በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በብልህነት የወደፊቱን ኑሮ ማመቻቸት

በብልህነት የወደፊቱን ኑሮ ማመቻቸት

ምዕራፍ 87

በብልህነት የወደፊቱን ኑሮ ማመቻቸት

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣ አታላዮቹን ቀረጥ ሰብሳቢዎች፣ ሌሎች የታወቁ ኃጢአተኞችን፣ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ጨምሮ ለሕዝቡ ስለ አባካኙ ልጅ የሚገልጸውን ታሪክ ገና ተናግሮ መጨረሱ ነው። አሁን ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ቤቱ አስተዳዳሪ ወይም መጋቢ መጥፎ ወሬ የሰማን ሀብታም ሰው በተመለከተ አንድ ምሳሌ ነገራቸው።

ኢየሱስ እንደገለጸው ሀብታሙ ሰው መጋቢውን ጠርቶ ሊያባርረው መሆኑን ነገረው። “ጌታዬ መጋቢነቱን ከእኔ ይወስዳልና ምን ላድርግ?” ሲል መጋቢው አሰበ። “ለመቆፈር ኃይል የለኝም፣ መለመንም አፍራለሁ። ከመጋቢነቱ ብሻር በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን አውቃለሁ አለ።”

መጋቢው ያቀደው ነገር ምን ይሆን? ከጌታው የተበደሩትን ሰዎች ጠራ። “ምን ያህል ዕዳ አለብህ?” ሲል የመጀመሪያውን ጠየቀው።

ሰውየውም መልሶ ‘2,200 ሊትር ዘይት’ ሲል ተናገረ።

‘መዝገብህን እንካ ፈጥነህም ተቀምጠህ 1,100 ብለህ ጻፍ’ አለው።

ሌላውን ደግሞ ‘አንተስ ስንት ዕዳ አለብህ?’ ብሎ ጠየቀው።

እርሱም መልሶ ‘630 መስፈሪያ ስንዴ’ አለ።

‘መዝገብህን እንካ 504 ብለህም ጻፍ’ አለው።

መጋቢው አሁንም ቢሆን በጌታው ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ላይ ኃላፊ በመሆኑ ከጌታው የተበደሩትን ሰዎች ዕዳ የመቀነስ መብት አለው። የዕዳቸውን መጠን በመቀነስ እሱ ከሥራው በሚባረርበት ጊዜ ውለታ ሊመልሱለት ከሚችሉት ሰዎች ጋር እየተወዳጀ ነበር።

ጌታው ያደረገውን ነገር ሲሰማ ተደነቀ። እንዲያውም “ዓመፀኛውን መጋቢ በልባምነት ስላደረገ አመሰገነው።” (ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) ኢየሱስ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል:- “የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸው።”

ኢየሱስ ምሳሌው የሚያስተላልፈውን ትምህርት ለደቀ መዛሙርቱ በመግለጽ እንዲህ ሲል አበረታታቸው:- “የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፣ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ።”

ኢየሱስ መጋቢውን ያሞገሰው በዓመፀኝነቱ ሳይሆን በአርቆ አስተዋይነቱ ማለትም በብልህነቱ ነው። ብዙውን ጊዜ “የዚህ ዓለም ልጆች” ገንዘባቸውን ወይም ሥልጣናቸውን ውለታውን ሊመልሱላቸው ከሚችሉ ሰዎች ጋር ለመወዳጀት በብልጠት ይጠቀሙበታል። ስለዚህ “የብርሃን ልጆች” የሆኑት የአምላክ አገልጋዮችም “የዓመፃ ገንዘብ” የሆነውን ቁሳዊ ንብረታቸውን ራሳቸውን መጥቀም በሚችሉበት መንገድ በጥበብ ሊጠቀሙበት ይገባል።

ሆኖም ኢየሱስ እንዳለው በሀብታቸው ወዳጅነት መመሥረት ያለባቸው “በዘላለም ቤቶች” ሊቀበሏቸው ከሚችሉ ጋር ነው። ለታናሹ መንጋ አባላት እነዚህ ቤቶች የሚገኙት በሰማይ ነው፤ ለ“ሌሎች በጎች” ደግሞ እነዚህ ቤቶች የሚገኙት ገነት በምትሆነዋ ምድር ነው። በእነዚህ ቦታዎች ሰዎችን ሊቀበሉ የሚችሉት ይሖዋ አምላክና ልጁ ብቻ ስለሆኑ የመንግሥቱን ዓላማዎች ለመደገፍ የሚያስችለንን ማንኛውንም “የዓመፃ ገንዘብ” በመጠቀም ከእነሱ ጋር ወዳጅነት ለማዳበር ትጉዎች መሆን አለብን። ቁሳዊ ሀብት ዋጋ ቢስ መሆኑ ወይም መጥፋቱ አይቀርም። በዚህ ጊዜ ዘላለማዊው የወደፊት ሕይወት ተስፋችን የተረጋገጠ ይሆናል።

ኢየሱስ በመቀጠል በእነዚህ ቁሳዊ ወይም አነስተኛ የሆኑ ነገሮች የታመኑ ሰዎች የላቀ ዋጋ ባላቸው ነገሮችም የታመኑ እንደሚሆኑ ገልጿል። “እንግዲያስ” በማለት ኢየሱስ ንግግሩን ቀጠለ፤ “በዓመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፣ እውነተኛውን ገንዘብ [መንፈሳዊ ነገሮችን ወይም የመንግሥቱን ጥቅሞች ማለት ነው] ማን አደራ ይሰጣችኋል? በሌላ ሰው ገንዘብም [አምላክ ለአገልጋዮቹ በአደራ የሰጣቸውን የመንግሥቱን ጥቅሞች] ካልታመናችሁ፣ የእናንተን [በዘላለም ቤቶች የሕይወት ሽልማት] ማን ይሰጣችኋል?”

ኢየሱስ በማጠቃለያው ላይ እንደገለጸው በአንድ በኩል የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች ሆነን በሌላ በኩል ደግሞ ለዓመፃ ገንዘብ ማለትም ለቁሳዊ ሀብት ባሪያዎች መሆን አንችልም:- “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፣ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።” ሉቃስ 15:​1, 2፤ 16:​1-13፤ ዮሐንስ 10:​16

▪ በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው መጋቢ ከጊዜ በኋላ ሊረዱት የሚችሉት ወዳጆች ያፈራው እንዴት ነው?

▪ “የዓመፃ ገንዘብ” ምንድን ነው? በዓመፃ ገንዘብ ወዳጆች ማፍራት የምንችለውስ እንዴት ነው?

▪ “በዘላለም ቤቶች” ሊቀበሉን የሚችሉት እነማን ናቸው? እነዚህ ቤቶችስ ምንድን ናቸው?