥም ግብዝነታቸውን ለማጋለጥ የደፈረ ማንኛውም ሰው ሕይወቱ አደጋ ላይ ይወድቃል!

ኢየሱስ በመቀጠል እጅግ ኃይለኛ ቃላት በመጠቀም አወገዛቸው። “እናንተ እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች፣” አላቸው፤ “ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?” ገሃነም የኢየሩሳሌም ቆሻሻ የሚጣልበት ሸለቆ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ጻፎችና ፈሪሳውያን መጥፎ ጎዳና በመከተላቸው ዘላለማዊ ጥፋት እንደሚደርስባቸው መናገሩ ነበር።

ኢየሱስ ወኪሎቹ አድርጎ ስለሚልካቸው ሰዎች ሲናገር እንዲህ አለ:- “ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፣ ከእነርሱም በምኲራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ [በሁለተኛ ዜና ላይ ዮዳሄ ተብሏል] ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ። እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።”

የእስራኤል መሪዎች ዘካርያስ ስለነቀፋቸው “ተማማሉበትም በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ወገሩት።” ሆኖም ኢየሱስ በተነበየው መሠረት እስራኤል በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ለፈሰሰው የጻድቃን ደም ሁሉ የእጅዋን ማግኘቷ የማይቀር ነበር። ከ37 ዓመታት በኋላ በ70 እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ኢየሩሳሌም በሮማ ሠራዊት ስትጠፋና ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ አይሁዶች ሲገደሉ ቅጣታቸውን ተቀብለዋል።

ኢየሱስ ይህን አሰቃቂ ሁኔታ ሲያስበው በጣም አዘነ። አሁንም በድጋሚ እንዲህ አለ:- “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፣ . . . ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ፣ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።”

ከዚያም ኢየሱስ “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም” ሲል አክሎ ተናገረ። ይህ የሚሆነው ክርስቶስ ሰማያዊ መንግሥቱን በመውረስ በሥልጣኑ ላይ በሚገኝበት ጊዜ ነው፤ በዚያን ጊዜ ሰዎች በእምነት ዓይን ያዩታል።

አሁን ኢየሱስ በመቅደሱ ውስጥ ያሉትን የገንዘብ መዋጮ የሚደረግባቸው ዕቃዎችና ዕቃዎቹ ውስጥ ገንዘብ የሚከቱትን ሰዎች ማየት ወደሚችልበት ቦታ ሄደ። ሀብታሞቹ ብዙ ሳንቲሞች ይከቱ ነበር። ሆኖም አንዲት ድሀ መበለት መጣችና ምንም ያህል ዋጋ የሌላቸው ሁለት ሳንቲሞች ከተተች።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠራና “እውነት እላችኋለሁ፣ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች” አላቸው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ብለው ሳያስቡ አልቀረም። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገለጸላቸው:- “ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፣ ይህች ግን ከጒድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች።” ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ቤተ መቅደሱን ለመጨረሻ ጊዜ ለቆ ሄደ።

ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በቤተ መቅደሱ ስፋትና ውበት በመደነቅ “መምህር ሆይ፣ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ” አለው። በእርግጥም ድንጋዮቹ ርዝመታቸው ከ11 ሜትር በላይ እንደሆነ፣ ወርዳቸው ከ5 ሜትር እንደሚበልጥና ከፍታቸው ከ3 ሜትር በላይ እንደሆነ ይነገራል!

ኢየሱስ ‘እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያላችሁን?’ ሲል መለሰላቸው። “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም።”

ኢየሱስና ሐዋርያቱ ይህን ከተነጋገሩ በኋላ የቄድሮንን ሸለቆ አቋርጠው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። እዚያ ላይ ሆነው በጣም የሚያምረውን ቤተ መቅደስ ቁልቁል መመልከት ይችላሉ። ማቴዎስ 23:​25 እስከ 24:​3፤ ማርቆስ 12:​41 እስከ 13:​3፤ ሉቃስ 21:​1-6፤ 2 ዜና መዋዕል 24:​20-22

▪ ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ቤተ መቅደሱ በሄደበት ወቅት ምን አከናውኗል?

▪ የጻፎቹና የፈሪሳውያኑ ግብዝነት በግልጽ የታየው እንዴት ነው?

▪ የ“ገሃነም ፍርድ” ማለት ምን ማለት ነው?

▪ ኢየሱስ መበለቷ ከሀብታሞቹ የበለጠ መዋጮ እንዳደረገች የተናገረው ለምንድን ነው?